እኛ ተማሪ እያለን.... ሕንድ በዛ!



                    እኛ ተማሪዎች እያለን፤ ሕንድ በዛ!
.. 1964 ነው። ባሌ ጎባ ነው አገሩ። ትምህርት ቤቱም አዝማች ደግለሃን ይባል ነበር። 7 እሰከ 12 ክፍል የሚከታተሉ ተማሪዎችን የሚያስተናግደበት፤ ከድንጋይና ከእንጨት የተሰሩ ክፍሎችም ነበሩት። ተራራ ብቻውን ታሪክ የሚሰራ ይመስል፤ ታሪካዊ ስሙ በደንቆሮው ደርግ ጊዜ ተፍቆ ባቱ ተራራ ተብሎአል።
ታዲያ በዳግልሃን /ቤት ውስጥ ሕንዶች በዙ! ተባለ። አሁን ልብ ብዬ ሳየው፤ሕንዶችእንላቸው የነበረው፤ ፊሊፒኖችንም ጭምር ነው። አንድ ሕንድ ወይም ፊሊፒኖ አስተማሪ በአንዴ ሂሳብ፣ጆግራፊ ወይም ታሪክ እንዲያስተምር ይመደባል። እንግሊዠኛና ሂሳብ የሚያስተምሩም ነበሩ። አንዳንዶቹ አስተማሪዎች በቂ ዝግጅት ስላልነበራቸው ሽምድደው የመጡት ነገር ጥያቄና መልስ ከጎበዝ ተማሪዎች ሲያስነሳ ብስጭት ውስጥ ይገባሉ። ወይም በነገ ይደር እየተባለ ጥያቄዎች ሳይመለሱ እንዲረሳሳ ያደርጋሉ። እኛ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ነበርን። ከኢትዮጵያውያን በስተቀር አንድም የውጭ አገር ዜጋ እኛን እንዲያስተምር አልተመደበም። ታዲያ ከላይ የሆነውን ያወጋዋችሁ፤ ሕንዶች በዙ! ጥሩ አስተማሪዎች ስላይደሉ፤ እነርሱ ሊያስተምሩን አይገባም። ሌላ ጥሩ አስተማሪዎች ይመደቡልን፤ እያሉ የዳግለሃን የተማሪዎች ካውንስል ከተማሪዎች ጋር ምን ማድረግ አለብን ብለው ሜዳ ላይ ይወያይበት በነበረበት ጊዜ የማስታውስውን ነው።
ተማሪዎቹ በካውንስሎቻቸው አማካኝነት አቤቱታቸውን ለጋሼ ይትባረክ ያቀርባሉ። ጋሼ ይትባረክ በጣም ተወዳጅ ዳሬክተር ነበር። ከት/ቤቶች ስራ አስኪያጅ ግራዝማች ካሳዬ(የኔ አባት አይደሉም) ጋር አይንና ናጫ ነበሩ። የኔ አባትና ጋሼ ይትባረክ ወዳጅ ናቸው። ጋሼ ይትባረክ ለግራዝማቹ የሚጽፈውን ደብዳቤ ለአባቴ ኮፒ ስለሚያደርገው ይኼን ደብዳቤ አንብብልኝ ይለኝ ነበር። አባቴ መጻፍና ማንበብ በደንብ የሚያውቅ የመንግስት ሰራተኛ ነው። እንደሚመስለኝ ማንበብ መቻሌን ለመፈተን ይመስለኝል አንብብልኝ የሚለኝ። አንዱ ትዝ የሚለኝ ደብዳቤው፤ በባሌ 8ተኛ ክፍል በላይ ተማሪ ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚችል /ቤት ዳግለሃን ብቻ በመሆኑ፤ ጋሼ ይትባርክ የትምህርት ቤት ስራስኪያጁ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፤ በሌሎች አውራጃዎች መከፈት አለባቸው የሚለው ተደጋጋሚ ውትወታው የነበረበት ነው። ጋሼ ይትባረክ ለስራአስኪያጁም ትልቅ ንቀት ነበረው። ግራዝማቹ ሹመታቸውን ያገኙት .. ባሌን ለመጎብኘት 1962 በመጡበት ሳይሆን አይቀርም። በትምህርት ሚኒስቴርም ግራዝማች አለ? እያለ ሰው ይሳለቅባቸው ነበር። ትምርታቸውም ከሰምንተኛ ክፍል በላይ እንዳልዘለለ ይነገር ነበር። እርሳቸውም ትምህርት ከማስፋፋት ይልቅ፤ በተለይ በጀማሪዎች ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከብቶቻቸውን ማርባት ነበር የተያያዙት። አንዴ አጥር ሾልኬ ልሄድ ስል ደረሱብኝና ሁለተኛ ቢደግመኝ ከትምህርት ቤት እንደሚያስወጡኝ አስጠነቀቁኝ። ለአባቴ ነገሪውኸረ ባክህ? እስኪ አባቱ ያስወጣኽነበር ያለኝ። እኔም እየተገላመጥኩም ቢሆን መሽሎኬን አልተውኩም። ምክንያቱም ወደ ዳግለሃን ለመሄድ ከበቴ ወጥቼ ተጎና ወንዝን ለመሻገር የሚቀርበኝ መንገድ አጥር መሽሎክን ያስገድዳልና! እንዴ! ቢያንስ 200 ሜትር በእዛ በጭቃ ከመሮጥ ያድናል።
ጋሼ ይትባረክ፤ የተማሪዎቹን ካውንስል ጥያቄ በተመለከተ ያደረገውን ነገር አሁን አላስታውስም። ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ ጥያቄያቸው ስላልተመለሰ፤ ከሁለቱ ጎበዝ ሕንዶች በስተቀር(ሜነንና ቬላፑላ የሚባሉ ነበሩ) ሌሎችን ሰብስበው፤ የዳሬክተሩን ቢሮ በጉልበታቸው ከጸሃፊዋ ተረክበው፤ ህንዶቹን ከቢሮው አስገብተው ቆለፉባቸው። የትምህርት ቤቱ የውጭ በሮች ሁሉ ተዘጉ። ተማሪው በሙሉ በአጥሩ ዙሪያ ተሰማርቶ በድንጋይና በዱላ ታጥቆ ቅጥር ግቢውን ነጻ አውጥቶአል።
እኛ አርቀን ድንጋይ ለመወርወር የማንችለው ጮጬዎች ድንጋይ በሹራባችንና በኮታችን እየሰበሰብን ለጎረምሶቹ እናቀርባለን። ማንን ለማጥቃት ነው? ሕንድን? አይደለም! ፖሊስን ነው! ፖሊስ እርምኛችንን።
ፖሊስ ጉድዩን ስምቶ አጥር ግቢውን 50 ሜትር በሚሆን እርቀት ከቦታል። ለመጠጋት ሞክሮ በጭራሽ የማይቻል ሆኖበታል። የድንጋይ ውርወራው ትእይንት የዋዛ አልነበረም። አይኑ የጠፋ ፖሊስና የተፈነከቱም ነበሩ። ፖሊስ ሌላ ትእዛዝ እስኪሰጠው ድረስ ጠመንጃ ቢይዝም ለመተኮስ አልቻለም። የተማሪዎች መለቀቂያ ሰዓት እየደረሰ ነው። ወላጆች ረብሻውን ቀደም ብለው ሰለሰሙ፤ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ልጆቻቸውን ለመከላከል ሽጉጥ የታጠቁ ወላጆችም አሉ። በከተማው ተማሪዎች ህንዶችን አገቱ ሳይሆን፤ ገደሉ! የሚል ወሬ ይነዛል። ይኽን የሰሙ ወላጆች ወደ ልጆቻቸው መሮጥ ይጀምራሉ። ወላጆች በተማሪና በፖሊስ ፍጥጫ መካከል እንደገላጋይም ሆነ እንደ ልጆቻቸውን ተከላካይ ሆነው ገቡ። አስተዳደሩ የሕንዶቹን ወሬ ሳያጣራ ለፖሊስ ተማሪዎችን ከእግራቸው በታች በጥይት እየመታ እንዲበትናቸው ትእዛዝ ደረሰው ይባላል። ግን እንዴት ሆኖ ትእዛዙን ይፈጸም ፖሊስ? በተለይ የበሉዋቸውን ወሬ የስሙ ወላጆች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ፖሊስ በጣም ተቸገረ። እናሳ! የወላጅ ኮሚቴ ተጠርቶ የሕንዶቹ ሕይወት መኖሩ ይጣራ ተባለ። የአድማው አስተባባሪዎች ፈቀዱ። ወላጆች ህንዶቹን ይዘው ከትምርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲወጡ፤ ፖሊሲም ቀኝሁዋላ ዙር! ብሎ ወደ ካምፑ ተመለሰ። ሕንዶቹም እንደወጡ ቀሩ! ተማሪዎችም ትጥቃቸውን የቅርጫት ኩዋስ መጫወቻው ሜዳ ላይ ስብስበው ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ቤታቸው ሄዱ። የጠየቁትም ጉዳይ አልቀረም። ተፈጸመላቸው። እስኪ መልሱን የማውቀውን ጥያቄ ልጠይቃችሁ። በእናተ ዘመንስ? የፖሊስ፣ የወላጅና የተማሪ ግንኙነቶች ምን ይመስላሉ? የአሜሪካንንማ አታንሱት! እጅግ አደገኛ ነው!!

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!