እብሪት፣ምቀኝነትና ሕሊና ፤ ከሎሬት ፀጋዬ አንደበት



ባለፈው ስለ አፈላማ እጽፋለሁ ብዬ ነበር። የዛሬ አራት አመት የጻፉኩት ማስታወሻ ስላለኝ ወደፊት እየቆነጠርኩ አሰረጫዋለሁ። ዛሬ ግን ባለፈው ተስፋዬ ገብረአብ የሎሬት ፀጋዬን የቁዋንቁዋ ምርምር በእብሪተኛ አንደበቱ “የቃላት ጫወታ” ብሎ ማሾፉን በተመለከተ፤ ጋሽ ፀጋዬ እ.አ.አ በ 1995 ስለነተስፋዬ አይነት ሰዎች ያወጋኝን ላካፍላችሁ።

“ጋሼ ፌደል በቆጠረው መካከል ያሉት ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው”?

… ትንሽም አላመነታ። “እብሪትና ምቀኝነት”! “እብሪት በተለይ ጎልቶ የሚታየው በባለስልጣናት ላይ ነው። በትምህርትና በልምድ ሳይሞረዱና ሳይለስልሱ ስልጣን ላይ ጉብ ይላሉ። ከዚያ በሁዋላ ስልጣን የሌላቸውንና በእውቀት ይበልጡናል ብለው የሚገምቱትን ሰዎች አሽቆጥቁጠው ማዘዝና ትንሽ አድርጎ መመልክት ይጀምራሉ። ይሄ እብሪት ነው። አንተ ተግትህና ጌዜህን ወስደህ የሰራኸው ስራ፤ ካለምንም ምክንያት በአንድ እብሪተኛ ባለስልጣን እንዳይታተም፣ለሕዝብ እንዳይታይ ወይም በሌላ መልክ እንዳይሰራጭ ይደረጋል። ለማን አቤት ይባላል? እነርሱ ካሉት ውጭ ምንም መንገድ የለም። መስፍን እንዳለው ስልጣናቸው እውቀት ይሆንና ያርፋል። ስልጣናቸው ሕይወትን የሚያህል ክቡር ነገር መቅጠፍ ያስችላቸዋልና፤ እንደኔ ያለው ፈሪ ከእነዚህ ጋር አይጋፈጥም። ደፋሮች አሉ፤ እንደነ መስፍን። መስፍን? አይፈራም። ያኔ በተማሪዎች እንቅስቃሴ እንኩዋን ከተማሪዎች ጋር ይሰለፍ ነበር።”
“ሕዝቡ ግን ፌደል ከቆጠረው እብሪተኛ ባለስልጣናት የሚከላከልበት መንገድ አበጅቱዋል። ለምሳሌ በታህሳሱ ግርግር ጌዜ፤ እነ መንግስቱ ነዋይን ደግፎ ነበር። ወዲያው ደግሞ ግልበጣው እንደከሸፈ ሲረዳ፤ ያው ሕዝብ እንደገና ወጥቶ ድጋፉን ለንጉስ ነገስቱ ሰጠ። የሚገርም የሚደንቅ ነገር ነው። እንደ ፈረደበት ካንዱ ወዳንዱ እየተላተመ እስካሁን ይኼው በስቃይ አለ። አንዴ ፈንቅሎ ወጥቶ በቃኝ የሚልበት ቀን ግን ይመጣል።”

“ምቀኝነትም ከእብሪት ጋር ትሥስር አለው። አንድ አውራ/ጎበዝ ሲወጣ፤ እንደ እርሱ ለመሆን እፈልጋለሁ! መጣር መጣጣር አለብኝ የሚል መንፈሳዊ ቅናት ይጎለናል። እንደውም የሚቀናን አውራውን እንዴት አድርገን እንደምናጠፋው ዘዴ መፈለግ ነው፤ ተንኮል መጎንጎን ነው። ይኼ አንዱ የሕብረተሰባችን ካንሰር ነው። ”

ቀጠልን ወጋችንን… “ጋሼ፤ የአርባጉጉና የበደኖ አራጆች ሕሊና አላቸው?”


“አዎ! ሰው ሁሉ ሕሊና አለው። የአንዱ ሕሊና የሰላ ነው። ቅርብ ነው። በራሱ ላይ ሊደረግበት የማይፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አያደርግም። አልፎ ተርፎም እውነተኛ ነጻነትን ይሻል። ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። ጴጥሮስ ያደረገው ይህንኑ ነው። ሕሊናቸውን በውስጥ እግራቸው እየረገጡ የሚኖሩም የሰው አውሬዎች ሞልቶውናል። እነዚህ አራጆች ቀን ሲጎልባቸው የሚባንኑበት ቀን ይመጣል። ሰው ገድለህ በጭራሽ ሰለም አታገኝም። አንድ የማምነበት አባባል ነበር። “ስቃይን ያየና የቀመሰ በሊሎች ላይ ክፍት አይሰራም የሚል።” ትግራይ በርሃቡ ወቅት ሄጀ ነበር። እህል ለመሰፈር ከተሰለፉት መካከል፤ እስኪ ስጡኝ አልኩና የአንዱዋን እናት ልጅ አቀፍኩት። እዚያው እጆቼ ላይ እንዳለ አረፈ። ግን አሁን ተመልከት ወያኔ ምን እንደሚያደርግ? ይገላል?ያስቃያል? ሻእቢያም ያው ነው። ሁለቱም መተቱ!! ስለዚህ “ስቃይን ያየና የቀመሰ በሊሎች ላይ ክፍት አይሰራም የሚለውን አባባል እንዳለ ለመቀበል ከእንግዲህ አልችልም።”

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!