አሞላቃቂ ጥቅመኛ!


ስልጡን ይሁን ገልቱ አመራር በስልጣን ላይ የማስቀመጥ ሃላፊነት የሕዝብ ነው፡፡ሕዝብ ደግሞ ሃላፊነቱን በቅጡ ለመወጣት እውነተኛ መረጃ ያስፈልገዋል። በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ካለመታከት መልካም ስነምግባርን በማበረታታት፤ ለሕብረተሰብ የማይጠቅምን ድርጊት ይሁን ሃሳብ ጠንቅነቱን በማስተማር፤ ለህዝብ ቆመናል በማለት የሚሞላቀቁትንና ሃቀኞቹን የስልጣን ተፎካካሪዎች ተከታትለው ማንነታቸውን በማስተዋወቅ  ትልቅ አጋዥ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡

ፋኖና የኢትዮጵያ ዲያስጶራ ሚዲያዎች

ፋኖ ባለፉት 2 አመታት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጀምሮ በማህበራዊና በሳተላይት መረጃ የሚያስተላልፉትን ሚዲያዎች፤ የኢሳት ፍርስራሾችና ሌሎች ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡

የኢሳት ፍርስራሾች

ወያኔን ለመታገል በግንቦት 7 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን(ኢሳት) የዲያስጶራው ድጋፍ ነበረው፡፡ብዙዎቹ ጋዜጠኞቹም ወያኔ በቅንጅት መሸነፉን አልቀበልም ብሎ ባሳረፈባቸው ዱላ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ናቸው።

ኢሳት ወያኔን ታግሎአል። ይሁን እንጂ በግንቦት 7 ፖለቲከኞች ቁጥጥር ስር ስለነበረ ነጻ ሚድያ አልነበረም። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ከሻእቢያ ጋር መስራት እንደጀመሩ፤ኢሳት ለብሄረተኞች ሰፊ መድረክ በመስጠት በቅንጅት መንፈስ ጠውልጎ የነበረውን ጎሰኝነት እንዲለመልም አፍራሽ ሚና ተጫወተ። የግንቦት-7ን የፈጠራ ወታደራዊ ኮሚንኬ በማስራጨት አማራው በተለይ በጎንደር በወያኔ እንዲመታ ዱላ አቀበለ። ኢሳት ሁነኛ ተቁዋም ሆኖ እንዲዘልቅ ከግንቦት 7 ይላቀቅ የሚለው ውትወታ በጊዜው ስሚም አላገኘም፡፡ የአገር ፍቅር እንጂ የፖለቲካ እውቀት የለኝም የሚለው የኢሳት የገንዘብ ዋና አሰባሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ፤ “ኢሳት የግንቦት 7 ቢሆንስ?” እያለ ይሳለቅ ነበር።እርግጥ ነው ለሚድያ የሚውል ከዲያስጶራው በቂ የስራ ማስኪያጃ ስለይገኝ፤ በውጭ አገር ሆኖ በቁዋሚነት የጋዜጠኝነት ስራ ለመስራት እንደ ኤርትራና ምስር ካሉ አገሮች የተገኘው እርዳታ በግንቦት 7 ላይ ብሎም በኢሳት ላይ የራሱ ቅድመ ሁኔታ ይዞ እንደሚመጣ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ወያኔ ተገፍቶ መቀሌ ከገባ በሁዋላ ኢሳት ለተወሰነ ጊዚያት የአንዳርጋቸው ጽጌ መተዳደሪያ ከመሆን እልፍ ሳይልና፤ቀሪዎቹም ጋዜጠኞቹ ፖለቲካውና ጥቅም ስለከፈላቸው ተበታትነው ዛሬ እነርሱ አንድ መሆን ያልቻሉትን፤ ፋኖ አንድ መሆን አለበት በሚል የይስሙላ ዲስኩር እያደነቆሩን ይገኛሉ።

ለምሳሌ የአንከሩ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን በአንድ ወቅት ከአፋሕዱ ጌታ አስራደ ጋር ባደረገው ውይይት ፤ አንከር ሚዲያ የፋኖ አመራሮችን በማቅረብ ለምን ወደ አንድነት እንደማይመጡ በህዝብ ፊት ለማወያየት እንደሚሰራ ቃል በገባበት አፉ፤ ብዙም ሳይቆይ 360 ዲግሪ ዞሮ ፤ ወደ ሚዲያ ብናመጣቸው የበለጠ ስለሚከፋፈሉ እዚያው ራሳቸው ጉዳያቸውን ይጨረሱ በማለት፤ ህዝብ እውነቱን እንዳያውቅና ተንኮለኞቹ እንደተሞላቀቁ እንዲቀጥሉ እድል ይሰጣቸዋል።መሳይ መኮንን ብዙ የተማሩ ሰዎችንና በጣም የተለያየ ሃሳብ ያላቸውን ግለሰቦች ያቀርባል። ግን ከኢሳት ጀምሮ ለጋዜጠኝነት የሚያሳየው ስነምግባር በእውነት ፋለጋ ላይ ሳይሆን በውገና ላይ የተመሰረተ ነው። ሌላው የኢሳት ጋዜጠኛ ደግሞ ዛሬ በ(EMS) የሚሰራው ፋሲል የኔአለም ነው። ፋሲል በኢሳት ዘመኑ የግንቦት-7 የፈጠራ የወታደራዊ ኮሚኒኬ አንባቢ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነው።በዚህ በፋኖ ትግል ውስጥ አፋሕድ የሚሰጠው መግለጫ ስሜቱን እንደሚረብሸው ከፊቱ ይነበባል። በተጨማሪም አፋሕድ በሜዳ የሚቀዳጃቸውን ድሎች እንዲሁ በፋኖ ስም ብቻ ነው የሚዘግበው። የሌሎች ፋኖ በተለይ የጎጃም ሲሆን ግን ሰማቸውን ጠርቶ ነው የሚዘግበው። እዚህ ላይ አንድ ነገር አለ። መሳይም ሆነ ፋሲል አገራቸውን አይጠሉም።ግን ሁለቱም እውነት ያለመወገናቸው ነገር ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ፤በግልፍተኝነት የሚመጣው እሳቢያችን አማሮች ስላልሆኑ ነው? የሚል ሊሆን ይችላል። ዋናው ጉዳይ ግን የጥቅም ጉዳይ ነው።እንደነዚህ ያሉ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያም ሆነ የአማራ ሰቆቃ መተዳደሪያቸው ስለሆነ የእውነት ፍለጋ ተልእኮአቸው ላይ አያተኩሩም።አሞላቃቂ ጥቅመኞች ናቸው።

የኢሳቱ ሲሳይ አጌና ገና በጥዋቱ በአብይ ስለተሞካሸ ወደ ጎራው ገብቶአል። ደረጀ ሃብተወልድ ገራ ገር ነው። ውፍረቱ ከዚያ የመጣ ይመስል፤ "የብርሃኑ ነጋ ንግግር እንደ ምግብ ይስማማኛል" የሚል ነበር።አቁዋም የለሽ ነው ደሬ። የሆዱ ነገር አይሆንለትም። የበረከት ስምዖን ግርፉ ኤርሚይስ ለገሰም በራሱ አድርባይነት ነው ከኢትዮ-360 የወጣው። ብዙም በኢሳት ላይ ያልሰሩት ምናላቸውና  ሃብታሙ አያሌው በጣም ተቃራኒ ሰዎች ናቸው። ምናላቸው የሚቀናው መንሸራተት ነው። ሃብታሙ ግን አቀበት መውጣት የማይሰለቸው ለእውነት የቆመ አከርካሪ ያለው ጋዜጠኛ ነው። የሃብታሙ ችግር ተዳርሶት ነው። ዩ-ቱዩብ በየቀኑ ይዘጋዋል። እርሱም ትንታኔውን ስለማያሳጠር(በጣም ይደጋግማል) ጊዜ የሌለው ሰው የሚናግረውን ጨርሶ ለመስማት አይችልም። ለአማራ በእውነት የቆመ ጋዜጠኛ አንድ ጥራ ብባል ሃብታሙ አያሌው! ነው። እየሩሳሌም ሌላዋ ናት።  

ይሁን እንጂ ኢትዮ-360ም የፋኖ አመራሮች አንድ እንዲሆኑ ብቻ ከመናገር በስተቀር መሪዎቹን በሚዲያው አቅርቦ ለምን አንድ እንደማይሆኑ ሃሳባቸውን ህዝብ እንዲያውቀው የወሰደው ተነሳሽነት እንዳለ አላውቅም።በዘመኔ ካሴ ተክለሰውነት የደነዘዙ የፋኖ አመራሮች ለኢትዮ-360 መግለጫ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እየሩሳሌም “ሁዋላቀር” ነው ብላ ስትበሳጭባቸው አድምጪያታለሁ።

 ቦጋለ ካሣዬ

ይቀጥላል

 

 

 

 

 

 

 

 

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!