መለስ ብዬ ሳየው 3



አቶ አድነው ስለ ኸረና ዘመቻ የሚያወጉት ሞልቶአቸዋል። “ሽፍቶች ሸሽተው ወደ ኸረና ደን ውስጥ ስለገቡ የረባ ጦርነት አልገጠመንም። ይሁን እንጂ፤ ነጭ ለባሽ መዝናናት አብዝቶ ነበር። አንድ ቀን ፍታውራሪን አጅበን ለአሰሳ ፈት ፊት ሲሄድ ዛፍ ሲወዛወዝ አየሁ። ዝንጀሮ ነው! ጉሬዛ ነው! ቢሉኝም አላመንኩም። ፍታውራሪም ተው ዝንጀሮ ነው አሉኝ። የለም እምቢ ብዬ ተኩስ ከፈትኩ!” “ወዲያው ከሽፍቶች አንዴ እሩምታ! ታ!ታ! ድም! ድም! ድብልቅልቅ ያለ ውግያ ሆነ። አድፍጠው ሊጨርሱን ነበር!ተከታተልናቸው!የታባታቸው! አመለጡን”!  ፍታውራሪም በዚህ ተደስተው ነፍሴን ያተርፍካት አንተ ነህ እያሉ ስለሚያሞግሳቸው አቶ አድነው በንቁነታቸው ይኩራራሉ። አድነው የማር ነጋዴነታቸውን ትተው በሀረና ዘመቻ ባሳዩት ወታደራዊ ንቃት የወህኒ ቤት ዘበኛነት ተቀጥረው ደሞዝተኛ ሆኑ።

የንጉሱ ጉብኝትና የሰላም ጥሪ

ዋናው ሽፍታ ዋቆ ጉቱ እጃቸውን ቢሰጡምና የባሌም ሽፍትነት በመንግስት ጦር ቢፈታም፤ ኸረና የመሽጉት የዋጎ ጉቱ ቀኝ እጆች፤እነ ሐሰን ቱሬና ከዲር ዋቆና ሁሴን ዳዲና የመሣሰሉት አሁንም እጅ አልሰጡም። ኸረና ከጎባ በስተደቡብ የሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ደን ነው። በመሆኑም እዚያ ውስጥ ወታደርም ሆነ ነጭ ለባሽ መላክ ሰው ማስጨረስ ካልሆነ ትርፍ ስለሌለው የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ አገዛዝ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ወይም አካባቢውን በአውሮፕላን ለመደብደብ ወስኗል።


ገብሬ ሞረዱ

ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡጡ!ጡጡጡ

“ንጉስ ነገስትህ!ንጉስ ነገስትህ!
ኃይለ ስላሴ!ኃይለ ስላሴ!
ሊ ጎ በ ኙ ህ! ሊ ጎ በ ኙ ህ!
ይመጣሉና!ይመጣሉና!
ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡጡ!

ቀዬህን አፅዳ!
አጥርህን እጠር!  
በርህንም ቀለም ቀባ!
ብለውሃል!
ጡ!ጡጡ!ጡጡጡ!ጡጡ!ጡጡጡ

የገብሬ ሞረዱ ጡርንባ ብዙውን ጊዜ ሰው ሲሞት ለቀበር ጥሪ የሚደረግ ነው። የሚለው ነገር ግን ከሩቅ በደንብ ስለማይሰማ የየሰፈሩ ልጆች ሮጠው አጠገብ ይደርሱና ዜናውን አጣርተው ለወላጆቻው ያደርሳሉ። አንዳንድ ልጆች ግን ጡርንባውን እንዲያስነፈቸው ሲማፀኑት እሺ ስለማይል ያናድዳቸውና ካጠገቡ ራቅ ካሉ በኋላ ድንጋይ ይወረውሩበታል። አንዴ እንደውም ጉቱ የወረወረበት ድንጋይ ፈንክቶታል። ስለዚህ ልጆች ሲጠጉት፤

“ገብሬና ልጅ፤
ሩቅ ለሩቅ።
ሽፍሮ ሁሉ!
ራቅ በሉ! ይላል!”
የንጉሱን ጉብኝት ለማስተናገድ ሁሉም በየፊናው ሽር ጉድ ይዟል። የነከተማ ቤት መንገድ ላይና ከሰፈሩም ሁሉ ከሚሻሉት ቆርቆሮ ቤቶች አንዱ ነው። ግቢውም በጥሩ የሺቦ አጥር የታጠረ ነው።  የቤታቸውም የእንጨት መስኮቶችም ሆነ የዋናው መግቢያ በር በድጋሚ ውሃ ሰማያዊ ቀለም ጋሽ ጎይቶም ሶስት ብር ተከፍሎት አሳብዶ ቀብቶአቸዋል። ሌላው ሰፈር አረንጓዴ ቢጫና ቀይ የተቀባም አጥር ይታያል። ልጆች በየሰፈሩ የሚያዩትን የቅብ አይነት እያወዳደሩ፤
ይሄ ያምራል! ይህ አያምርም! እያሉ መሟገቻ አግኝተዋል።
ጎባ አውሮፕላን ማረፊያው እከተማው ማሕል ስለነበር ለንጉሱ አቀባበል፤ በአውሮፕላን ማረፊያው ሜዳ ግራና ቀኝ የሚገኙት ቡና በቶች፣ መኖሪያ ቤቶችና የጋሽ አደም ሻይ ቤት ሳይቀሩ ቀለም ተቀብተዋል። ጋሽ አደም እስላም ነው። የጎባ ልጅ ሆኖ የርሱን ፓስቲ/ማይጨው/ቆቀር ያልበላ የለም። ማይጨው ለመብላት ሲገባ ጋሽ አደም ከፕላስቲክ በተሰራ ጎድጓዳ ሳህን አራት ያቀርባል። በይው ከአራቱ ሁለቱን ከበድ ያሉትን ያነክትና፤ “ለውጥ ይላል!” ሌሎች ሁለት የተሻሉ ይቀርቡለታል። ከተለወጠው አንዱን ብቻ አሊያም ሁለቱንም በልቶ ከአንድ ሻይ ጋር ስሙኒ ከፍሎ፤ ግራና ቀኝ ስው አየኝ አላየኝ ብሎ ወልቅ ነው! ከሻይ ቤቱ። ወላጆች ልጆቻው ሻይ ቤት እንዳይለምዱ በጣም አድርገው ይቆጣጠራሉ። ጋሽ አደም ቤት ገብቶ በልቶ ሲወጣ የታየ፤ ገንዘቡን ከየት አባክ አመጣህ? እቤት የምትበላው አጥተህ ነው ያን ሞፎ የምትገምጠው?ተብሎ መገረፉ አይቀሬ ነው። ጎባ ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው የኪስ ገንዘብ አይታወቅም። ያው ለእንቁጣጣሽ አበባ ሲዞርና በሆያ ሆዬ ጊዜ የሚገኝ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ጊዜ በየሳምንቱ ብእሬ ጠፋ፣ ወይም ቀዘነ፣ እርሳሴ ተስነጠቀ በሚል ሰበባ ሰበብ ነው ለማይጮው መግዣ የሚገኘው።

አቀባበል

የንጉሱ አውሮፕላን ጎባ ከሚያርፉት የተለየ አይደለም። በሩ ገና ከፈት ሲል ሁለት ድንክዬ ውሾች ተከታትለው ወጡ። አንደኛዋ ንጉሱ ለሰራዊቱ ስላምታ እንዲሰጡበት ከተሰራው ደረጃ ላይ ብር ብላ ሄዳ ግራ ቀኝ ስታሽት ሌላኛዋ ደግም ለንጉሱ መቀበያ በተዘጋጀው አዳራሽ ውስጥ እየዘረች ምን እንደምትፈልግ አይታወቅም። ንጉሱ ከአውሮፕላን ብቅ አሉ!እልልታው፣ ሆታው ድብልቅልቅ ሆነ። ውሾቹ ግን ስራቸውን አልጨረሱም። ወደ አውሮፕላኑ አጠገብ ሄደውም የሚፈልጉት ያለ ነገር ይመስላል። ከሩቅ አንድ የጥቁር ቡራቡሬ የሰፈር ውሻ አይተው  ገና ቡፍ! ቡፍ! ማለት ሲጀምሩ ፖሊስ እየተንደረደረ የመንደሩን ውሻ ሲያባርረው ከተማ በአንድንቆት ከአክስቱ አጠገብ ሆኖ ያስተውላል። ንጉሱ ለተቀበላችው ሰው ንግግርም አላደረጉ። ለተሰላፊው ወታደር ሰላምታ ስጥተው የአቀባበሉ ስርአት ካላቀ በኋላ ላንድሮቨር መኪናቸው ውስጥ ገብተው ወደ እንደራሴው ግቢ መንቀሳቅስ ሲጀምሩ እንደገና እልልታው ቀለጠ። እንደ የከተማ አክስት የጋሽ አየለ ዋከኔ ሚስት ከሆነ፤ “የንጉሱ ፊት እንደ ፀሃይ ስለሚያበራ ደፍሮ ለማየት አይቻልም።” መኪናቸውም ነቅነቅ ሲል መሬቷም አብራ ቀጥ! ቀጥ! ቀጥ! ቀጥ ትላላች!
በማግስቱ ንጉሱ የፖሊስ መምሪያንና አንዳንድ ቦታዎችን ይጎበኛሉ። ከተማም በንጉሱ አቀባበል ሰበብ የተገዛለትን አዲስ ልብሱን ለብሶ ንጉስን ይከታተላል። ንጉሱ አንድ ቀይ ሰውዬ በሚነዱት ላንድሮቨር መኪና ጎን ተቀምጠው እጃቸውን ግራና ቀኝ በመኪና መንገዱ ዳርቻ ለቆመው ሕዝብ ያወዛውዛሉ። ግን ብዙዎቹ የማመልከቻ ወረቀታቸውን ይዘው ወደ ንጉስ መቀርብ ቢሞክሩም አልቻሉም። ማመልከቻቸውን ግን አንድ ፖሊስ ይቀባላል። የማመልከቻው ጉዳይ ግብር በዛብን ይማሩን ነው። እነ ከተማ የንጉሱን መኪና እየተከተሉ ፖሊስ መምሪያ ደረሱ።
እዛም በፖሊሶቹ የጁዶና የአክሮባት ችሎታ ከመደነቃቸውም በላይ ንጉሱን በቅርቡ የማየት እድል አጋጥሟቸው ነበር። ለእነ ከተማ እንደ ከተማ አክስት ሳይሆን ንጉሱ ፈታቸውም የሚታይና በጣም የከሱና አጭር ናቸው። የንጉሱን መኪናና ዱካ የሚከታተሉትን ልጆች ከንጉሱ ብር እንዲቀበሉ በሶስት ረድፍ መሰለፍ ጀምሩ። ከተማ ሁለተኛው ረድፍ ላይ ተስልፏል። በመጀመሪያው ረድፍ የተሰለፉት አንዳንድ ሽከካ ብራቸውን እንደተቀበሉ የንጉሱ መኪና መንቀሳቀስ ስለጀመረች ሁለተኛውና ሰሰተኛው ረድፎች ምንም ሳያገኙ ቀሩ። ጠጅ ነጋዴዋ የከተማ አባት ታናሽ እህት ወይዘሮ እጅጌ ይሄን ስምተው ለከተማ የዛን እለት ብርዝ ብቻ ሳይሆን ሁለት ብርም አሽከሙት። የ40 ማይጨው መብያ!

ንጉሱ ለባሌዎች ሹመት ሰጥተውና ግብርም ምረው ተመለሱ። ከዚህም ሌፍተናት ጀኔራል ጃካማ ኬሎን የባሌ እንደራሴ አድርገው ሾሙ። ጃጋማ ቀይና መልከ መልካም ናቸው።  ጃጋማ እጃቸውን ያልሰጡ ሽፍቶችን መጀመሪያ በዘዴ ለማስገባት ከጠቅላይ ግዛቱ የመንግስት ባላስልጣኖች ሁነኛ ሰው ሲያፈላልጉ ጊዜ ወሰደባቸው። ይህን ጉዳይ የደሎ አውራጃ ሂሳብ ሹም የከተማ አባት አቶ አሳዬ ይሰማሉ።  ኸረናም በደሎ አውራጃ ስር ነው። የደሎ አውራጃ ገዥ የአቶ ካሳሁን አለቃ ፍታውራሪ አለማየሁ ስው የማይወዳቸው ሆዳምና ጉበኛ ስለሆኑ መቼም በርሳቸው በኩል ሽምግልና የማይሞከር ጉዳይ ነው። አቶ አሳዬ ግን በረዢም ጊዜ የመንግስት ሰራተኛነታቸው በተለይ በደሎ አውራጃ ስራቸው በጉቦ ማንም ሰው አያማቸውም። እንደውም ቀጭንና ረዢም ስለሆኑ፤ ቋንጣ! አይበላ አያስበላ የሚል ስም ወጥቶላቸዋል። ለከተማ እንደነገሩት አባቱ ሰራ የተቀጠሩት በአስራ ስምንት አመታቸው በአምስት ብር ደመወዝ ከጎባ አሰላ በእግራቸው ፓስታ አመላላሽነት ነው።  ቀጥሎ የጊንር ግምጃ ቤት ሹም ሆነው ሲስሩ ደሞዛቸው ስለማይበቃቸው ትንሽ ጎቦ ይበሉ ነበር። ከዚያም በኋላ በእድገት ወደ ጎባ ተመልሰው ቀጥሎም በተሻለ እድገት ወደ ደሎ ከሄዱ በኋላ ደመወዛቸው በቂ ስለሆነ ለንስሃ አባታቸው ያለፈውን የጊንር ኋጢአታቸውን ነግረው ሁለተኛ የሰው ገንዘብ ላለመብላት ማሉ።
ታዲያ አቶ አሳዬ የአውራጃው ሰው እንደሚወዳቸው ያውቃሉና በራሳቸው አነሳሽነት ከሐሰን ቱሬ ጋር በሚስጥር መላላክ ያስቡና ተግባራዊ ያደርጉታል። ሐሰን ቱሬ ስለ አቶ አሳዬ ስመ ጥሩነት ቢሰማም ስለማይተዋወቁ ለሽምግልናው የሚያምናቸውን የጎባውን ነጋዴ አቶ ንጉሴ ገብረመድህንን መሆኑን  ያስታውቃቸል። ካሳሁንም ከአቶ ንጉሴ ጋር በጣም ወዳጅ ስለሆኑ ይህንን በሚስጠር ሐሰን ቱሬ ማጣራት እንደሚችል ስለ ገለጹለት የመጀመሪያ ጉንኙነት ለማድረግ ከፈለገ ከንጉሴ ጋር አሊያም ብቻቸውን እርሱ የመረጠበት ቦታ ለመገኘት ባቀረቡት ሃሳብ ስለተስማማ አሳዬ የፋሲካን ጦም ፍቺ ከልጆቼ ጋር ነው የማስልፈው በሚል ለጥርጣሬ የማይዳርግ ሰበብ ሰጥተው የአስራ ምስት ቀን ፋቃድ ወስደው ከሐስን ቱሬ መልክተኛ ጋር ወደ ኸረና ጫካ ዘልቀው ከቀንደኛው የባሌ አማጺ ጋር የመጀመሪያ ግኑኝነት ያደርጋሉ።

ይቀጥላል

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!