አገር ቤት ደርሶ መልስ....
ባህርዳር...
እንደ ደረስን ወደ ሆቴላችን በባጃጅ ለመሄድ ሃሳቡ ነበረን። ሻንጣችንን ከመኪናው ላይ ያወረደው ልጅ ግን፤ ..."ጋሼ እኛ ባጃጅ የሌለን ምን ስርተን እንብላ? ሆቴላችሁ እዚህ ቅርብ ነው። ኑ ተከተሉኝ"!.... እንዳለውም አምስት ደቂቃም ሳንራመድ ደረስን። እውነቱን ነው። አሳዘነኝ።
አንድ ወዳጄ እንዳጋጣሚ ለስራ ጉዳይ እዚያው ባህርዳህ መጥቶ ሆቴል ይዞ ስለነበር... ጣና ባህሩ ዳር ወስዶ ጥሩ ራት ጋበዘን። ይሁን እንጂ ልጄ አይነቱ በዛበት መሰለኝ... አሞት አደረና በሚቀጥለው ቀን ያቀድነው ፕሮግራም ሊካሄድ አልቻለም። እኔም መጽሃፍ እያነበብኩ ከሆቴሉ ሳልወጣ ዋልኩ። አንድ ዘመድም ስለነበረኝ ረፋዱ ላይ የርሱን ልጆች ላይ ሄድኩኝ። በማግስቱም ጥዋት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የባህርዳር ጽ/ቤት ካረፍኩበት ሆቴል ቅርብ ስለነበር ሰተት ብዬ ሄጄ ተዋወኩዋቸው። የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ገና አልቆ ስላልተበተነ ላገኘው ባልችልም፤ በመሬት የግል ይዞታና በኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ላይ ጥሩ የሃሳብ መለዋወጥ አድረግን። ስለ አብንና አዴፓ ግንኙነት በሚመለከት ከነርሱ የተሰጠኝ መልስ ግን ስጋት ውስጥ ጣለኝ። አዴፓ አብንን ለማጥፋት እንደሚሰራና አብን በህዝቡ ድጋፍ ብቻ ህልውናው ሊጠበቅ እንደቻለ አስረዱኝ። አዴፓ ያሰረባቸውን አባሎቻቸውንም ህዝቡ እንዳሰፈታቸው ነገሩኝ። ይኼንኑ ስጋቴን አዲስ አበባ ተመልሼ እኔ አባል ለሆንኩበት የአማራ ህልውና የኢትዮጵይ አንድነት ድርጅት ሰዎች ነገርኩዋቸው። የአማራ ህልውና ለኢትዮጵይ አንድነት አመራሮች ከሁለቱንም ከፍተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች ጋር ተነጋግረዋል። ድርጅቶች እየተቀራረቡ ሲመጡ ሊፈታ የማይችል ምንም አይነት ጉዳይ እንደማይኖር ነው የሚያስቡትና እንደ አፋቸው ያድርግላቸው።
ቀጥለን ታንኩዋ ተከራይተን ጣና ላይ በመንሳፈፍ ጉማሬና ፔሊካን ወፎችም አየን። አንድም ቅርብ ገዳም ጎበኝን። በሶስተኛው ቀን ልጄ በደንብ ስለተሻለው ጉዞ በመኪና ወደ ጢስ አባይ ሆነ። ወዳጄም አብሮን ሄደ። ከአስፋልቱ መንገድ ወደ ግራ ታጥፈን ወደ ሃያ ኪሎ ሜትር በመኪና ከተጉዋዝን በሁዋላ ከአንድ ሰአት ያልበለጠ ደግሞ በእግራችን ሄድንና ጢስ አባይ ደረስን። ወደ ጢስ አባይ ስንሄድም ሆነ ከጢስ አባይ መኪናዋን ያቆምነበት ቦታ እስክንመለስ ድረስ ብዙ አጀብ ነበረን። የአካባቢው ልጆች ናቸው። ቀን ጎጃም ተምረው ማታ ቤታቸው ጎንደር ያድራሉ። የሰፉትን አገልግል፣የፈተሉትን ነጠላና ሌሎች እቃዎችን ግዙን የሚሉ ናቸው። ካልገዛኻቸው እንዲህ በቀላሉ የሚለቁ አይደሉም። ተስፋ አይቆርጡም። "ጋሼ እቺን ግዛኝ... ጋሼ ካንቺ ነው የምገዛው አላልከኝም ነበር ?"። ውትወታቸው አይጣል ነው። የተከተሉኝን ሶስቱንም ጠራሁና ከሁላችሁም መግዛት ስለማልችል ተስማሙና ካንዳችሁ አንድ ነገር ልግዛ አልኩዋቸው። ምንም ሳያቅማሙ እሺ አሉ። አንድ አገልግል በስድሳ ብር ገዛሁና እፎይ አልኩ። ይሁን እንጂ አጀቡ አሁንም አልቀረ። አንድ መልከ መልካም ልጅና ምናልባትም ትንሽ እህቱዋ ይከተሉኝ ጀመር። .."ለምን እኔን ብቻ ትከተሉኛላችሁ? ልጄም ጉዋደኛዬም እነዛ ናቸውና እነርሱን እስኪ ደግሞ ተከተሉ"! ወይ ፍንክች...." ጋሼ ደግሞ ሰው ልቡ የፈቀደውን እንጂ የሚከተል"! አሁን ከትልቁዋ ጋር ወግ ጀመርኩ...
-"ስንት አመትሽ ነው"...." ሃያ"
-"ታዲያ አግብተሻላ!፡..." ምነው ጋሼ አግብቺ ምን ላረገው? ደግሞ ራሴን ሳልችል።"
የእኔ ልጅ አላገባም ። አንቺ ብታገቢው ደስ ይለኛል።"። እኔ ሽማግሌ ባልሆን ኖሮ ዛሬ ጠልፌ ነበር የምወስድሽ...!.." እንደ ኮረከሩት ሳቀች"።
አንድ ወንድምና አንድ እህት አሉዋት። አባትዋ ገበሬ ነበር። አርፈዋል። እናቱዋ አሉ። ሁለት አመት እናቱዋን ለመርዳት ብላ ትምህርቱዋን አቁዋርጣለች። አሁን ደግሞ ጥዋት ትምህርት ቤት ትሄዳለች... ከሰአት ደግሞ እነሆ ቱሪስት እያሳደደች ከቀናት ትንሽ ፈራንክ ታገኛለች። በሚቀጥለው አመት ባህርዳር ሄዳ ትምህርቱዋን ለመቀጠል እቅድ አላት። እርስዋ በምትኖርበት ቀበሌ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት አያገኙም። ስለዚህ ተማሪዎቹ የሚያጠኑት በላምባ ነው። ይባስ ብሎም የአካባቢው ባለስልጣኖች መብራት ይገባላችሁዋል ብለው ከየቤተሰቡ መቶ መቶ ብር ቢሰበስቡም እስካሁን የመብራት ተጠቃሚ አልሆንም ነው የምትለኝ። የመብራቱ ፖል ከመንደራቸው አራት መቶ ሜትር እርቀት ላይ ተገትሮ ቆሞአል። በተደጋጋሚ አቤቱታ አስምተው ማንም የሚሰማቸው አላገኙም። ይኼን የሚያነቡ ፖለቲከኞች ካሉ ነገሩን ቢከታተሉ ጥሩ ነው። በግሌ ለክልሉ ሃላፊዎች ደብዳቤ እጽፋለሁ። ወደ መኪናችን ደረስን። በሉ አሁን እኔ ምንም አልገዛችሁም ብዬ ጉርሻ ሰጠሁዋቸው። ደስ አላቸው። መኪና ውስጥ ገብቼ ሳያት ትልቁዋ ከአንድ ትልቅ ሴትዮ ጋር(ምናልባት እናቱዋ ሳይሆኑ አይቀሩም) ቆማ ወደ እኛ ሲያዩ ተገጣጠምን። ጠራሁዋትና የገዛሁትንም አገልግል ስጥቻት ተለያየን።
ቀጥለን ባሌ ጎባ ዘመዶቻችንን ለመጠየቅ ሄድን። ስንመለስ ናዝሬት ያልቱንም አይተን ደብረዘይት አንድ ቀን ቆም አልንና አዲስ አበባ ተመለስን።
እድሳት...
በሶስት ሳምንታት ቆይታችን ውስጥ አምስት ሆቴሎች ውስጥ አልጋ ይዘናል።አልጋዎቹ የሚመቹ አንሦላዎቹም የጸዱ ናቸው። ሁሉም ሆቴሎች ግን የጸዳ ፎጣ የሚያቀርቡ አይደሉም። አንድ በጎባ ከተማ ጥሩ ሆቴል የሚባለው ውስጥ ክፍል ሃምሳ አንድን ተከራየን፡ ተከራዮቹ ብዙዎቹ ፈረንጆች ናቸው። ይሁን እንጂ የሽንት ቤቱ በር ከተዘጋ በሁዋላ ክውስጥ አይከፈተም። ሰው መጥቶ ነው ከውጭ ሊከፍተው የሚችለው። ይኼን የሚያሕል ሆቴል የራሱ የውሃ ማጠራቀሚያ ስለሌለው ውሃ ይመጣል፤ ይሄዳል።ለዚያ ትልቅ ሆቴል ሶስት አስተናጋጆች ብቻ ናቸው ውር ውር የሚሉት። ሻይ አዘን ግማሽ ሰአት በላይ መጠበቅ የተለመደ ነው። አገረኛው ሆቴሉ ከመንግስት ወደ ግል የተዛወረው በጣም በትንሽ ክፍያ ነው እያለ ያማል። ምናልባት መንግስት በቅርቡ ሊወርሰው የሚችል ሁቴል ሳይሆን አይቀርም። ጎንደር ያረፍነብት ሆቴል ውስጥ እንዲሁ የሻወሩ የመስታወት መጋረጃ በደንብ ስለማይገጠም ውሃው በየቦታው ይፈነጣጠቃል። የባህርዳሩ ሆቴል እንዲሁ የውሃ ማሞቂያው ሲንሰር ስለማይሰራ ሌላ የተለቀቀ ክፍል ሄደን ሻወር መውሰድ ነበረብን። ደብረዘይት የያዝነው ሆቴል ክፍያው ሳውና ያለውና የመታሻ አገልግሎቱንም የሚያጠቃልል ነው። በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር ውድ ሆቴል ነው። ሁሉም ነገር የተሙዋላበት ነው። ይሁን እንጂ ከሳውና በሁውላ ሻወር የሚወሰድበት ቦታ ጣሪያው በእንፋሎት የበሸቀጠና የቆሸሸ ጥቀርሻውን ዞር ብሎ ያየውም የለም። መኝታ ክፍል ውስጥ ያለውም የሻወሩ እጄታ ሆነ ቀዳዳዎቹ በበሃ ድንጋይ ቅርፊት እየተሞሉ ናቸው። በኢትዮጵያ... "የቀለም እንጂ ሌላ እድሳት አይታወቅም!" አለኝ አንድ ታዛቢ።
የህዝብ ማመላለሻዎች...
- አዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግርዋን ለማቃላል የከተማ ውስጥ አገልግሎቱን ባቡር መስመሮች ማበራከት የግድ ይላታል። ይኼን ሁነኛ ጉዳይ ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የሚወዳደር ሰው እንደ ትልቅ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ቢነሳ እመክራለሁ።
- ባህርዳርም ሆነች ናዝሬትም ይኼን ማድረግ አለባቸው። በእነዚህ ከተሞች የባጃጅ ቁጥር እጅግ በመብዛቱ የከተሞቹን ትራፊክ ሆነ ውበት እያበላሸው ነው።
- ረዢም ርቀት የሚጉዋዙ አውቶብሶች ምቾታቸውና የሚሄዱበት ጊዜ ቁጥጥር ያስፈልገዋል። ከአዲስ አበባ ወደ ጎባ የተጉዋዝንበት አውቶብስ አንደኛ ደረጃ ነው። ይሁን እንጂ ምቾቱ በጭራሽ ለቁሳቁስ ካልሆነ በቀር ለማንኛውም ፍጡር የሚሆን አይደለም። ጉልበታችን ከመቀመጫው ጀርባ ተጣብቆ ስንሰቃይ ነው የደረስነው። እንደነገሩኝ ከሆነ መቀመጫዎቹ ሆን ተብሎ ብዙ ሰው እንዲይዙ ሆነው ነው የተገጠሙት። ሌላም የሚገርም ነገር አለ። አውቶብሱ ውስጥ እንደገባን የመቀመጫ ቁጥራችን የተመለከተበትን ትኬት እየጠየቀ ትኬት ቆራጩ ህጋዊ ደረሰኝ ቆረጠና ሰጠን። ከዚያ ደግሞ ሮቤን አልፈን ጎባ ልንደርስ ስንል ደረሰኙን ተቀበለንና የአውቶብሱን መስኮት ከፍቶ ጣለው!! ይኼ መቼስ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም። በተጨማሪ አንድ አውቶብስ ከሞላ ብቻ መንቀሳቀስ አለበት የሚባለው ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ነው። አንድ ከጥዋቱ አንድ ሰአት መነሳት የሚገባው አውቶብስ ካልሞላ ስንት ሰአት መጠበቅ አለበት? የተሳፋሪውን መብትም ለማክበር የሰአቱም ጉዳይ አብሮ መታየት አለበት። በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ውስጥ ያየሁት ሌላው ጉዳይ ተሳፋሪው እንደ ዋና የገቢ ምንጭ ተቆጥሮ ምንም እንክብካቤ እንደማይደረግለት ነው። ሸፌሩም ከመንዳት ትኬት ቆራጩም ገንዘብ ከመቀበል ውጭ በተሳፋሪውና በእነርሱ መካከል ምንም ግንኙነት የለም።
መጽሃፍ...
ጎንደርም ሆነ ባህርዳር መጻህፍት ከሚያዞሩ ልጆች ገዝቻለሁ። አዲስ አበባም እንዲሁ ከመነገድ ገዛ ገዛ አደረኩና ወደ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በአዲስ አበባ ዩኒቨስቲ ፕሬስ ከሚታተሙትም ለመግዝት አቀናሁ። በሩ ላይ መታወቂያ ይጠየቃል። ፓስፖርቴን አሳየሁ። ..."ጥሩ ስጠኝ ስትወጣ እመልስልሃለሁ አለኝ።" የሚገባ የሚወጣውን የሚቆጣጠሩት ቢያንስ አምስት ይሆናሉ። ..."ፓስፖርቴን ለመያዝህ ምን ማስረጃ ትስጠኛለህ "? ..."ምንም"። የሚሰራው በእምነት ነው። ሌላ የኢንሹራንስ ካርድ ስለነበረኝ ..."ይኼን መያዣ ላድርግ ...ፓስፖርቴን ግን አልያሲዝም"... አልኩ። .."እሺ " ብሎ ተቀበለኝና ደረት ኪሱ ውስጥ ከተታት።
ካምፓሱ ከርክሶአል። መንገዱ ፈራርⶃል። ወደ መጻህፍት መሸጫው ገባሁ። መቃብር ቤት ይመስላል። የቤቱ ሽታ በሰንደል ጭስ ስለታወደ ...ራስ ምታት እንዳይቀሰቀስብኝ ብዬ ሁለት መጻህፍት ገዛሁና ፈትለክ ብዬ ወጣሁ። መታወቂያ በማስያዝ የገጠመኝን ችግር ለመጻህፍት ሻጭዋ ነገርኩዋት። ..." እውነትህን ነው እንደ አንድ ድርጅት ቢያንስ ባጅ መሰጠት ነበረበት" አለቺኝ። ..."በይ እህት ..ይኼን ለአስተዳደሩ ንገሪልኝ። ትልቅ ድክመት ነው። "
Interesting article. Thank you for sharing.
ReplyDeleteወንድም ቦጋለ፤ ይህንን በማካፈልህ በጣም ደስ ብሎኛል። እንኳን ለዚህ አበቃህ። የጎባ ጉዞህ በኮፈሌ፤ ዶዶላ፤ አዳባ አርጎ ከሆነ፤ በየመንገዱ ስላለፍካቸው ከተሞች ጥቂት ብታወሳን ጥሩ ነበር። ባሌ የትምህርቱ ስርአት እንዴት ነው? የላቲኑ ጽሁፍስ? ጥንት የዶዶላ ተማሪ ነበርኩ። ጎባንም አውቀዋለሁ። አዝማች ደግልሃንስ እንዴት ነው?
ReplyDeleteበርታ
ወንድምህ - ፀሐይ ደመቀ