ግንባር? ውህደት? እየተስተዋለ!



       ግንባር? ውህደት? እየተስተዋለ!


                ‘ነጻነቴን ከኢሳያስ መንጋጋ አገኘዋለሁ ማለትህን ተወኝ!’

                        ቦጋለ ካሣዬ (አምስተርዳም ኦገስት)

በኢሳያስ አፈወርቂ ‘እየተደገፉ’፤ ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ የትጥቅ ትግል እናካሄዳለን የሚሉ ሶስት ድርጅቶች አንድ ግንባር ለመፍጠርና ወደፊትም ለመዋሃድ መስማማታቸውን በቅርቡ የግንቦት-7ቱ ኢሳት በሰበር ዜናው ነግሮናል። የዲያስጶራውም ሰሞነኛ መነጋገሪያ ነጥብ ሁኖአል። ከዜናው ትንሽ ቀደም ብሎ የኢሳቱ ዋና ሰው ፋሲል የኔአለም፤ የወያኔ መውደቂያው ዶርሶአል ሲል ተቁነጥንጦ በፊስቡኩ ላይ የለጠፈው የመልካም ምኞት ብስራት፤ ፍጥምጥሙ ያለቀ ጉዳይ መሆኑን ያመላክታል።

ዜናው ወያኔ በማንኛቸውም መንገድ ተወግዶ ለማየት ለሚሹ ገራገር ኢትዮጵያውያን ክፋት ያለው አይደለም። ሌላም ሰው ቢሆን ጭቆና ባለበት የትጥቅ ትግልን ማስቆም እንደማይቻል ስለሚገነዘብ፤ ተዋጊዎቹ ግንባር መፍጠራቸውን ክፉ ነገር ነው! ብሎ ቢያንባርቅ የፖለቲካ ሀሁ ያልገባው ቂላቂል ተብሎ ሊቆጠር እንደሚችል አይስተውም። ለነገሩ ጠላት አይናቅምና፤ ግንባሩን እንደ ክፉ ነገር ሊያይ የሚገባው ወያኔ ይሆን እንዴ?

‘ናይ ፖለቲካ ናጽነት አይኮነን ሆድ ናጽነት !’

በቅርቡ ወያኔ መጪውን ምርጫ ተከትሎ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በፓሮፓጋንዳ ለመጠዝጠዝ፤ በመቀሌ ባካሄደው ስብሰባ፤ የባሕረ ነጋሽና የእርሱ ጦርነት ዋናው መንስኤ በዶላር እንጂ በናቅፋ መገበያየት፤ አለብን! የለም! የለብንም! በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ እንደሆነ ከረዢም ዓመታት በፊት የምናውቀውን ሃቅ መልሶ አረጋግጦልናል።
ሃቁም በባህረነጋሽ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እድገት የታየው ከኢትዮጵያ ጋር በፌዲሬሺን በተዳደረችበት ወቅት ብቻ መሆኑን ነው። በኢታሊያና በእንግሊዝ ኮሎኒያል አስተዳደሮች ስሙዋም(የምጠየፈው ኤርትራ) ሆነ ኢኮኖሚያዋ ኮሎኒሊይስቶችን እንዲጠቅም ሆኖ የተመረዘና የተዋቀረ ስለነበሩ በባርነት ይተዳደር ለነበረው ብዙሃን ከዘረኝነትና ከውርደት በስተቀር ምንም ጠብ ያለለት ነገር አልነበረም። ፌዴሬሽኑ እንደተሳካ፤ ከተሜ ቀመስ መረብምላሴዎች ከኢታሊያ በልምድ በገበዩት የእጅ ሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፤ መኪና በመጠገን፣ቀለም በመቀባት፣ባንቡዋ በመዘርጋትና በመሳሰሉት እጅግ ለመክበር በቅተው ነበር። ይሁን እንጂ ይኼን ሙያ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በልምድና በተጨማሪም ከቴክኒካል ኮሎጆች እየተመረቁ የሚወጡት ገበያቸውን መሻማት በመጀመራቸው ብቻቸውን መብላት የለመዱት ብዙ መረብ ምላሴዎች ማኩረፍ ጀመሩ። የጀበሃና የሻእቢያም የጥትቅ ትግሎች ይኼን በሥስት ወይም በቅንቅን ለተከፋው ሆዳቸው ምሽግ መሆን ቻሉ። ስለዚህ ድሮም ቢሆን የመረብምላሴዎች ከተሜ ቀመስና አስኮላ ቀመስ  አንዱ ችግር የሥስት ነበር። ዛሬም የፖለቲካ ነጻነታችንን ተቀዳጀን ብለው በሆዳቸው ግን ነጻ አንወጣም በሚል የሚፈጥሩት ሁከት መፍትሄ አላገኘም። እንደውም አሁን ለኢትዮጵያ ትልቅ የህላዌ አደጋ ሆነዋል።
ዘካርያስ በአዲሳባ የጭነት መኪናዎችና ጋራዥ የነበራቸው ሃብታም ነበሩ። ልጆቻቸውንም ውጭ አገር አስተምረዋል። የሻአቢያንም ትግል ደግፈው ለናጻነት ድምጽ ሰጥተዋል። ታዲያ ከጦርነቱ በፊት ሲባረሩ፤ መባረራቸው እንደ ሕልም ነበር የሆነባቸው። መቆዘም… መቆዘም… ነበር ውሎአቸውና አዳራቸው።
ለፍቶ ያገኘ ሰው በፖለቲካ ትእዛዝ በአንዴ ሙልጩን ሲቀር ቢያዝን ምን ይደንቃል? ዘካርያስ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “ከእንግዲህ ‘አማራን’ ዙፋን ላይ መልሰህ ሆድህን አርፈህ መሙላት ነው የሚሻለው”። ከባድና የሚያም ትምህርት!
ዛሬ ባህረነጋሽ የልምላሜዋ መሰረት በሰው ሰራሽ አጥር ስለታጠረ መረብ-ምላሴዎች ለአስከፊ ድህነት ተዳርገዋል። ብልጦቹ ኢትዮጵያ ያሉት ግን ዛሬም ጥሩ ኑሮ ይኖራሉ። እንደውም አብዛኞቹ ገዢዎች ናቸው። አብዛኛው መናጢ የመረብ ምላሴ ድሃ በደርግ ጊዜ ቢያንስ ጤፍና የቤት ኪራይ እንደዛሬው አልቀመስ ያሉ ነገሮች እንዳልነበሩ በግልጽ መናገር ከጀመረ ውሎ አድሮአል። ከውጭ አገር የሚገባው የመረብ-ምላሴዎች ድጋፍ ባይኖር ኖሮ፤ ብዙ ሕዝብ በረሃብ ሊያልቅ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ዛሬም ቢያንስ በቀን 70 የሚሆኑ መረብምላሴዎች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። አሁንም ስደት፣ድህነትና እርዛት ከነጻናት በሁዋላ እንደቀጠሉ ነው። አዎ ኩራት አንድ ነገር ነው። ግን ብቻውን ራት አይሆንም።

እንግዲህ ባህረነጋሽ በፖለቲካ ነጻነቴ እንጂ፤ በሆዴ ከኢትዮጵያ አልገነጠልም የማለቱዋ አባዜ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ትልቁ ጠብ ነው። ይህ ድርቅናዋ በጦርነት እውን ሊሆን እንደማይችል ሲገባት፤ የወያኔ ኢትዮጵያን በተለያዩ መንገዶች መፈታተኑዋን አልተወችም። አንደኛው ጥረትዋ የጦርነቱ መንሲኤው የድንበር ብቻ አድርጎ በመቁጠር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ሕዝብረተሰብ እንድትገለል የማድረግ ዘመቻ ነው። ይኼ አልሰራም። ሌላው ደግሞ የተባረሩትንም ሆነ ቀደም ሲል በስደት ነዋሪ የሆኑ መረብ-ምላሴዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲወስዱና ለሻእቢያ አምስተኛ ረድፍ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
ሶስተኛው ደፋ ቀናዋ ደግሞ የወያኔ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉትን ማስታጠቅና ወያኔን ለማስወገድ ወይም አዳክሞ፤ የራስዋን ፍላጎት አሜን ብሎ የሚቀበል አገዛዝ በአዲስ አባባ ማቆም ነው።

ግንባር ይሁን ውህደት ዛሬ ለምን አስፈለገ?

የጥያቄውን መልስ ለማግኘት ከምናደርገው ጥረት በፊት፤ ስለ ሶስቱ ድርጅቶች ጥቂት መነካካቱ ክፍት የለውም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር(ኢሕአግ)፤

ይህ ግንባር ለወያኔ አስጊ ጦር ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ሻእቢያ በኢትዮጵያ ተቀጣጥሎ የነበረው የቅንጅት መንፈስ ስላስደነገጠውና የግንባሩም የልብ ትርታ መሆኑን ስለሚያውቅ፤ ይህቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም እንዲሉ፤ መሪዎቹን በማሰርና በመግደል ስላዳከመው ዛሬ በስም እንጂ ያለው አመራሩም ሆነ አጠቃላይ ጥንካሬው ብዙ ትችት የሚሰነዘርበት ድርጅት ነው። በእምነት(የብእር ስም) አንዱ የግምባሩ መስራችና ተዋጊ አሁን አውሮፓ ይኖራል። እንደ እርሱ ከሆነ ኢሕአግ ከወያኔ ወታደር የሚማርከውን የጦር መሳሪያ እንኩዋን የመጠቀም መብት የለውም። ሻእቢያ ኢሕአግ ከወያኔ የበለጠ ይሁን የሚስተካከል መሳሪያ እንዲታጠቅ አይፈቅድም። በዚህ የተነሳ አርበኛው ይመኝ የነበረው እንደምንም ብሎ በሰሜን ኢትዮጵያ መሰረት መጣል፣ በሱዳን በኩል ለመዋጋት መሞክርና ካልሆነም ስደት ነበሩ። 
የኢሕአጉ መሪ ኮ/ሌ ታደሰ ሙሉነህ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይዞ የመጣውን ሁለት የጦር ሜዳ መነጽር እንኩዋን ሳይቀር ሻእቢያ ተረክቦ ካዝናው ውስጥ ቆልፎበታል። ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የኤርትራን አየር ሃይል ያሰለጠነና ለኤርትራ ውለታ የዋለ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ይሙት ይኑር አይታወቅም። የዛሬን አያድርገውና፤ አንዳርጋቸው ጽጌ(ወይኔ ያጀገነው…ለልጆቹ ያብቃው) ኮሌኔሉ የታሰረው ኤርትራውያን ጋር በማሴር ኢሳያሳን ለመጣል ሞክሮ ስለተደረሰበት ነው የሚል የሻእቢያን ተረት! ተረት! እንደ ገደል ማሚቱ በማስተጋባት ጭቡ ይሰራና ይሳለቅ ነበር።

ደግሞ የዚሁ ኢሕአግ ድርጅቱ መሪ ነኝ የሚል መሰከረም አታላይ በጀርመን ጉድ ስርቶአል። በቅርቡ “ስደት የፈታው ቤት” በሚል አስፍው ከበደ በጻፉት መጽሃፍ ውስጥ፤ ለአርበኞች ተብሎ በጀርመን የተዋጣውን ገንዘብ፤ መስከረም አታላይ(በመጻህፉ ውስጥ ስሙን አያነሳም) «በአስቸኩይ ለቁስለኞች እንዲደርስ» በሚል ተቀብሎ እዛው ጀርመን ስደተኝነት ጠይቆ፤ የግል ንግዱን ለማካሄድ እንደተጠቀመበት ጠቅሶታል። 
ለነገሩ ቀደም ሲል ኢሕአግ ከግንቦት-7 ጋር መስራት ጀምሮም ነበር። ኢሳትም ግንባሩ የሚያወጣቸውን የወታደራዊ መገልጫዎች ያነብ ነበር። ይሁን እንጂ ግንባሩ ‘በግንቦት-7 እንዳንዋጥ እንሰጋለን’ እያለ ስላስቸገረ፤ የግንቦት-7ቱ አለቃ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ኢሳት ሁለተኛ የወታደራዊ ድሎቹን እንዳያነብና፤ እንደውም የሚነበበው ውሸት እየተፈበረከ መሆኑን የሃሰት ፕሮፓጋንዳውን ስራ ብርሃኑ ራሱ ሲያጋልጥ፤ ከሻእቢያ ጋር በምንም መንገድ መስራት የለብንም ብለው  ግንቦት-7ዴን የመሰረቱት አባላት ሚስጥሩን  ለሕዝብ አጋልጠዋል። እዚህ ላይ ብርሃኑ ነጋ የፈቀደው ውሸት እዲቆም ትእዛዝ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን መጤን ያለበት፤ ኢሕአግም ጥንካሬ የሌለው ድርጅት እንደሆነ የብርሃኑ ትእዛዝ በራሱ ከላይ የጠቃቀስናቸውን መረጃዎች ማጠናከሩም ነው። ለመሆኑ ዛሬ ልዋሃድ ነው የሚለው ግንባር ለምን ትናንት በግንቦት-7 ለመዋጥ ፈራ? ይኼ በድርጅቶች መካከል እምነት እንዳይኖር ሻእቢያ ሆን ብሎ ከመጀመሪያው የሚፈጥረው ሰበብ አይደለምን?
ኢሕአግ ብዙ የወታደራዊ ኮሚኒኬዎች በማውጣት መግደሉንና መማረኩን ቢነግረንም እስካሁን በከፋኝ ተጀምሮ የቀጠለው  የ20 ዓመታት የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ተራራ እንኩዋን አስለቅቆ መስረት ለመያዝ አላስቻለም።

የግንቦት-7 የፍትህና የዴሞክራሲ ንቅናቄ፤

አራት ዙር ተዋጊ አሰልጥኛለሁ ብሎናል። ምንም እንኩዋን በአንዳርጋቸው መታሰር የተደናገጠው ብርሃኑ ነጋ ከእንግዲህ ወዲህ ‘እየገደልን እንሞታለን’ ቢልም በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወያኔን የሚያሰጋ ጦር አላደራጀም ተብሎ የሚመራው ድርጅቱ ሊወቀስ አይገባም የሚሉ አሉ። የሆኖ ሆኖ ግንቦት-7 በሜዴያው ስርጭት በኩል የወያኔ ውጋት መሆኑና ለኢትዮጵያም ሕዝብ አማራጭ ሚዲያ እንዲፈጠር ማድረጉ ቀላል ነገር አይደለም። ጣሂር የሚባል ግለሰብ እንደገለጸው፤ ዛሬ ግንቦት-7 ያለው 5 የሰለጠኑ ታጋዮች ብቻ ነው።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ኃይል(አዴንኃ)፤

ይኼ ድርጅት አማራ የሚደርሰበትን በእቅድ የሚከናወን መፈናቀል፣ የዘር ምከናና ሌሎች ጥቃቶች ለማስቆም የተደራጀሁ ነኝ ይላል። በተለይ በኢፋ መንቀሳቀስ የጀመረው ከጉራፈርዳ ወገኖቻችን ውጡ የተባሉ ጊዜ መሆኑን ዳዊት የሚባለው የድርጅቱ የፖለቲካ ክፍል አመራር አባል፤ በግንቦት-7 ደጋፊ ፓልቶክ ሩም(Ethiopian Free Discussion Forum) ካደረገው ቃለ ምልልስ ሰምተናል። እንደ ዳዊት ከሆነ ድርጅቱ በኢትዮጵያ መዋቅር ዘርግቶአል። መስራች አባላቱ የወያኔ ሰራዊት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ መኮንኖች ናቸው። ከሁሉም ድርጅቶች ጋር ለመስራትም ፈቃደኛ ነው። በተለይ በአፋር ሕዝብና በአማራው ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እየተሰነዘረ እንዳለ ዳዊት አስረድቶአል። ዳዊት የመላው ኢትዮጵያ ልጆችን እርዳታ ጠይቆ በተለይ ወደ ድርጅቱ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርጉዋል። እንግዲህ ይኸም ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ መዋቅር ሊኖረው ይችላል ብለን ብንገምት እንኩዋን፤ ገና ብዙ ተዋጊ ያለው ጦር ሊሆን አይችልም።
እንደ ጣሄሮ መረጃ ከሆነ ደግሞ ፤ ይኽ ድርጅት የተቁዋቁመው ልክ ዳዊት እንዳለው ሁሉ የዛሬ አራት አመት ነው። «የድርጅቱ ሊቀመነበር ኮ/ል አለበል የተስፋዬ ገብረአብ ወዳጅና መጽሃፉንም ሲጽፍ መረጃ በማቀበል የረዳው ነው። በዚህ መሰረት አለበል ወደ ሻእቢያ ሲገባ ግንቦት 20/2010 ቀን አዴንኃ እንዲመሰርት በኢስያስ ይታዘዛል። 16 አባላትም ነበሩት። 6ስቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሲሄዱ ሶስቱ በወያኔ ተይዘዋል፤ ሶስቱ ደግም ተበታትነዋል። ኮ/ል አለበል አሁን ስራ የለውም።»  በተጨማሪም በቅርቡ እንደተረጋገጠው ኮሌኔሉ የሚገኘው በስደት አውሮፓ ነው።

ቀደም ሲል የአርበኞች ግንባርና ግንቦት-7 ጤናማ ግንኙነት እንዳልነበራቸው አይተናል። ግንቦት-7 ከአዴንኃስ ጋር ጤናማ ግንኑነት ነበረው እንዴ? እንደ የውስጥ አዋቂዎች ከሆነ ግንቦት-7 ነገር ሳይገባው ይመስላል፤ አዴንኃን በስሩ ለማስገባት ሞክሮ አልተሳካለትም። ይኽም በመሆኑ፤ ምንም እንኩዋን እርሱን በቀጥታ ባይመለከትም፤ ደጋፊው ፓልቶክ ሩም (Ethiopian Free Discussion Forum ) ከአዴንኃኑ ዳዊት ጋር ቃለምልልስ ባደረገበት ቀን(የዛሬ ወር አካባቢ)፤ ድርጅቱን የጎሳ ድርጅትና መሪውንም ደግሞ የወያኔ አጋዚ ጦር አዛዥ አድርጎ የማጥላላት ዘመቻ ያጡዋጡዝ ነበር። ዳዊትን ይኸንኑ አታካች ተመሳሳይ ጥያቄ አምስት ጊዜ ሆን ብለው ጀሌዎቹ ጠይቀውታል። ይኼ የግንቦት-7 ጀሌዎች ሽፍጥ ከቅንጅት መፍረስ ጀምሮ ያየነው የማይድን የምቀኝነት በሽታ ባለበት ነው እንግዲህ ውህደት ደግሞ የተደረገው።

ግንቦት-7

1. ግንቦት-7 ችኩልና የትም ፍጬው ዱቄቱን አምጪው በሚል ፍልስፍና የሚመራ ድርጅት ነው። 500 ዶላር መሰብሰብ ላይ እያለ፤ በአቁዋራጭ(በግልበጣ) ስልጣን ለመያዝ ተቻኩሎ ነበር። ይኼ ጉዳይ ወደፊት የጠለቀ ምርምር ቢያስፈልገውም፤ ወያኔ በተለይ በጦሩ ውስጥ ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ ብሎ የሚፈራቸውን መኮንኖች እንዲያስወግድ ምክንያት የሆነ ነገር እንደሆነ መረሳት የሌለበት ነው።

2. የግንቦት-7 ስዎች በስደት ከኦነግ፣ ከኦብነግና ከመሰሎቹ ጋር በመወገን የአንድነቱን ኃይልና ቅንጅትን እንደከፋፈሉት ሁሉ፤ ዛሬ ውህደቱ እውነት እንኩዋን ቢሆን ወደዛው እጥፍ-ልጥፋ አባዜአቸው እንዳሄዱ የቱ ልጉዋም ተበጅቱዋል? ወይስ ራሳቸው አደብ ገዝተዋል?

3. እንግዲህ ግንባር ከተፈጠረ፤ የትግሉ ባሕሪ የአካልና የአእምሮ ጥንካሬን ስለሚጠይቅ፤ ተክለሰውነት በምላስ የገነቡትና 100 ሜትር በአስር ደቂቃ ሮጠው ለመጨረስ የማይችሉት እነ ብርሃኑ ነጋ ከአመራር ራሳችውን ገሽሽ ያደርጉ ይሆን? ብርሃኑ ራሱንም ሆነ ሌሎችን በስሜት የመንዳት የ5ኛ መንጃ ፈቃድ ቢኖረውም እነሆ ግንቦት-7ን ፈቀቅ አላደረገም። ታዲያ ግንባሩ የወንድ በር ለማዘጋጀት የተፈጠረ ነውን? ወደ ጡረታ? አይደረግም አይባልም።

4. ግንቦት-7 ሜዴያውን ከማንም በተሻለ ይሰራል። ስለዚህ ከዚህ በሁዋላ ለኢሳት የሚዋጣ ገንዘብ የሚባል ነገር ቆሞ፤ ለግንባሩ ይዋጣ ሊባል ይሆን? ግንቦት-7 ግንባር ፈጠርኩ እያለ ቀደም ብሎ ደግሞ በየቦታው ስብሰባ ጠርቶአል። ይኼ የገንዘብ አሰባሰብ ሻሞ አይደለም እንዴ?  ግንቦት-7 ስብሰባ ለመሄድ ያሰባችሁም፤ ጥሪው ማስተካከያ ካልተደረገበት ባትሄዱ ይሻላል። ስንቴ ተመሳሳይና አሰልቺ ዲስኩር ትጋታላችሁ? በተለይ አቶ ቸኮል ተናጋሪ የሆነበት ስብሰባ የሚሄድ በሙሉ ህዝብ በጅምላ(አማራ) ሲሰደብ አንጅቱ ቅቤ የሚጠጣ እንደሆነ ልታውቁት ይገባል።

5. ሌላው የግንባሩ ፋይዳ ለግንቦት-7 ምንድነው? አንዱ ጎልቶ የወጣው ፋይዳ፤ አንዳርጋቸውን ለማስለቀቅ አንድ እርምጃ የማይወስድ ድርጅት ባይኖር ይሻላል! ከሚል የፖለቲካ ጥፊ ለማገገምም፤ ግንባር መመስረቱ ትግሉን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ አድርገናል! ብሎ ፍታ! ስጡኝ ለማለት ጥሩ መደበቂያና መከራከሪያ መሆኑ ነው።

የግንባሩ ፋይዳስ ለኢሳያስ?

ኢሳያስ ኢትዮጵያን ከልባቸው የሚፈልጉ ወገኖችን ሲያናክስ፣ ሲገልና ሲገርፍ ስንብቶ፤ በተቃራኒው አራት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ10ሺህ በላይ የትግሬ ተዋጊ አሰልጥኖ ደምሄትን አስናድቱዋል። ለምን ታዲያ ደምሄት አንዳንድ የዘረፋ ስራ ከመስራት ውጭና፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ በሚለው አልቃሻ፣ የለበጣና የቀጣፊ ድርሰት መዝሙር ከመለማመድ በስተቀር ሲያዋጋው አይታይም? ከ10ሺህ በላይ የትግሬ ተዋጊ ከአዘጋጀ በሁዋላ፤ ለምን ከወያኔ ጋር ጦርነት እንደመጀመር፤ ኢትዮጵያ እንድትኖርላቸው ቢያንስ አቅም ቢያጡም ከልባቸው የሚሹ ወገኖች ግንባር እንዲፈጥሩ ይፈቅዳል? ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል።  

ኢሳያስ ደምሄትን ሲያደራጅ፤ የፋይዳውን ውስንነትና የተገነዘበ አይመስልም። ለማንም ቢሆን ደግሞ የዛሬ አምስት አመት ሊሆን የሚችለውን ቀድሞ ማየት ቀላል አይደለም። ዛሬ የኤርትራም ህላዌ በድህነት ሳቢያም ሆነ ከዓለም ህብረሰስብ በመገለልዋ እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶአል። ለነዚህ ተያያዥ ችግሮች ኢሳያስ መፍትሄ መፈለግ አለበት።

አንዱ የደምሂት ውስንነት እንደ ወያኔ ሁሉ የአንድ ጎሳ ጦር መሆኑ ነው። ወያኔ ደግሞ ስልጣን ይዞ በኢትዮጵያ የረጨው የትግሬ ዘረኝነትን መርዝ መላው ኢትዮጵያን ያንገፈገፈና የበረዘ ነው።
በዚህም መሰረት ምናልባት በትግራይ ካልሆነ በስተቀር፤ ከዚህ ቀደም ለወያኔ እንዳደረገው የትግሬውን ጦር ደምሄትን አልጋ በአልጋ የጎንደር፣ የወሎ፣ የጎጃምና የሸዋ  ገበሬ አዲስ አበባ ያስገባዋል ብሎ መገመት ቂልነትም አደጋም አለው። መርዝ ካለው ይሰጠው እንደሆን እንጂ፤ በምንም መዝሙር ይሁን መፈክር ቢታጀብ ሕዝቡ ዳግመኛ የትግሬን የተደራጀ ዘረኝነት የሚሸከምበት ትከሻ አለው ብሎ መድፈር ጀብደኝነት ነው።

ደምሄት ልክ እንደ የወያኔ ትግሬ ጦር ተመሳሳይ የድርጅት ችግርም አለበት። በቅርቡ ለምሳሌ ከ30 የሚበልጡ ትግርኛ ተናጋሪዎች በወያኔ ጦር ውስጥ ተሰግስገው ለኤርትራ ሲስልሉ ስለተደረሰባቸው ብዙዎቹ ሳይያዙ አምልጠዋል። ወያኔም በደምሄት ውስጥ ስርጎ ለመግባት የቁዋንቁዋም ሆነ ሌላ የረባ የባህል ልዩነት ሆነ እምነት ስለማያግደው ከዚህ አንጻርም የደምሄት ጠቀሜታ ትግራይን ለመዝረፍ እንኩዋን አስተማማኝ አይደለም። ሌላም መጨመር ይቻላል። ኢሳያስ እስካሁን ደምሄትን ሳያዋጋ የቀረበት ምክንያትም ወያኔን ስለፈራ ነው ማለት ይቻላል። 10ሺህ ጦር በወያኔ ላይ ማስመራት ሺጀምር፤ ወያኔ ተወረርኩ! ብሎ ኤርትራን ሊወር ይገደዳል። ይኼም የኢሳያስን ከፖለቲካው ዓለም ተዋርዶ መወገድን ሊያስከትል ይችላል።

በነገራችን ላይ ደምሄት በሰነልቦና ይሁን በድርጅት ወያኔም/ሻእቢያም ስለመሆኑ ከዚህ ቪዲዮ መረዳት ይጠቅማል። https://www.youtube.com/watch?v=0JDQBET7zZQ

ስለዚህ ኢስያስ ባህረ ነጋሽ የቀረባትን የኢትዮጵያ ገበያ በስነስርአት ለመጠቀም ከፈለገ ኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ሁና ለማየት የሚፈልጉትን ተቃዋሚዎች ለማጠናከር መፈለጉ ሊገርመን አይገባም ። ከዚህ አኩዋያ ካየነው ኢሳያስ አሁን የፈቀደው ግምባር ምስረታ ይሁን የወደፊት ውሕደት የባህረ ነጋሽን ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው።
ይኽን የኢሳያስ አቅጣጫ ተአማኒነት የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ነገሮች ግን ማየት አለብን።
አንደኛው፤ በጎሳ ተደራጅተው የመገንጠል አጀንዳ የማያራምዱትም ድርጅቶች በውህደቱ እንዲሳተፉ ማድረግ አለበት። በተለይ ጂኔራል ከማል ገልቹ ኦነግ የሚለውን ጭንብል አውልቆ የግንባሩም ሆነ የውህደቱ አካል እንዲሆን መደረግ አለበት። ጄኔራል ከማል ኦሮሞ ግንድ ስለሆነ አይገነጠልም በማለቱ በኢሳያስ ጥርስ ውስጥ የገባ እንደሆነ የምናውቀው ጉዳይ ነው።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መገንጠልን የሚደግፉትን፤ የዳውድ ኢብሳን ኦነግና ኦብነግን እንዲሁም ተስፋዬ ገብረ እባብን ኢሳያስ ከባህረ ነጋሽ ቢያባርር ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አመኔታ ሊያተርፍ ይችላል። ለሁሉም የሚበጅም ጊዜ እንዲመጣ ጥሩ ጥርጊያ መንገድ ይጥላል። ኢስያስ እንዲህ የጠራና ለበጣ የሌለው እርምጃ ከወሰደ የወያኔን የስልጣን እንድሜም ሆነ ትእቢት በአጭር ጊዜ እንደሚለወጥ ማንም አይጠራጠርም። ኢስያስ እንዲህ ያለ ቆራጥ እርምጃ ካልወሰደ ግን ዛሬ ተፈጠረ የተባለውን ግንባርም ሆነ የወደፊቱን ውሕደት፤ ቢያንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ስር ስዶ መንቀሳቀስ እስከጀመረ ድረስ  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቀልድም በጎሪጥም ማየቱን እንደሚቀጥል ሊያውቀው ይገባል። ኢስያስ ኢትዮጵያን እንበትናለን የሚሉትን መርዳት ከቀጠለ፤ የሚገነጠሉት አገሮች ሃብት ለራሳቸውም ስለማይበቃ፤ ልክ ወያኔ እንዳደረገው ከመረብ-ምላሽ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተው  ለመዋጋት እንደሚገደዱም ማወቅ አለበት።
በመጨረሻም የረባ የትጥቅ ትግል ተመክሮና ኢትዮጵያ ውስጥ ድርጅታዊ መዋቅር በእውነት ተዘርግቶ ቢሆን ኖሮ ከግንቦት-7 የኢሳት የፕሮፓጋንዳ ስራ ጋር በግንባር ይሁን በውህደት አንድ ሆኖ መታገል ጠቀሜታው ሳይታለም የተፈታ ነው ማለት ይቻል ነበር። ታዲያ የወያኔ ቤት ምን ያኸል ተሸብሮ አድሮ ይሆን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ለተፈጠረ ግንባር?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!! ምንይልክ ይኽን ጉድህን ቢሰሙ፤ “ነጻነቴን ከኢስያስ መንጋጋ አገኘዋለሁ ማለትህን ተወኝ!” ይሉህ ነበር። ለራስህ እወቅበት።

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!