መልሰ ብዬ ሳየው...4


...
አሳዬ ከሐሰን ቱሬና ከከዲር ዋቆ ጋር ተገኛኝተው መንግስት ደኑን በጄት ለመደብደብ አስቧልና ይህ ጉዳት ከመደረሱ በፊት በሰላም እጃቸውን ለመሰጠትና የሚይቀርቡትም ቅደመ ሁኔታ ካላ ቀጥታ ከእንደራሴው ጃጋማ ኬሎ ጋር ለሁለቱም አመቺ ቦታ ፈልገው ለማገናኘት እንደሚሞክሩ  ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት... ሐስንም ሆነ ከዲር እንዲሁም ሁሴን ዳዲ፤ በከር ጂሎና ሐጂ ተመካክረው ተስማሙ። መጀምሪያ ግን ከከዲር ዋቆ ወደ ሰላም እንዲገባ እንፈልጋለን። እኛም ሁኔታውን እያየን ተራ በተራ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ለመመለስ ማለትም እጅ ለመስጠት ፍላጎት አለን።  ካሳሁን ስምምነቱን ይዘው ከሃሰን ቱሬ ሰላይ ኡመር ሃስን ጋር ወደ ጎባ በማቅናት ከእርሳቸውም ሆነ ከሐሰን ቱሬ ወዳጅ ከሆኑት አቶ ንጉሴ ገረመድሕን ቤት በሁለተኛው ቅዳሜ እቴቱ ላይ ደርሰው አዳር ያደርጋሉ። እቴቱ ከጎባ 10 ኪሎ ሜትር የምትርቅ የገጠር ቀበሌ ናት። በማግስቱም ኡመርን ንጉሴ ቤት ትተው እነ ከተማ ከእንቅልፋቸው ገና ሳይነሱ፤  ልጆች! ከተማ! አቡ! በሩን ክፍተሉኝ ሲሉ ተጣሩ።

አሳዬ ጃጋማን በአስቸኳይ ለማነጋገር ቀርቶ ስልጣናቸውም በቀጠሮ እንኳን ቢሆን ለማነጋገር ስለማያስችሏቸው ዘዴ መፈለግ ነበረባቸው። ጊንር ሰራተኛ በነበሩበት ጊዜ በጣም ወዳጃቸውና ጃጋማን በቀላሉ ለማግኘት የሚችል በቀለ ቱሉን ማነጋገር ነበረባቸው። እንዳሰቡትም በቀለ በሌላ ሁነኛ ሰው በኩል መልእክቱን ለጃጋማ እንዲድደርስ አንደረጉ። ጃጋማም በመገረም አቶ ከበደን ሰኞ ጥዋት በ 2.00 ቢሮአቸው እንዲመጡ አስጠሩዋቸው። ማታውኑ ከበደ የሆነውን ለካሳሁን ሲነግራቸው በጣም ተደስተው ጃጋማ ከተመቻቸው ንፍስ ለመቀበል ብለው በመኪና እቴቱ ድረስ ላይን ያዝ ሲል ቢመጡ ኡመርንም ማነጋገር እንደሚችሉ ያውቁት ዘንድ ለአቶ ከበደ አደራ ይላሉ።
ይህ በእዲህ እንዳላ ከምሽቱ አስር ሰአት ሊሞላ ሲል የጃጋማ መልክተኛ አቶ አሳዬ ቤት ደርሶ ጥዋት በ 2 ሰአት ቢሮ እንዲገኙ የሚል ትእዛዝ ይደርሳቸዋል። ካሳሁን ወዲያውኑ በቀለ ቤት ገስግሰው ሄደው እኔ ካሁኑ እርሳቸው ጋር ስቀረብ ከታየሁ ከፍተኛ ባለስልጣን ስላልሆንኩኝ የፈጠራ ወሬ ይነሳና በየጠጅ ቤቱ ወሬው ተባዝቶ ያስብነውን ከግብ ለማድረስ አላስፈላጊ ችግር ገና ምንም ሳንሰራ ይገጥመናልና፤ በመጀመሪያ በሚስጥር መገናኘቱ እንደሚሻል እንዲነግራቸው አደራ ይሉታል።  አሁን እንደራሴው ቢሮ መሄዴን ያ ሆዳም አለማየሁ የሰማ እንደሆነ እያሴርብኝ ነው። ምናባቱ ያዳርጋል እንደራሴው ቢሮ እኔ ሳላውቅ? እያለ አገሩን ያብጣል። በብልሃት ነው ነገሩን መያዝ ጃል። እርሳቸው ለአገሩ እንግዳ ናቸው። ይሄን አስረዳቸው። 

አቶ ከበደ ጥዋት በ2 ሰዓት በቀጥሮአቸው ደርሰው አቶ አሳዬን ያልመጡበትን ለጊዜው ግንኙነታቸው በሚስጥር እንዲያዝ የፈለጉበትን ምክንያትም  አስረዱ። ጃጋማም በነገሩ በጣም ተደንቀው ማክሰኞ እለት ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ አሳዬ ከኡመር ጋር ሆነው እንዲጠብቁአቸውና አቶ በቀን ግን ከእሳቸው ጋር አብረዋቸው እንዲሄዱ ጠይቀው በቀጥሮአቸው እቴቱ ጫካ ውስጥ ከአቶ ንጉሴ ቤት አጠገብ ተገናኙ። ኡመር ካላስተርጓሚ በአፋን ኢሮሞ ሽፍቶቹ እነማን እንደሆኑና ያሉበት ሁኔታና በአቶ ካሳሁን በኩል የላኩት የምህረት ጥያቄ እውነተኛ እንደሆነ ለጃጋማ ሁሉንም ዘረዘረላቸው። ጃጋማም ለምን ተራ በተራ እንጂ ሁላችሁም በአንዴ እጃቸውን አትሰጡም ብለው ላነሱት ጥያቄ፤ ብዙ ደም ስለፈሰሰ እጃቸውን በአንዴ ሰጥተው ቢታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ችግር ላይ ላለመጣል ፈርተው ነው እንጂ ምንም ሌላ ድብቅ አላማ እንደሌላቸው አሰረዳ። ጃጋማም በእውነት የሰላሙን ጥሪ ከተቀበላችሁ መንግስት አገሩን በጄት ለመደብደብ ፍላጎቱ የለውም። ይሁንና የሰላሙን ጥሬ መቀበላችሁን ብቻ ሳይሆን በተግባር ማየት ስለምፈልግ በቅርቡ ዋናው አለቃ ሐሰን ቱሬም ባይሆን በስምምነታችሁ መሰረት የአንጌቱው ከዲር ዋቆ ወደ ሰላማዊ ኑሮው መመለሱን ማየት እፈልጋለሁ። ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲያዝ በእናተ በኩል አቶ አሳዮንና አቶ ንጉሴን እንደምታምኑ አይቻለሁ። በመንግስት በኩል ለዚህ የሰላም ጥሪ የምወክለው ሌላ ሁነኛ ሰው ከአቶ አሳዬ ሌላ ሰለማያስፈልግ የምትፈልጉትን ሁሉ በርሱ በኩል ልትልኩብኝ ትችላላችሁ። አሳዬም ቀጠል አድርገው .....ክብሩነቶ ለጣሉብኝ እምነት በጣም እያመሰገንኩ፤ በኸረና ቆይታዬ እንዳየሁት አገሬው በጣም በአስከፊ ድህንትና በሽታ ስለሚሰቃይ በተለይ የወባ መድሃኒት፤ የሰንዴ ዱቄት፤ስኳር፤ሳሙና የመሳሰሉት ቢላኩላቸው በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባላሁ ። ...ወይ ጉድ አቶ አሳዬ፤ ደግም ብለህ ብለህ ጃጋማ ሽፍታ ቀላቢ ልታሰኘኝ ነዋ? .....አይ ጌታዬ ለእዚህ እኮ ነው ሁሉም ነገር ብርቱ ሚስጥር መሆን ያለበት። ዞሮ ዞሮ ሁሉም በሰላም ለመግባት ፈልገዋል። በተለይ ሕጻናቱ ወተት ቢያገኙም ወላጆቻቸው ስንዴም ሆነ በቆሎ እንደልብ ስለማያገኙ በመጎዳታቸው ብዙዎቹ እየረገፉ ነው ጌታዬ። እኔ እንኳን ሶስት ሕጻናትና 6 የአዋቂ ሬሳ ቀብሬ ነው የመጣሁት ጌታዬ። ወተትና ስጋ ብቻ በልቶ መኖር የሚችል የኸረና አንበሶችና ጅቦች ናቸው  ጌታዬ። በደሎ መና የመንግስት ጦር መጋዘን ውስጥ በቂ ዱቄቴም ሆነ መድሃኒት ስላለና ወዲሁም ቦታው ከመና ቅርብ ስለሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጦርነት ለተጎዱት ሲቪሎች ስም ወጥቶ ሊደርሳቸው ይችላል። ክብርነቶ እንዳሉትም የአንጌቱ ወረዳ ሰላም ከሰፈነባት የቅዳሜና የሮብ ገበያ ስለሚጀምር በዚህ በኩል የከዲር ዋቆን ወደ ሰላማዊ ኑሮ ቶሎ ማስመለስ ሊፋጠን ይገባል። እነሱም ይኼንኑ ተገንዝበው ነው መጀመሪያ ከዲር እንዲገባ ያሳሰቡት። መንግስት  በስፋት ይሄን አስቦቦት ካለ ምንም ደም መፋሰስ ቶሎ በደሎ አውራጃ ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይችላል ጌታዬ።

ፍታውራሪና አለማየሁና አቶ አሳዬ አይንና ናጫ ስለሆኑና አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የአቶ አሳዬ የሰላም ተልእኮ ነገሩን ስለሚያባብሰው፤ ጃጋማ ፍታውራሪን አስጠርተው ወደ አዲስ አበባ አገር አስተዳደር ሚኒስትር እንዲቀየሩ አደረጉ። አቶ አሳዬም ጥሩ አጋጣሚ ስለተፈጠረላቸው የአውራጃውን አስተዳዳሪነት ሹመት ከዛሬ ነገ በእጄ ትገባለች በማለት ሁሉንም በሆዳቸው ይዘው፤ የጃጋማ ኬሎ ልዩ መልእክተኛ በመሆን መጀመሪያ ከዲር ዋቆን ወደ ሰላም ኑሮዉ መለሱት። ከተማ የማይረሳው ከዲር ዋቆን ነው። ጋሽ ከዲር አማርኛ ትንሽ ትንሽ ነው የሚችለው። ታዲያ እስላምም ሆኖ ቦካ እየለጋ ይስክራል። ቦካ የኦሮሞ ድንግል ልጃገረዶች የሚትሉት ጠጅ ነው። ያንን በተለይ በሽፍትነቱ ዘመን እየለጋ ድፍረት ሰለሚሰጠው አሁንም በሰላማዊ ኑሮው ወቅት ካላርሱ መኖር አልቻለም። ታዲያ የከተማ እናት የጣሉትን የበሰለ ጠጅ በጣም ሰለወደደው፤ ያንን ይለጋ ይለጋ ና..” ጋሼ አሳዬ ኢንቅልፌ መጣ ይላል? የከተማ አባት ደክሞአቸው ሲያፋሽጋቸው አይቶ እንቅልፍህ መጣ ወይ ማለቱ ነው። እነ ከተማ ይሰቁበተና ያርሙታል። ጋሽ ከዲር እንቅልፍህ መጣ ወይ በል ይሉታል። ከዲር ዋቆ እጅግ ቆንጆ ከመሆኑም ሌላ ሽፍታ አይመስልም። የእስላም ኮፊይ ዓለው። ልብሱም ሆነ ገላው እጅግ ንፁህ ነው። ታዲያ ጎባ የመጣውና ከጃጋማ ለመገኛኘት ነበር። ጃጋማም መአት ጥይት፣ የጉያ ሽጉጥና አምስት መቶ ብር ቢሰጡትም አሁንም ያ የሽፍትነት ድንባሬው ስላለቀቀው በጣም ተጠራጣሪ ነው። አሳዬ ይህን አይተው ከተማን ከእርሳቸው ጋር ሳይሆን ከከዲር ጋር እንዲተኛ አደረጉ። ከተማም ደስ ብሎት እንቅልፍ እሲኪወስደው ድረስ አማርኛውን ያርመዋል። አንዴ ጋሽ ከዴር ከተማና እርሱ የሚተኙበት ሳሎን አጠገብ ያለውን ፋኖስ ለማጥፋጥ ሲመራመር ከተማ ዝም ብሎ እያየው ይሰቅበታል። ጋሽ ከዲር የፋኖሱን መስታወት ከፍኖሱ መቀመጫ የሚያላቅቀውን መያዣ ወደ ታች ጫን አድርጎ እሳቱን እፍ አድርጎ ከማጥፋት ይልቅ፤ የፋኖሱን ምላስ ከፍና ዝቅ ማደረጊያዋን መዘወሪያ ይዞ ወደ ግራ ሊዘውረው ሲል ከተማ ያስጥለውና እንዴት እንደሚጠፋ ያሳየዋል። ቶሌ ቶሌ አካሢ! ይልና በከተማ ሳቅ እርሱም አብሮ ከጠጁ ጋር ከት! ከት! ከት! ብሎ ይስቃል።  ጋሽ ከዲር አንድ ነገር ኮሽ! ካላ ብድግ ነው የሚለው። ጠመንጃው ጎርሶ አጠገቡ ነው ያለው። 

ወፏ

ከዲር ዋቆ ከገባ በኋላ አሁን የሚጠበቀው የእርሱ አለቃ ሐሰን ቱሬ እጁን በሰላም እንዲሰጥ ነው። ይሁን እንጂ ሐሰን ቱሬን ከሰው ምክር ይልቅ በዘልማድ ባገኘው በኸረና ወፍ ምክር ስለሚመራ ከዛሬ ነገ እገባላሁ እያለ አሳዬን ሃሳብ ላይ ጣላቸው። ሆኖም ጃጋማ ግድ የለም ምናልባት ከዲርን ያስሩታል ብሎ ስግቶ ነው አታስብ እያሉ በትግስት እንዲጠብቁ ይመክሯቸዋል። በመጨረሻ ከዲር ዋቆ በገባ በስድስተኛው ወር ሐሰን ቱሬም ደሎ መና ሄዶ ለሕዝብ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንደተመለስ ታየ። ይሁን እንጂ ወደ ጎባ መጥቶ ከጃጋማ ጋር ለመገኛኘት ዛሬ ነገ የወፉአን በጎ ምክር ሲጠባበቅ ጃጋማ ተቀይረው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። ጃጋማ አቶ አሳዬን ከዛሬ ነገ የደሎ አውራጃ ገዥ ያደርጓቸው ይሆናል የሚለውም ተሰፍ ሕልም ሆነ ቀረ። ጃጋማ የባሌን ዋና ከተማ ጎባን ወደ ርሳቸው አዲስ እርስት ጎሮ ለማዛወር አስበው ብዙ ተቃውሞ ገጠማቸው ነበርጎሮ የውሃ ችግር አለበት። ከመቀየራቸውም በፊት ከፍታውራሪ አሻጋሪ ላይ የገዙትን ኩታ ገጠም መሬት ለማየት በሄሊኪብተር ሲሄዱ አደጋ ስለደረስ ፍታራሪው ተቃጥለው ሲሞቱ ጃጋማ ቢተርፍም እጃቸውና ፊታቸው ክፍኛ ስለተቃጠለ ወደ አዲስ አበባ የመቀየራቸውን ምክንያት አጣደፈው።


አርባጉጉ

አቶ አሳዬ የኸረናን ሽፍቶች ካሰገቡ በኋላ ጃጋማ በድንገት ወደ አዲስ አበባ ስለተቀየሩ፤ ባደረጉት በጎ ስራ ከመደስት ይልቅ ቂም የነከሱባቸው አለቆቻቸው አያታቸውም ሆኑ ቅድመ-አያታቸው ተወልደው ካዳጉበት ባሌ ሊነቅሏቸው አሲረው በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት የአርባ ጉጉ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሰሩ የሚል የዱብ እዳ ሹመት ደረሳቸው። ሹመቱን አልቀበልም ብለው ለደጅ ጥናት ወደ አዲስ አበባ ወጡ። በዚያኑ ወቅት የአቶ አድነው ልጅ ብዙነህ የሳንባ ነቀርሳ ይዞት ደም ይተፍ ስለነበር፤ አድነው ወደ ሻሸመኔ ወስደው ለማሳከም ሲጥሩ የለም አዋቂ/ጠንቁዋይ  መጠየቅ ይሻላል ተብሎ፤ ከተማ አክስቱን ተከትሎ ወደ አዋቂ ቤት ሄደ። አዋቂውም ሻሸመኔ ይዞት እንዳይሄድ ብዙየም እንደሚድን ተናግረው አቶ አሳዬ ግን ወደ አርባጉጉ ቢሄድ ከአስም በሽታቸውም እንደሚዱንና አርባጉጉም ምድረ ገነትን የሚመስል አገር እንደሆነ ተናገሩ። ከተማም በነገሩ በጣም ተደንቆ አዋቂውን ደርግ እስካሰራቸውና እስከገደላቸው ድረስ በብዙየ ሞት ተጠያቂ ናቸው ብሎ ቂም ይዞባቸው ስለነበር ሲሞቱ እሰየው! ነው ያለው።
አሳዬ አዲስ አበባ ሁለት ወር ቆይተው በጃጋማ ጥረት በደሎ አውራጃ የአንጌቱ ወረዳ አስተዳዳሪነትን ተሾመው ወደ ትውልድ አገራቸው ባሌ መጡ።

የለውጥ ሃዋሪያት፤

አሳዬ አንጌቱን እንደተሾሙ፤ ድልድይና መንገድ በማሰራት ሕዝቡን ለልማት ማሳትፍ ጀመሩ። እንደውም አንዴ የተሰራውን ስራ በሬዲዮ እንዲነገር ልከው ድፍን ኢትዮጵያ ስምቶቷል። ይሁን እንጂ አንጌቱ ወበቃም ስለሆነ በአስም ይስቃያሉ። በተለይ አስሙ የሚብስባቸው ጠጅ ሲጠጡ ቢሆንም ማንም ደፍሮ ጠጁን እንዲተው የሚመክር ደግሞ የለም። ታዲያ የደርግ ሃዋርያትም ወደ አንጌቱ ዘልቀው በየመንገድ አገሬውን እያስቆሙ ስለ አስተዳዳሪው በሚያገኙት በጎ ምላሽ ...በአሳዬ የሕዝብ ተወዳጅነት ይገረማሉ። ታዲያ  በአስም በሽታ መስቃየታቸውን አይተው ሕክምና የተሻለበት ቦታ መመደብ ይገባቸዋል ብሎው ለአገር አስተዳደር ትእዛዝ በመስጠታቸው ካሳሁን ከአንጌቱ በጥሩ የደሞዝ እንደገት ወደ አዳባ ወረዳ አስተዳዳሪነት ተመደቡ። ይህ አጋጣሚም ከ 15 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልጆቻቸው እናት ጋር በአንድ ላይ ለመኖር ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረ። የከተማ አባት ጉቦ እምቢ ካሉ ጀምሮ ምቀኛ ስለበዛባቸው አንዴ የጎባ አውራጃ ሂሳብ ሹም ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ ገንዘብ አጉድለሃል ተብለው ለ 9ወራት ከሰራቸው ታግደው ነበር። ታዲያ የዚያን ጊዜ የባሌው እንደራሴ ወርቁ እንቆስላሴን ተከትለው ደጅ ጥናት ኤልከሬ ድረስ ሄደው ወደ ጎባ ሲመለሱ መኪናው ጭቃ ውስጥ ገብቶ ለማውጣት ጭቃውን በአካፋ እየዛቁ ሲጥሉ የጣታቸው ጥምዝ ወርቅ በልቶአቸው ደማቸው መፍሰሱን ሳያውቁ እየቆፈሩ እያሉ፤ ወርቁ እንቆስላሴ ያንን አይተው ከማዘን ፋንታ ...ባክህ ወዲያ ያንን ተቀበለው ደሙን አያዝራብን ብለው በመመፃደቃቸው አሳዬ እብሪቱ እያንገፈገፋቸው ሁሌ ለከተማ ይነግሩት ነበር። ሆኖም ወርቁ እንቆስላሴ በደርግ መገድላቸውን በሬድዮን ሲሰሙ..."እግዚአብሄር ይይለት ፈጃቸው" ነበር ያሉት።

ጊዜ ሲኖር ደግሞ  የደርጉን ዘመን ደግሞ መለስ ብለን እናየዋለን.....

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!