ገብሬ ሞረዱ፣ማይጨውና የጃንሆይ ጉብኝት!

እንዴት ነበር የኖርነው… ካለፈው የቀጠለ…


«ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!

ንጉስ ነገስትህ!ንጉስ ነገስትህ!
ኃይለ ስላሴ!ኃይለ ስላሴ!
ሊ ጎ በ ኙ ህ! ሊ ጎ በ ኙ ህ!
ይመጣሉና!ይመጣሉና!
ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!

ቀዬህን አፅዳ!
አጥርህን እጠር!
በርህንም ቀለም ቀባ!
ብለውሃል!ብለውሃል!
ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!»

የገብሬ ሞረዱ ጡርንባ ብዙውን ጊዜ ሰው ሲሞት ለቀባሪ የሚደረግ ጥሪ ነው። የሚለው ነገር ግን ከሩቅ በደንብ ስለማይሰማ የየሰፈሩ ልጆች ሮጠው አጠገቡ ይደርሱና ዜናውን አጣርተው ለወላጆቻው ያደርሳሉ።  ልጆች ግን ጡርንባውን እንዲያስነፋቸው ሲማፀኑት እሺ ስለማይል ያናድዳቸውና ካጠገቡ ራቅ ካሉ በኋላ ድንጋይ ይወረውሩበታል። አንዴ እንደውም ጉቱ የወረወረበት ድንጋይ ፈንክቶታል። ስለዚህ ልጆች ሲጠጉት፤
“ገብሬና ልጅ፤
ሩቅ ለሩቅ።
ሽፍሮ ሁሉ!
ራቅ በሉ!” ይላል! አይወደንም።
የንጉሱን ጉብኝት ለማስተናገድ ሁሉም በየፊናው ሽር ጉድ ይዟል። የነከተማ ቤት መንገድ ላይና ከሰፈሩም ሁሉ ከሚሻሉት ቆርቆሮ ቤቶች አንዱ ነው። ግቢውም በጥሩ የሺቦ አጥር የታጠረ ነው።  የቤታቸውም የእንጨት መስኮቶችም ሆነ የዋናው መግቢያ በር በውሃ ሰማያዊ ቀለም ጋሽ ጎይቶም ሶስት ብር ተከፍሎት አሳብዶ ቀብቶአቸዋል። ልጆችም በየሰፈሩ የሚያዩትን የቅብ አይነቶች እያወዳደሩ፤ይሄ ያምራል! ይህ አያምርም! እያሉ መሟገቻ አግኝተዋል።
ጎባ አውሮፕላን ማረፊያው እከተማው ማሕል ስለነበር የንጉሱ አቀባበል ምክንያት በማድረግ፤ በአውሮፕላን ማረፊያው ሜዳ ግራና ቀኝ የሚገኙት ቡና በቶች፣ መኖሪያ ቤቶችና የጋሽ አደም ሻይ ቤት ሳይቀሩ ቀለም ተቀብተው አምሮባቸዋል።

ጋሽ አደም እስላም ነው። የጎባ ልጅ ሆኖ የርሱን ፓስቲ/ማይጨው/ቆቀር ያልበላ የለም። ማይጨው ጋሽ አደም ቤት ሲታዘዝ ስነ ስርዓቱ እንዲህ ነው። ከፕላስቲክ በተሰራ ጎድጓዳ ሳህን አራት ይቀርባል። በይው ከአራቱ ሁለቱን ‘ከበድ የሚሉትን’ ያነክትና፤ “ለውጥ” ይላል! ሌሎች ሁለት የተሻሉ ይቀርቡለታል። ከተለወጠው አንዱን ወይም ሁለቱንም በልቶ ሂሳቡን ከፍሎ፤ ግራና ቀኝ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ከሻይ ቤቱ ውልቅ ነው!  ወላጆች ልጆቻቸው ሻይ ቤት እንዳይለምዱ በጣም አድርገው ይቆጣጠራሉ።
ጋሽ አደም ቤት ገብቶ በልቶ ሲወጣ የታየ፤ “ገንዘቡን ከየት አባክ አመጣህ? እቤት የምትበላው አጥተህ ነው ያን በዘይት የተጨማለቀ ሞፎ የምትገምጠው?” ተብሎ መገረፉ አይቀሬ ነው። ሲጋራ ማጨስማ በጭራሽ የሚታሰብ አልነበረም። እንደ ትልቅ ብልግና ይቆጠር ነበር። እናንተ የዛሬ ወጣቶች ጭስና ጫት ይለያዋችሁዋል እንዴ? በእኛ ጊዜ ጎባ ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው የኪስ ገንዘብ አይታወቅም። ያው ለእንቁጣጣሽ አበባ ሲዞርና በሆያ ሆዬ ጊዜ የሚገኝ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ጊዜ በየሳምንቱ ብእሬ ጠፋ፣ ወይም ቀዘነ፣ እርሳሴ ተስነጠቀ በሚል ሰበባ ሰበቦች ነው ለማይጮው መግዣ የሚገኘው። ፊልም ቤት የሚባል የለም። ባሌ ዳርቻ ነው። በተፈጥሮ ሃብት የታደለ ጨለማ አገር ነበር።
አንዴ ከተማ የማይረሳው ነገር ጋሼ አደም ሻይ ቤት የሆነውን ነው። የትምህርት ቤት ጓደኛው ብሩክ  እናቱ ከጋሽ አደም ጋር የወተት ኮንትራት ስላላቸው፤ ሁለት ጮጮ ወተት( አራት ሊትር) ወደ ጋሽ አደም ሻይቤት ያደርሳል። ሰለዚህ ብሩክ ሻይ ቤት ለመግባት 'ሕጋዊ ሰውነት' አለው ማለት ነው። በዚህ መሰረት ማይጨው ሲበሉ እንዳይታዩ የሚፈሩ ልጆች እንዲገዛላቸው ፍራንክ ይሰጡትና  ለአገልግሎቱ አንዳንድ ማይጨው ‘ይወጉታል’። ታዲያ ይህቺን ለምዶ ወተቱን ካደረሰ በኋላ ካሁን ካሁን ተወጊ መጣ እያለ ሲንከራተት ከተማ ዳማ ፈረሱን ካሻይ ቤቱ ጀርባ አስሮ ዘው  ሲል ይገናኙና አብረው ይገባሉ። ከተማ የዛን እለት ያለቺው አሰራ አምስት ሳንቲም ብቻ ናት። ብሩክ ከዚያቺው በጭራሽ ካልጋበዝከኝ ብሎ ፍጥርቅ አርጎ ይይዘዋል። ከተማም “እሺ ብላ የፈለከውን" ይለውና የራሱን አንድ ሻይና ሁለት ማይጨው በልቶ ለጋሽ አደም 15 ሳንቲሞ ከፍሎ ፈትለክ ብሎ ወጥቶ ፈረሱ ላይ ወጥቶ ሽምጥ ይጋልባል! ታዲያ ብሩክ ማይጨውን በልቶ እዳ መግባቱን ለእናቱ ስለተናገረ አለንጋው አልቀረለትም። የሆኖ ሆኖ በሌላ ጊዜ የከተማ ሽወዳ ትልቅ ትምህርት ስለሆነው ሌሎች ልጆች ሲጋብዙት የጋባዡን ይሁንታ፤ጋሽ አደምም አውቆት ካልሆነ ማይጨዋን አይሞክራትም!

አቀባበል

የንጉሱ አውሮፕላን ገና ከፈት ሲል ሁለት ድንክዬ ውሾች ተከታትለው ወጡ። አንዱዋ ዳለቻና ቀጭን ናት። አንደኛዋ ደግም ወፈር ያለች ድንክዬ ናት። ድንክዬዋ ንጉሱ ለሰራዊቱ ስላምታ እንዲሰጡበት ከተሰራው ደረጃ ላይ ብር ብላ ሄዳ ግራ ቀኝ ስታሽት ዳላቻዋ ደግም ለንጉሱ መቀበያ በተዘጋጀው አዳራሽ ውስጥ እየዞረች ማነፍነፋ ጀመረች።

ጃንሆይ ከአውሮፕላን ብቅ አሉ!እልልታው ቀለጠ! ውሾቹ ግን ስራቸውን አልጨረሱም። ወደ አውሮፕላኑ አጠገብ ሄደው ማሽተት ጀመሩ። ደግሞ ከሩቅ አንድ የጥቁር ቡራቡሬ የሰፈር ውሻ አይተው  ገና ቡፍ! ቡፍ! ማለት ሲጀምሩ ፖሊስ ነብሱ እስክትወጣ እየሮጠ የመንደሩን ውሻ ሲያባርረው ከተማ በአንድናቆት ከአክስቱ አጠገብ ሆኖ ያስተውላል። ንጉሱ ለተቀበላችው ሰው ንግግርም አላደረጉ። ለተሰላፊው ወታደር ሰላምታ ስጥተው የአቀባበሉ ስነስርአት ካላቀ በኋላ ላንድሮቨር መኪናቸው ውስጥ ገብተው ወደ እንደራሴው ግቢ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ እንደገና እልልታው ቀለጠ። እንደ የከተማ አክስት ከሆነ፤ “የንጉሱ ፊት እንደ ፀሃይ ስለሚያበራ ደፍሮ ለማየት አይቻልም።” “መኪናቸውም ነቅነቅ ሲል መሬቷም አብራ ቀጥቀጥ! ቀጥቀጥ! ቀጥቀጥ! ቀጥቀጥ አለች!”

በማግስቱ ጃንሆይ የፖሊስ መምሪያን ይጎበኛሉ። ከተማም በእርሳቸው አቀባበል ሰበብ የተገዛለትን አዲስ ልብሱን ለብሶ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ሆኖ  መኪናዋን ይከተላል። ጃንሆይ አንድ ቀይ ሰውዬ በሚነዱት ላንድሮቨር ገቢና ውስጥ ተቀምጠው እጃቸውን ወደ ውጭ አውጥተው ግራና ቀኝ በመኪና መንገዱ ዳርቻ ለቆመው ሕዝብ ያወዛውዛሉ።
ብዙዎች የማመልከቻ ወረቀታቸውን ይዘው ወደ እርሳቸው መቅረብ ቢሞክሩም አልቻሉም። ማመልከቻቸውን ግን አንድ ረዢም ሰውዬ ይቀባላቸው ነበር። የማመልከቻው ጉዳይ “ግብር በዛብን ይማሩን” ነው።
እነ ከተማ የንጉሱን መኪና እየተከተሉ ፖሊስ መምሪያ ደረሱ። እዛም ለእርሳቸው ክብር በሰራዊቱ የታየውን  የጁዶና የአክሮባት ችሎታ በማየት እጅግ ተደነቁ። ከዚህም በላይ ንጉሱን አስር ሜትር እንኩዋን በማይሆን ርቀት የማየት እድል አጋጥሟቸው ነበር። ለእነ ከተማ እንደ ከተማ አክስት ሳይሆን ጃንሆይ ፈታቸውም የሚታይና በጣም የከሱና አጭር ነበሩ።

ልጆች ከጃንሆይ ብር ለመሸለም በሶስት ረድፍ እንዲሰለፉ ተደረገ። ከተማ ሁለተኛው ረድፍ ላይ ተስልፏል። በመጀመሪያው ረድፍ የተሰለፉት አንዳንድ አዲስ ሽከካ ብራቸውን እንደተቀበሉ፤ ለአይን መያዝ ስለጀመረ  መኪናዋ መንቀሳቀስ ጀመረችና ሁለተኛውና ሰሰተኛው ረድፎች ምንም ሳያገኙ ቀሩ! ነጋዴዋ የከተማ አክስት የከቴን ቅር መሠኘት አይታ፤ ለከተማ የዛን እለት ብርዝ ብቻ ሳይሆን ሁለት ብርም አሽከመቺው። የ40 ማይጨው መብያ መሆኑ እኮ ነው በዚያኔ ሲስላ!

ጃንሆይ ለባሌዎች ሹመት ሰጥተውና ግብርም ምረው ተመለሱ። ከዚህም በተጨማሪ የቀሩትን ሽፍቶች በሰላም ለማስገባት ካልሆነም ለመደምሰስ ጃካማ ኬሎን የባሌ እንደራሴ አድርገው ሾሙ። ጃጋማ ቀይና መልከ መልካም ናቸው።


ይቀጥላል….

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!