የፋኖ አንድነት እንዴት?
ቦጋለ ካሣዬ/2025
የዚህ መጣጥፍ ዋና አላማ የፋኖ አንድነት ሕዝባዊነቱን ጠብቆ እንዲረጋገጥ ቅንና ግልጽ ውይይት መቆስቆስ
ነው።በጎደለ መረጃ ሊዳብር ይገባል።
መነሻችን/መድረሻችን
እንደሚታወቀው የአማራ ፋኖ፤ለምሳሌ በትግሉ መነሻና መዳረሻ ጉንጭ አልፋ ሰበቦች
ወደ አንድ የፋኖ አደረጃጀት ሊመጣ አልቻለም። መነሻችንም አማራ መዳረሻችንም አማራ የሚሉት፤ አብይን ከስልጣን አውርደን ብቻችንን
ወይም ሊፎካከሩን ከሚችሉ ነገዶች ጋር ስልጣን ተጋርተን፤ የወያኔን ህገ መንግስት ትንሽ አሻሽለንም ይሁን እንዳለ ተቀብለን ኢትዮጵያን
እናስተዳድራለን ማለት ነው። መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያ ደግሞ ወያኔ የተከተለውን የጎሳ ስርአት ነቅለን በኢትዮጵያዊ ዜግነት
ላይ የተመሰረተ አዲስ ስርአት ተክለን ኢትዮጵያን እንታደጋለን ነው።
እንደ የሸዋ ፋኖ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር አብደላ እድሪስ ከሆነ ግን፤በዘመነ ካሴ የሚመራው የጎጃም
አማራ ፋኖ ፣በሻለቃ ምሬ ወዳጆ የሚመራው የወሎ ፋኖና በሻለቃ ባዬና በሻለቃ ሃብቴ የሚመራው የጎንደር አንድነት የወያኔው መለስ
ዜናዊ ፈለግ ተከትለው፤ መነሻችንም አማራ/መዳረሻችን አማራ ነው መንገዳቸው።ጄኔራል ተፈራ ፋኖን ከተቀላቀለ በሁዋላ ከሜዳ የሰጠው
አስተያየት የአስራትን ፈለግ የተከተለ ቢሆንም እርሱ የተቀላቀለው የሸዋ ፋኖ አቁዋም ግን የወያኔን ህገመንግስት አጥብቆ የሚደግፍ
ነው። ጀኔራሉ ከልብ የአስራትን ፈለግ ተከታይ ከሆነ ለምን ወደ መከታው አልሄደም?
በፋኖ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) ስር የተደራጁት እዞች ደግሞ፤
መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያን ነው የሚያራምዱት።የልዩነታቸውን ሰበብ እስኪ በወፍበረር ከአደረጃጀታቸው ተነስተን እንቃኝ።
የፋኖ አደረጃጀት
የወያኔን ወረራ ለመመከት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገዛዙ ውጭ የተመሰረተው፤የፋኖ ህዝባዊ ሰራዊት በጎጃም
ነበር።መሪውም ዘመነ ካሴ ነበር።ዲያስጶራውም ከፍተኛ እርዳታ አድርጎለታል። ሌሎቹ ዘማች የፋኖ አደረጃጀቶች ጥምር ጦር ተብለው የራሳቸው
ድርጅት ሳይኖራቸው ነው ከመንግስት ጎን ሆነው ወያኔን ለመውጋት የዘመቱት። ከወያኔ ጋር በሚዋጉበት ጊዜም አገዛዙ መከላከያን እያስረገ
ኃይለኛ የፋኖ ተዋጊዎችን ያስገድል እንደነበር ለምሳሌ ፋኖ ምሬ ወዳጆ ነግሮናል። ይኼም ሆኖ ምሬ በተቻለው መጠን ከመከላከያ ጋር
አብሮ ለመስራትና ሰላም ከወረደም በሁዋላ ወደ ንግዱ ለመመለስ ነበር ሃሳቡ። ወያኔ ከተመታ በሁዋላ ግን ትጥቁን ለማስወረድ የተሸረበውን
ሴራ በመረዳቱ የምስራቅ አማራ ፋኖን መስርቶ መዋጋቱን ቀጠለ።ምሬ ስርአቱ አላሰራው አለ እንጂ ስለ ስርነቀል ለውጥ ሲናገር ተደምጦም
አይታወቅም።አሁንም ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ያለው ግንኙነት ስር ነቀል ለውጥ የማይስብ እንደሆነ አስረጂ ነው። አማራ ክልል በሚባለው ፋኖን በስፋት ለማደራጀት የከሸፉ እቅዶች እንደነበሩ ስምተናል። ዘመነ ካሴም፤ ወያኔ ከተመታ በሁዋላ
“ከመንግስት ውጭ የሚንቀሳቀስ ፋኖ ውሎ አድሮ አደገኛ ስለሚሆን መበተን አለበት።መሪዎቹም መታሰር አለባቸው፤ የሚል ምክር በአቶ
ዮሃንስ ቦያለውና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራ አማካሪ ቡድን የአማራ ክልልን አስተዳደር መክሮአልና ተጠንቀቅ!” ቢባልምና ራሱም
መረጃው ቀድሞ እንደደረሰው ቢያረጋግጥም፤ ከተሰወረበት ድረስ ከአገዛዙ ጋር ለመደራደር ብሎ መጥቶ(በአቶ ክርስቲያን ታደለ አሽማጋይነት)
በባህርዳር ተይዞ ታሰረ።
ወለጋና/ደራ
ሌላው የፋኖ አደረጃጃት ወያኔ ከተመታ በሁዋላ በወለጋና በደራ የሚጨፈጨፈውን አማራ ለመታደግና ወደ
ተቀረውም አማራ ክልል እንዳይዛመት በሚል በሻለቃ መከታውና እስክንድር ነጋ መሪነት አባይ በርሃ የገባው የፋኖ አደረጃጀት ነው።የአማራ
ፋኖ ሕዝባዊ ግንባርን(አሕግ) መስርቶ የዲያስጶራውን እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ በማስተባበር የፋኖ አደረጃጀቶች በሸዋ፣በጎጃም፣በጎንደርና
በወሎ ድርጅታዊ ቅርጽ እንዲይዙ ትልቅ ሚና ተጫውቶአል።ዛሬ ደግሞ የሸዋና የጎንደር ጠቅላይ ግዛት እዞች፣የወሎንና የጎጃም እዞች
በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) ስር አስተባብሮ እየታገለ ነው።
የአንድነት ጥሪና ሳንካው
ስለ ፋኖ አንድነት ጥሪ በቀረበለት ወቅት፤ የጎንደር ፋኖ መሪ ሻለቃ ባዬ ለብቻዬ እንጂ በአንድ ድርጅት
ጥላ ስር አልካተተም የሚል ገራሚ አቁዋም ነበር ያንፀባረቀው። ይኽ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ፤ በቅርቡ ከአፋሕድ ሳይጠበቅ
ከወጣው ሻለቃ ሀብቴ ጋር ሻለቃ ባዬ አብሮ በምክትልነት የጎደር አንድነት ፋኖ መመስረቱን ተመልክተናል።ሻለቃ ሃብቴ ጄኔራል ተፈራን
እንደአባቱ እንደሚያየው ከአንደበቱ ስምተናል።ሻለቃ ዳዊትም የፋኖን ወታደራዊና ፖለቲካ ኃይል መለየት ይበጃል የሚል ፖለቲካውን ያሽመደመደ ሰነድ
አዘጋጅተው፤ ከእንግዲህ እስክንድር ትግሉን መምራት የለበትም በማለት ቀደም ሲል ግንቦትን 7ን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ተይዘው
በሁዋላም በባልደራስ ውስጥ ‘ስራቸውን’ ይሰሩ የነብሩ ሰዎች በማሰማራት ፋኖን ከህዝባዊነቱ ወደ ደረቅ ወታደራዊ
ኃይል ብቻ እንዲያተኩር እየሰሩ ነው። በቅርቡ ከሸዋ እዝ ወደ የሸዋ ፋኖ ስሙን የለወጠው ድርጅትም የሻለቃ ዳዊትን ሰነድ ተቀብሎ
ወታደራዊውንና ፖለቲካውን መለየቱን ዶ/ር አብደላ ከበላይ ማናዬ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ነግሮናል።
የፋኖ አንድነት እንዳይሳካ ያደረገው መነሻችንም መዳረሻችንም አማራ የሚሉት፤ በፋኖ አመራር ምርጫ ሂደት
ዘመነ ካላተመረጠ በሚል ያፈሩት፣ዛሬም አንድ ላይ መሆን ያቃታቸው የፋኖ አመራሮች ናቸው። አንድነት እንዲመጣ የፋኖ ተዋጊም ሆነ
ህዝቡ እምቢ ያሉት ላይ ጫና እንዲያደርግና በሌላ አመራር እንዲለወጡ ማድረግ ቀጥዩ እርምጃ መሆን ሲገባው፤ ለምን በአፋሕድ የፖለቲካ
መሪዎች ላይ ጥርስ ይነከሳል? ለምን እስክንድር ካለጥፋቱ ሆን ተብሎ ከዘመነ ካሴ ጋር ይጃመላል? እንግዲህ አፋሕድን ወንጃዮች በአደባባይ የሚሰጡት
ሰበብ ውሸት ከሆነ፤ ከሚሰሩት ስራ ተነስተን እውነተኛ ምክንያታቸውን መፈለግ ሊኖርብን ነው።ስለዋሹን ለትግሉ ቀናአኒነት ወይም አማራጭ
ሃሳብ ማቅረባቸው ነው የሚለውን መንገድ አንከተልም።ይኼ የሞኝ መንገድ ነው።ጊዜ ማጥፋት ነው።
መረብና አምሮት ?
ብ/ጄ ተፈራ ገና በልጅነቱ ኢህዲንን(አንዱ መስራቹ አንዳርጋቸው
ጽጌ ነበር፤ ወደ ብአዴን የተለወጠው ድርጅት) ተቀላቅሎ ከእስራኤል ስልጥነው በመጡ ኮማንዶዎች ሜዳ ላይ የሰለጠነ፣ ወያኔ ስልጣን
ከያዘ በሁዋላ ራሱን ለማሻሻል ብዙ የተጋ ሰው ነው። በየትኛውም የሚሊትሪ አካዳሚ ለመማር እድል አላገኘም። ጄኔራሉ ወያኔን ለመገልበጥ
ከጣሩትና የአማራ ክልልን በወረረበት ጊዜም ልዩ ኃይሉን አዋግቶ ድል የተቀዳጀ ነው።ሃሳቡም የአማራ ልዩ ኃይል ሃላፊ ሆኖ ማገልገል
ነበር።አብይ አህመድ ፈርቶት ቶሎ አነሳው እንጂ።ይሁን እንጂ እንደ ሻለቃ ዳዊት፤ጄኔራል ተፈራም ለኢሳያስ አፈወርቂ አሳሳቢ
ቀናነት የሚያሳይ ሰው ነው።ይኼም የሚያሳየው የፖለቲካ አቅሙን ውስንነት ነው።በአደባባይ ፊቱ እየበራ "ሕግአኤ"
ሲል አድምጬዋለሁ።ጄኔራል ተፈራ ማወቅ ያለበት ጉዳይ ግን እርሱ ተሳትፎበት የከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ራሱ የሻእቢያ እጅ አልነበረበትም
ብሎ መደምደም ከባድ መሆኑን ነው።የዚህም ዋናው ምክንያት ወያኔን እንጥላለን ይሉ የነበሩትና በሻእቢያ ይደገፉ የነበሩት፤
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ...'' አማራ ከእንግዲህ ወደ ስልጣን ከመጣ ማንንም ድርሽ አያስደርግም" በሚል
የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ ለወያኔ በማሳወቅ እንዲከሽፍ የተጫወቱን ሚና በአማራ ድምጽ አዘጋጅ ደምስ በለጠ ቀርቦ ያጋለጠው የፈንቅለ-መንግስቱ
የውጭ አስተባበሪያቸውን ምስክር ማጤን ወሳኝ መረጃ ስለሆነ ነው። ደምስ አብይ ስልጣን እንደያዘ ውሎ ሳያድር ወደ አገሩ ገብቶ እስካሁን ባልታወቀ
ምክንያት ህይወቱ አልፎአል።የሆኖ ሆኖ የሻለቃ ዳዊትን ሰነድ ተከትሎ፤ተፈራ የጦር መሪ እንዲሆንና እስክንድርም
ሄሊኮፕተር ተልኮለት ከሜዳ ወደ ኤርትራ እንዲወጣ የቀረበው ሃሳብ ሲጤን-- የሻእቢያ መረብ በፋኖ ውስጥ እንደተዘረጋ
ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሰሞኑንም ሻለቃ ዳዊት ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ እንዲሆኑም መጣጥፋቸውን አጠናክረው የመበተናቸው ነገር
ይኼንኑ የኤርትራ ሚና የሚሳይ ነው። ይኽ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮ-360 በቅርቡ ተፈራ ከእስክንድር ጋር የሚያቃቅር ነገር እንደሌለው፤
ግን ደግሞ ወደ ሚዲያ ለመምጣት እንደማይፈልግ የሚል ደግ ነገር ነግሮናል።ተፈራ ብአዴንን ትርፋ አንጀት ብሎ የፈረጀ ሰው
እንደመሆኑ፣ የጎሳን ፖለቲካ የማይደግፍና እኔ መሪ ካልሆንኩ የማይል ሰው ከሆነ፤ የወያኔን ህገመንግስት
የሙጢኝ ካለው የሸዋ ፋኖ አጋሮቹ ወጥቶ ወደ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት መቀላቀል አለበት። ይኼን ማድረግ ካልቻለም የሸዋ ፋኖ አመራር ከአጭር
እይታ እንዲወጣ ተገቢውን ሚና መጫወት አለበት እንጂ አይናአፋር ጄኔራል መሆን የለበትም።
ዐይንአውጣ
ጄኔራል ተፈራ በሚዲያ አልቀርብም ሲል ከርሞ ፤አሁን በቅርቡ አፋሕድ ባካሄደው የውጭ ግንኙት የተነሳውን አቡዋራ ተከትሎ ካላምንም መረጃ..."እስክንድር ትግሉ ከብዶታል"'፤ "የተደረገው ድርድር ነው።" ከማለት አልፎም የእስክንድርን ስብእና የሚነኩ ተራ ቃላቶችን በመጠቀም፤ ከበቃሉ አላምረው ጋር ባደረገው ቆይታ ትንሽ ሰው መሆኑን አሳይቶናል።አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ሚዲያ አልመጣም ያለው ሰውዬ፤ እንዲህ ያለ አስተያየት መስጠቱ የፋኖ የጦር መሪ የመሆኑ ህልም ይተንብኛል ከሚል የስልጣን አምሮት ለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው።አንዳርጋቸው ጽጌም በመሳይ መኮንን ቀርቦ፤ "ድርድሩ አደገኛ ነው። ፋኖ በሌላ መልክ እየተደራጀ ያለውን መንገድ የሚጎዳ ነው" ያለው ጉዳይ ከዚሁ ከተፈራ የስልጣን አምሮት ጋር የሚስማማ ከመሆኑ በተጨማሪ የሻእቢያው ተላላኪና ቀንደኛ የአማራ ደመኛ ጠላት አንዳርጋቸው ጽጌ የአማራን ሕዝባዊ ትግል ለመግደል ዛሬም እየዶለተ እንደሆነ በቂ ማሳያ ነው።
ልክፍት
ዳዊት ደርግን ለመጣል ከሻእቢያ ጋር ሰርተው ዛሬ ኢትዮጵያ ለደረሰቺበት ውድቀት እንድትዳረግ አስተዋፅኦ
አድርገዋአል።ሌላው ይቅርና በ What a life! መጻህፋቸው ውስጥ የመጀመሪያው ከሻእቢያ ጋር ተመሳጥረው ደርግን
ለመገልበጥ የተደረገው ሙከራ ለምን እንኩዋን እንደከሸፈ አላውቅም በማለት ሳይጠቅሱት አልፈዋል።ለሻእቢያ የኢትዮጵያን ሚስጥር አካፍሎ
ጥሩ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ጉም መዝገን ነው። ሻእቢያ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ሃይል ሆኖ ለመውጣት መንግስቱ ሃ/ማሪያምን ማስወገድ
ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ጦር መበተን ዋናው ስራው ነበር። እርሱ እንኩዋን ባይችለው ኢትዮጵያ ጠንካራ ጦር እንዳይኖራት ለሚሹ ወገኖች
ሚስጥር አሳልፎ መስጠት እንደማይመለስ ማሰብ የፖለቲካ ሁ ሁ ነው። ለዚህም ነው የመንፈቅለ መንግስቱ ሙከራ ከሽፎ ጄኔራሎቹም ተረሽነው
ጦሩ እንዲፈርስ የተመቻቸው። ዛሬም ዳዊት ከዚሁ ከሻእቢያ ጋር ያላቸው ልክፍታዊ ቁርጭት በፋኖ ሕዝባዊነትና አንድነት ላይ
ማነቆ ገመድ እየሸበበ ሊሆን ሰለሚችል አጥብቀን ልንታገለው ተገቢ ነው።ፋኖ ሕዝባዊና ትግሉም የተጀመረው ኢትዮጵያ እምብርት ላይ
ስለሆነ ቀደም ሲል እንደከሸፉት፤ የከፋኝ፣የአርበኞች ግንባርና የግንቦት-7 ትጥቅ ትግሎች በሻእቢያ መረብ መተብተብ የለበትም።
ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካው በመርህ ላይ ተመስርቶ ትግሉን መቀጠል አለበት። ይሁን እንጂ ኤርትራ ለፋኖ ካለቅደመ ሁኔታ እርዳታ ብታደርግ
ምንም የሚያስከፋ ነገር የለውም። ኤርትራ ግን ለአማራም ሆነ ኢትዮጵያ መሪ መራጭ መሆን የለባትም።ወታደር የተቆጣጠረውን
አራት ኪሎ ለሲቪል አስተዳደር ያስረክባል የሚለው የዳዊት ቀልድም፤ ላም አለኝ በሰማይ ወተትቱዋንም አላይ እንደማለት ነው።አዲሱ
ትውልድ እንዲህ ያለውን ሽወዳ ወይም መደናበር 'አይነፋም' ይለዋል።የሸዋ ፋኖ እንዲህ ያለውን ቂላቂል ሃሳብ የተቀበለው በራሱ የቆመ
ድርጅት አለመሆኑን ነው የሚያሳየው። በእርግጥ ጦሩ በአብዛኛው የተመሰረተው በወርቁ አይተነው ገንዘብ እንደሆነ ቀደም ሲል ኢፋ ሆኖአል።
ዳዊት የአሕግ ዲያስጶራውን ውክልናቸውንም ሲመሩ ከርመው፤በአደባባይ በሰጡት አወዛጋቢና ግልፍተኛ አስተያየቶች
ራሳቸውን ለህዝበኛም ሆነ ለሃቀኛ ተቺዎች ያመቻቹ ናቸው። አማራ ጨቁዋኝ ነበር ብለው አምነው የጻፉትን እንኩዋን ተፀፅተው ማረም
ሲገባቸው የሚመሩትን ድርጅት ችግር ላይ የጣሉ፤እውቀትና ልምድ ያላቸው ግን በ20 አመታቸው በተነደፉት ያገር ፍቅር ኢትዮጵያን እንደ
ግል ንብረታቸው አድረገው የሚቆጥሩ ሰው ናቸው። የሚገርመው ደግሞ ከፋኖ ጋር ግንኙነት አለኝ ይላሉ እንጂ የፋኖ አደረጃጀቶች በመድረሻና
በመነሻ ልዩነታቸውን በግልጽ እንደሚያራምዱ እንኩዋን መረጃ ያላቸው አይመስልም።ወይም አውቀው እንዳላወቁ ይሆናሉ።
ሌላው ከሻእቢያ የበለጠ በትግሉ ላይ መረብ ሊጥል የሚችል ወያኔ ነው።የወያኔ ተጽእኖ ደግሞ በተለይ በጎጃም የአማራ ፋኖ 'የአማራ ሕዝብና የትግራይ ሕዝብ' መሰረታዊ ቅራኔ የለውም በሚል ሰበብ ለወያኔ ያሳየው ሥስ ልብ፤ ለምሳሌ በጎጃም ታስረው የነበሩትን ወታደራዊ መኮንኖች መልቀቅና ተማርኮ የነበረውን ኮሎኔል 'ጠፋ' በሚል መሸኘቱ አሳሳቢ የትሥሥር ገላጮች ናቸው። በጎንደርም ሆነ በወሎ የፋኖ አንድነት እውን እንዳይሆን ወያኔ ተኝቶ የማያድረው የራያና የወልቃይት የግዛት ነጠቃ ጥያቄዎቹ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰሩ ስለሆነ ነው።
ማጠቃለያ
መነሻችን አማራ መዳረሻችን አማራ አድማሰ አጭር የወያኔ መንገድ ነው።ከፋፍለህ ግዛውና የቅኝ ገዚዎች
ሃሳብ ነው።የሌቦች መሸሸጊያ ነው። ላለፉት 33 አመታት ሰላም አላመጣም። አማራውን ይሁን የተቀረውን የኢትዮጵያ ነገዶች ከድህነት
አረንቁዋም አላወጣም። በዚህ መንገድ የፋኖ አንድነት አይመጣም።
ለአማራም ሆነ ለማንኛውም በኢትዮጵያ ለሚኖር ነገድ በታሪካዊ ዳራና በኢኮኖሚ ካሰላነው ድህነትን አሽቀንጥሮ
የሚጥለውና ስላም የሚያስፈነው በመዳረሻን ኢትዮጵያ ትግሉ ሲቁዋጭ ነው።ይኽ አቅጣጫም የተፈራው ሌቦችና ነገዳውያን ባለፉት 32 አመታት
ካለአግባብ ያጋበሱትን ሃብት እናጣለን ከሚል ተጨባጭ ስጋት ነው።
የፋኖ ትግል መሰረቱ ህዝባዊ ስለሆነ ፖለቲካውና ወታደራዊ አደረጃጀቱን መለያየት አያስፈልግም። መለያየቱ
አደጋ አለው። ምክንያቱም ከድል በሁዋላ ወታደሩ ወይ ስልጣን አለቅም፤ ወይም ባልታገሉ አድርባዮች ተከቦ ራሱን እንደ ደርግ ወደ
ሲቪል ቀይሪያለሁ ለሚል ሌላ አዙሪት ሊዳርግ ስለሚችል ነው። ይኼ ደግሞ በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች የታየ ነው።
የፋኖ አደረጃጀቶች በየጊዜው እውቀት፣ችሎታና ብልሃት ያላቸውን መሪዎች ወደፊት ማምጣት የሚያስችላቸው
ደንቦች ያስፈልጉዋቸዋል።አንዱ ለአንድነት አስቸጋሪ የሚሆነው ጉዳይ በድርጅት ውስጥ ቀደም ብለው የመሪነት ቦታ በአጋጣሚ የተቆናጠጡት
ሰዎች ትግሉ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ አቅማቸውን ስለሚፈታተነው ለተሻለ ሰው አሳልፎ መስጠት ድፍረት ስለሚያጡ ነው። በዚህ
ረገድ ለምሳሌ በምሬ ወደጆ የሚመራው የፋኖ አመራር የፖለቲካ አመራር ዝግጅቱ በጣም ውስንነት እንዳለው የአደባባይ ሚስጥር ነው።የዚሁ
ፋኖ አደረጃጀት የፖለቲካ ክፍል ሃላፊ ፋኖ አበበ ብስለት በኮሎኒል ፋንታሁን ከሚመራው የወሎ እዝ የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ እያሱ አበራ
ጋር ሲወዳደሩ፤ እያሱ ረጋ ያለ፣አስቦ የሚናገርና ጨዋ ሰው ነው። አበበ የእርሱ ተቃራኒ ነው።ፈራጅና ትግሉን በጭራሽ ያልተገነዘበ
ፋኖ ነው።
በዘመኔ ካሴ የሚመራው የአማራ ፋኖ በጎጃም በውጭ አገር ያለውን የሚዲያ ተዳርሶት አብላጫውን ቢይዝም፤
ለትግሉ የማይመጥኑ ሃሳቦችን በየጊዜው በማሰራጨቱ ነጥሮ የሚመለሰው ግብረመልስ ጉዳት እንጂ ጥቅም አላመጣለትም። ዘመነ አሁን
ደግሞ የህልውና ትግሉን እርግፍ አርጎ ትቶ፤ ‘አብዮታችንን ሊነጥቁን ነው’ የሚል 80 አመት እድሜ የሰጠውን ጎጣዊ መፈክር ይዞ
መጥቶአል።ዘመነ በትልቅነት አባዜ የሚሰቃይ፣ ጋዜጠኛም ሆነ ሊሎች የፋኖ አባላትን አፋኝና ገዳይ ነው። የጎጃም ፋኖ የአመራር ለውጥ
ካላደረገ አሁን ላይ በአደባባይ የምናቃቸው አመራሮች ትግሉን ፈቀቅ ሊያደርጉት አይችሉም።
በአፋሕድ ስር የተሰብሰቡት የፋኖ አደረጃጀቶች በአማራ ሕዝባዊ ግንባር ስር ሆነው ለመተዋወቅና ለመተማመን ጊዜ አግኝተዋል።ድርጅታዊ መዋቅራቸውም በመርኽ ላይ የቆመ እንደሆነ በፋኖ አንድነት ምርጫ ሂደት ይሁን፤ የጎንደርን እዝ ለመበተን የተደረገውን ሴራ በጣጥሰው ፤የጎንደር ጠቅላይ ግዛት እዝና ቀጥለውም ኮር በማቁዋቁዋም ፀንተውና አቅማቸውን አሳድገው ትግላቸውን መቀጠላቸው በቂ ዋቢዎች ናቸው።ምንም እንኩዋን የሌሎች ፋኖ አደረጃጀቶች በፋኖ አንድነት ላይ አዎንታዊ አሻራቸውን ገና ያላሰፈሩ ቢሆንም፤ አፋሕድ ያለመታከት ለሌሎች የፋኖ አደረጃጀቶች የአንድነት ጥሪ ከማቅረብ አልፎ ከአንድነት ውጭ አማራጭ የለም! የሚል ጥሪውን እየደጋገመ ነው።አፋሕድ በወታደራዊና በሲቪል ህይወታቸው ለህዝብ ዋጋ የከፈሉና በትምህርታቸውና በስብእናቸው ልህቅትን ያሳዩ የፋኖ አመራር ስብሰብ ነው። ዲያስጶራውም ሊደግፍ የሚገባው ለዘለቄታዊ ድል አስተማማኝ የሚሆነውን ይኼንኑ መንገድ ነው። የተቀሩት የፋኖ አደረጃጀቶችም ሰከን ያሉ የተማሩ መሪዎችን ወደፊት በማምጣት አብሮዋቸው ከሚዋደቁት ወገኖቻቸው ጋር አንድነት መፍጠርና የአማራን ሆነ የኢትዮጵያ አበሳ የሚያበቃበትን ወቅት ማሳጣር እንዲቻል አምላክ ልቦና ይስጣቸው።
Comments
Post a Comment