የምርጫው ነገር፤ ደግሞ መጣ!
የምርጫው ነገር... ደግሞ መጣ!
===
“እኔ የምለው… ወያኔ በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን በሰላም ያስረክባል እንዴ”? ባያስረክብስ ምን መደረግ እንዳለበት ዝግጅት አለ እንዴ? እኚህ ጠያቂ ዛሬ ስማቸው ብዙም አይጠራም። የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ታዬ ወልደሰማያት ናቸው።
===
ከምርጫው በፊት ለጥያቄዎቻቸው መልስ የሰጣቸው ሰው አልነበረም። በመጨረሻም የጠበቁት ሆነ። ወያኔ በቅንጅት ተሸነፈ። ግን ሽንፈቱን አልተቀበለም። የለመደውንም ደም አፈሰሰ። የተቃዋሚዎቹም አንድ ወጥ ያልሆነ አመራር ተደምሮ ዴሞክራሲ ጨነገፈ። ጭቡ ውሎ ይደር እንጂ ይደርሳል ትል ነበር አክስቴ። አይ! አይ! ናይ! ወያኔ! ዛሬ የራስሽ ደም ጢሻ ለጢሻ፤ ገደል ለገደል እየጎረፈ ነው። እብሪአትና ዘረኝነት መጨረሻቸው ውድቀት ነው።
የአብይ አህመድ አሊ ምርጫ
===
ታዲያ … የአብይ አህመድ ብልፅግና ምርጫውን በግድም በውድም ካላሸነፈ ስልጣን ይለቃል ወይ? ካለሸነፈና እንደ ወያኔ አሻፈረኝ የሚል ከሆነ ምንድን ነው የሚደረገው? ቀድሞ ዝግጅት ለማድረግ ታስቦአል ወይ በተቃዋሚዎቹ?
ብልፅግና በኦሮምያ፤
1. ብልጽግና የድሮ ኢሕአዴግ ሲቀነስ እየተደመሰሰ ያለው ወያኔ ነው። ልብ በል የወያኔ አባል የነበሩና ቀደም ሲል ወያኔን ለቀው ወደ ብልጽግና የተቀላቀሉ አሉ። አሁንም በትግራይ ብልጽግና ውስጥ ተደራጅተዋል። ለምሳሌ የትግራይ ተሹዋሚ ዶ/ር ሙሉ ወያኔ የነበረ ነው። እነዚህ አሁንም የጎንደርና የወሎ ግዛቶች ይገቡናል፤ እናስመልሳለን የሚሉ ፀረ-ስብ ናቸው። ከእነዚህ ጋር አማራ ጉዳይ የለውም።
2. ብልጽግና ውስጥ የፖለቲካ ሹኩቻ በተለይ በአማራና ኦሮሞ መካከል ስለተከሰተ ፓርቲው አጠቃላይ ጉባኤ ማድረግ እንደተሳናው ይነገራል። ምን ማለት ነው ግን አጠቃላይ ጉባኤ ማካሄድ አለመቻል? በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም፤ አጠቃላይ ጉባኤውን ቢያካሄድ፤ ዶ/ር አብይ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን ያለው እድል እርግጠኛ አይደለም ማለት ሊሆን ይችላል። ይኽ ደግሞ እናቱ ትንግርት ለተናገረችችለት ንጉስ የማይዋጥ ጉዳይ ነው።
3. ዶ/ር አብይ በአጭር ጊዜ የስልጣን ዘመኑ፤ ተወዳጅነት እንዳተረፈ ሁሉ፤ ዛሬ ደግሞ የተአማኒነቱ ችግር እየጎላ ስለመጣ የስልጣን መሰረቱ በተለይ በአማራና በሌሎች ኢትዮጵያዊነትን በሚያስበልጡ ዜጎች ሰፈር እንደሳሳ መገመት አያዳግትም። ኦሮሞንም በተቻለው ሁሉ ለመጥቀም ቢሞክርም፤ የድጋፉ መሰረት ስልጣኑን ለማስቀጠል አስተማማኝ አይደለም። እነ ኦነግና ኦፌኮም ድጋፍ ስላላቸው፤ እውነተኛ ምርጫ ከተካሄደ የኦሮሞ ብልፅግና በኦሮሚያ በሚባለው ክልል በነጻ ምርጫ ማሸነፉን እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። በተጨማሪም በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ተብዬ ከተሞች ነዋሪዎቹ ለአብን፣ ለባልደራስ፣ ለመኢአድ(ጥምረት ፈጥረዋል) እንዲሁም ለኢዜማና ለሌሎች ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይኼን ሁኔታ በመገምገም ነው ከአሁኑ የድጋፍ ስልፍ ውጡልኝ፤ እኔ በውድም በግድም ስልጣን ላይ መቆየት አለብኝ። አማራንም በኦሮሚይ አሸማቁልኝ። አብንን ባልደራስንና መኢአድን እመርጣለሁ ካለ፤ ዋ! ዋ! እኔን ነፍጠኛ/አማራ አያድርገኝ! አይነት ማስፈራሪያ ለማስተላለፍ የተሞከረው።
4. በአጭሩ አብይ አህመድ የስልጣን መሰረቱ አስተማማኝ ስላልሆነና ስልጣን ላይ ለመቆየት ደግሞ ብርቱ ፍላጎት ስላለው በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ለመልቀቅ የተዘጋጀ ሰው አይደለም።
ብልፅግና አማራ፤
===
አማራ ክልል በሚባለው ውስጥ ብልፅግና አማራ፣ ጥምረቱ፣ የአማራ አንድነት ዴሞክራሲ ግንባር፣ ኢዜማና ሌሎች እጩዎቻቸውን የሚያቀርቡበት የፖለቲካ ገበያ ነው። በእኔ ግምት እውነተኛ ምርጫ ከተካሄደ ሊያሸንፍ የሚችለው ጥምረቱ በተለይም አብን ነው። አሁንም እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ አብን/ጥምረቱ ካሸነፈ ብልጽግና አማራ፤ ኮሮጆ ግልበጣ አይገባም ወይ ነው? ሕዝቡስ ይኼ እንዳይሆን… ማለትም ድምጹ እንዳይነጠቅ ምን አይነት ቅደመ-ዝግጅት ለማድረግ እያሰበ ነው? ብልፅግና አማራ ሽንፈቱን በፀጋ ከተቀበለ ፤ በኦሮሙማ በሽታ የተለከፈውን ብልፅግና ኦሮሞን ማንሳፈፍ ይቻላል። ከአብን/ጥምረቱ ጋር እኩል ወይም የበለጠም ይሁን ያነሰ ድምፅ ካገኘም አሁን ካለው የፓርላማ መቀመጫ እኩል ይዞ ከኦሮሞ ብልጽግና ጋር ሊቀጥል ስለማይችል የአማራ ብልፅግንና ፓርቲ የፖለቲካ ፋይዳው እዚህ ግባ ሊባል አይችልም።
የሶማሌ፣አፋር፣ የደቡቡና የጋምቤላ ብልፅግኖች
===
እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያዊነቱን ከሚያቀነቅኑ ኃይሎች ጋር ቅራኔ የላቸውም። አንዳንድ ሸውራራዎች ባይታጣባቸውም። በምርጫው ደግሞ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። የኦሮሞ ብልጽግና በኦሮሚያ ለማሸነፍ በቂ ድምጽ ካላገኘ፤ ሶማሌ፣አፋር፣ጋምቤላና ደቡቡ ከብልጽግና ኦሮሞ ጋር ድምጻቸው ተደምሮ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ቁጥር ያገኛሉ ተብሎ ቢታሰብ እንኩዋን፤ የኦሮሞ ብልጽግና የአዛዥ ናዛዥ ስልጣን አይኖረውም። የኦሮሞ ብልጽግና እስከነአካቴው በኦሮሚያ ከተሸነፈ የእነዚህ ክልሎች በብልፅግና ስም ማሸነፍ የክልላቸውን ስልጣን ከማስረገጥና በፓርላማ ከመወከል ሌላ ፍይዳ አይኖረውም። ቤኔሻንጉል ከኦሮሙማ ጋር የተጣመደ ቢሆንም፤ የተፈናቀለውም ድምፅ ይሰጣል ተብሎአልና፤ ከዚህ ክልል ብልጽግና ኦሮሞ ሊያገኝ የሚችለው የፖለቲካ ትርፍ እምብዛም ነው።
የእነዚህ የብልፅግና የነገድ ፓርቲዎች ፋይዳ በክልል መወሰን የኃይል ሚዛኑን ደረቅ አድርጎታል። ለሌላ አማራጭ እድል አይከፍትም። ከጥምረቱም ሆነ ከኢዜማና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመቀናጀት የሚያስችላቸው የፖለቲካ አካሄድ አለ ወይ? ወይስ በደመነፍስ ብልፅግና በሚባል ጉሮኖ ውስጥ ታጉረው የሚገኙ ናቸው? ለምሳሌ የሶማሌም ይሁን የአፋር ክልል ብልፅግናዎች እንደሚያሸነፉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይሁን እንጂ ድምፃቸውን ከብልጽግና ውጭ አውጥተው ከሌሎች ጋር መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ደንብ አላቸው ወይ? ለምሳሌ የሶማሌና የአፋር ብልፅግና ከአብን/ጥምረቱ ጋር መንግስት መመስረት ይችላሉ ወይ? አይመስለኝም።
ምርጫ ቦርድ
===
ምርጫ ቦርድ በብልጽግና የተሾመ ስለሆነ ብድሩን እየከፈለ ነው። ለሌሎች ፓርቲዎች እንደ መስፈርት የተወሰደው የአጠቃላይ ጉባኤ ማካሄድ ነገር ብልጽግናን እንደማይመለከተው አሳይቶናል። ይኼም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንና የአማራን ብሄረተኝነት የሚያቀነቅኑትን ፓርቲዎች የብልፅግና ምስክርነትን ተንተርሶ በምርጫው እንዳይሳተፉ ሰርዞአቸዋል። ለምሳሌ የዐማራ ሕልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና ኢዴፓ መስፍርታቸውን በሚገባ ቢያሟሉም የቅርጫው መደብ ይሳሳብኛል በሚል፤ ሆን ብሎ ከአለአግባብብ አግዶአቸዋል። አዲስ አበባና ድሬዳዋም የተለየ ምርጫ ቀን እንዲካሄድባቸው አድርጎአል። ይኼም የአብይን ስልጣን ለማስቀጠል የተደረገ ጥርጊያ መንገድ መሆኑ ግልጥ ነገር ነው። አብንም ቢሆን በምርጫ ቦርድ ያልተሰረዘው፤ አማራን ይወክላል ተብሎ የሚገመት ድርጅትን በዚያ ደረጃ ማግለሉ የማያዋጣ ስለሆነ ብቻ ነው። ለዚህ ነው አሁን በድጋፍ ስም አብን ላይ ሁለተኛ ዘመቻ የተካሄደው። ስለዚህ የብርቱካን ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ከገባ ውሎ ያደረ ስለሆነ፤ ምርጫውን ለብልፅግና በሚያዳላ መልኩ ሊያስቁዋጭ እንደሚችል ከወዲሁ በቂ ፍንጭ ሰጥቶአል።
===
እንግዲህ ምርጫው እነ እስክንድር ነጋን ሸብቦ፤ በብልጽግና አሸናፊነት እንዲደመደም እየተጎነጎነ ስለሆነ፤ ምን መደረግ አለበት ከድህረ ምርጫ በሁዋላ በሚለው ሊመከርበት ይገባል።
ምክረሃሳብ አንድ
===
ጥምረቱ በአማራ ክልልና በትላልቅ ከተሞች የሚያሸንፍ ከሆነ፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ለእራሱ ሲል ሽንፈቱን ተቀብሎ፤ ጥምረቱን እንኩዋን ደስ ያለህ ሊለው ይገባል። በዚህም አማራውንም ሆነ ኢትዮጵያን ይክሳል። ጥምረቱም በአማራ ብልጽግና ውስጥ አቅም ያላቸው ሰዎችንና በምርጫው የሚሸነፉትንም በሚመሰርቱት አስተዳደር ውስጥ ሊያካትቱዋቸው ይገባል። ለነገሩ አሸናፊው ወገን የመንግስት ቢሮክራሲዎን እንዳለ ስለሚወርስ በጥምረቱ ማሸነፍ ማግስት የአማራ ብልጽግና ደጋፊዎች ስራችንን እናጣለን የሚል አንዳች ስጋት ሊደርስባቸው አይችልም። ስለዚህ ብልፅግና አማራ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለመሸነፍም ራሱን ዝግጁና ስልጡን ማድረግ ይጠበቅበታል። እንዲህ ከሆነ አማራ ድጋሜ ታሪክ ሰራ ሊባል ይችላል።
ምክረሃስብ ሁለት
===
የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ6ስተኛ ጊዜ በምርጫ ስም አምባገነኖች በስልጣን ማማ እንዲቀጥሉ መፍቀድ የለበትም። ምርጫው ከተጭበረበረ ከአሁኑ በሰላማዊ መንገድ ሕዝባዊ አመፅ እንዴት እንደሚቀጣጠል ዝርዝር ዝጅግት ያስፈልጋል። መራጩ የትም ሆነ የት፤ ብልጽግናን እየደሰኮሩ ብልግናን የሚያራምዱትን እምቢ! ሊላቸው ይገባል።
በርቱ! እግዜአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝቡዋን ይታደግ!
ቦጋለ ካሣዬ
Comments
Post a Comment