መነሻችን አማራ መዳረሺያችን ኢትዮጵያ!

 መነሻችን አማራ መዳረሺያችን ኢትዮጵያ!

 

አንድ ለመንገድ /2/ ... እስክንድር ነጋና አማራ

ቀጥለን እስክንድር በ1996(የዛሬ 20 አመት) በጋዜጠኛነቱ “አማራ የለም” ብለው ከሞገቱት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ጋር ያደረገውን ክርክር በደምሳሳው እንመለከታለን፡፡ እግረመንግዳችንንም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፤ “አንዳንድ ምሁራን አማራ የለም ሲሉ ይደመጣሉ፤ የአማራ ጠላቶች ግን አማራውን ለይተው ለማጥቃት ሲቸገሩ አናይም” ብለው አማራ የለም ባዮችን መተቸታቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ አስራት ለአማራ ጦርነት ማስተማር፤ እናት ለልጁዋ ምጥ እንደማስተማረች ይቆጠራል ብለው አማራ እንዲዋጋ በጥዋቱ አስጠንቅቀውት ነበር፡፡ዘግይቶም ቢሆን ዛሬ እውነቱን እያየነው አይደለም እንዴ?

አማራ

እስክንድር ፕሮፈሰር መስፍን አማራ የሚባል ጎሳ የለም፤[1] ቃሉ ለክርስትና ነው የሚቀርበው ያሉበትን በቂ መረጃ አላቀረቡም ይላል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደ ምንጭ የተጠቀሙባቸው ከሳቴ ብርሃን ተሰማ፣አለቃ ደስታ ተክለወልድ፣ አለቃ አሜና በአባ ዪሃንስ ገ/እግዚአብሄር(ትግርኛ) መዝገበ ቃላት የሰፈሩት ፍቺዎች አንድም ቦታ አማራ ክርስቲያን ማለት ነው የሚል የለባቸውም፡፡ ፕሮፌሰር ያጣቀሱት የአለቃ ደስታ ተክለወልድ፤አማራ ማለት ተጠምቆ ተገዝሮ፤ ማተብ አስሮ ቢልም አማራ የሃይማኖት መጠሪያ ነው አይልም፡፡የአለቃው ማብራሪያ የሳውዲ ዜጋ ለመሆን እስልምና መቀበል ወይም የእስራኤል ዜጋ ለመሆን(ከጥቂት አረቦች በስተቀር) የአይሁዲ ሃይማኖት ተከታይ መሆን እደሚያስፈልግ አይነት ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡

ዐማራ ለመሆን ለምን ክርስቲያ መሆን አሰፈለገ? ሲል እስክንድር ይጠይቃል፡፡ነገሩ ከታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እንደ እስክንድር ከሆነ ምክንያቱ ሙስሊም አማሮች ሃይማኖታቸውን እየተዉ ክርስትና እንዲቀበሉ ለማድረግ ነበር፡፡አማራ ነህ እስላም የሚለውም የመጣው ከግራኝ ወረራ በሁዋላ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት አልነበረም፡፡አማራን ከጎሳ ይልቅ ወደ ክርስትና የምንመድበው ከሆነ፤ ለምሳሌ አማራና ጋላን እንዴት ልንወስዳቸው ነው? ጋላ የሚለው ስም የሃይማኖት መጠሪያ ነው ማለት ሊሆን ይችላል?አለቃ ደስታ ጋላን፤ህዝብ፣ጭፍራ፣ስመ ነገድ፤ጋሉሳ ከሚባል ህዝብ የመጣ ወይም ከመሃል አፍሪቃ የመጣ(ተረት) ሲሉ ይገልጡታል፡፡

በዚህም መሰረት ጋላና አማራ ከጎሳ ጋር በተዛመደ መልኩ እንደተቀመጠ አዋዛጋቢ ሊሆን አይችልም ባይ ነው እስክንድር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን አማራ ሲሉ አባ ዩሃንስ ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለታቸው ነው የሚል መከራከሪያቸውም ብዙም የሚያስከድ አይደለም፡፡ እንደ እስክንድር ከሆነ አባ ዩሃንስ ያሉት በኢትዮጵያ የሚኖር የአንድ ህዝብ ስም ማለታቸው እንጂ፡፡

እስክንድር ኣማራ ጎሳ ነው ወይስ አይደለም ለማለት የፈረንጆችን ስራ ማየት አስፈላጊ ባይሆንም፤ለረዢም ጊዜ በኢትዮጵያ የኖሩት የፈረንሳዩን ኮልቦን(ስለ ሃይማኖትና ፖለቲካ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚል መድብል አሳትመዋል) ስራዎችና የአንቶሮፖሎጂስቱን  የአሜሪካውን የፍሬዴሪክ ሲመንስን ጥናቶች ማየቱ ሃሳብን ያጠራል ይላል፡፡

እንደ ኮልቦ ከሆነ... የአማራ አገር ታላቅ ተራራ የትግሬን ሀገር ተራራ በቁመት ይበልጠዋል። የተከዜ ወንዝ የአማራን ሀገር በሰሜን በኩል ያለውን ትግሬን ወሰን የሚለይ ነው። በደቡቡ በኩል የሚያዋስነው አባይ ነው። በስተምዕራብ በኩል ሻንቅላዎቹ የሚገኙበት አገር ነው”

ስለ ሃገሩ ቁዋንቁዋ

ህዝቡ በመልኩና በጸባዩ የዚህ ዘር ነው ለማለት የኢትዮጵያ ውስጥ ቁዋንቁዎችን መርምሮ ማወቅ የተረጋገጠ ብርሃን ይሰጣል።...

1ኛ/ የትግሬ ነዋሪዎች ከልዩ ልዩ ዘር የተደበላለቁ በመሆናቸው የሚበልጡት ዘራቸው የሚስማማ አይደለም።

2ኛ/ የአማራ ህዝብ ግን ከዚያው ከሃገሩ የተወለደ ህዝብ ስለሆነ እውነተኛ ባላባት ነው ለማለት ይቻላል።

3ኛ/ የኦሮሞ ህዝብ በቅርብ ዘመን ከውጭ ሀገር የመጣ ጥርቅም ህዝብ ነው ሲሉ ሃትተዋል።

ኮልቦ እንዳሉት ለምሳሌ በትግራይ ውስጥ በራያና በጸለምት እንዳለው የትግርኛ  ልዩነት፤ በኦሮሞ ውስጥ በሃረርና በወለጋ ኦሮምኛ ልዩነትና እንዲሁም በእንግሊዝ፤ በሊቨርፑልና በለንደን እንዳሉት የእንጊሊዘኛ ልዩነቶች በአማርኛ የለም። ክልቦ የዐማራ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ይልቅ አንድ ወጥ ነው ለማለት ያበቃቸው አንዱ የአማርኛ ቁዋንቁዋ አንፃራዊ ወጥነት ነው።

ፍሬዴሪክ ሲመንስን ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚል ባወጣው ጥናታዊ ጽሁፍ፤ “በኢትዮጵያ አማራና ክርስትና እንደ አንድ ሀገር ሆነው ይታያሉ። አንድ አማራ ክርስትና ከተወ አማራ መሆኑ ቀርቱዋል ተብሎ ይታመናል።

ሆኖም ሁሉም ክርስቲያኖች አማራ ናቸው የሚባሉት በቁዋንቁዋና በባህል አማራ የሆኑት ናቸው” ይላል።

ለምሳሌ በሰሜን ያሉ አገው ክርስቲያኖች አማራ ናቸው አይባሉም። በጎንደር አቅራቢያ ያሉት ጉሙዞችም ክርስትናን በመቀበላቸው ብቻ ዐማራ ሆኑ ተብሎ አይጠሩም ሲል በአማራና በክርስትና ያለውን ልዩነት አጥርቶአል።

ፍሬዴሪክ ሲመንስ የአማራን ባህልም በማጥናት አማራ ከሌሎች ህዝቦች/ጎሳዎች(ትግራይ) የበለጠ የጋራ ስነልቦና እንዳለው በጥናቱ አረጋግጡዋል።

ታዲያ ይኽ በሆነበት ሁኔታ ፕሮፌሰር መስፍን አማራ የሚባል ጎሳ የለም ማለታቸው ፍጽም ኢሳይንሳዊ ያደርገዋል ይላል እስክንድር።

 

ይቀጥላል



[1] ድል ለዲሞክራሲ እስክንድር ነጋ 2013

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!