ወርቅ-ቅብ፣መርዘኛ ብእር። እኛም አውቀናል፤ ጉድጉዋድ ምሰናል!

ወርቅ-ቅብ፣መርዘኛ ብእር። እኛም አውቀናል፤ ጉድጉዋድ ምሰናል!

ከቦጋለ ካሳዬ፤ ማርች 2014 አምስተርዳም

የአፈንዲ ሙተኪ ጮሌነት ፀሃይ ሞቆታል። በዚህም ምክንያት ተጨንቆ በትክክል ማሰብ እንደተሳነው ከመጣጥፎቹ መረዳት አዳጋች አይደለም። አፈንዲ የከሸፈውን የተስፋዬ ገ/አብን ተልእኮ፤ ከውስጣችን ተቀላቅሎ ረቀቅ ባለ መንገድ እያካሄደ የሚገኝ ለምድ የለበሰ የቀበሮ ባሕታዊ ነው። ብዙ ክሶችን ደረደርኩ አይደል? ምክንያቶቹን እንያቸዋ አብረን።
 
1.በኦነግነት ተከሰስኩ ብሎ በሰጠው ምላሽ ላይ፤ ኦነግን ይደግፍ እንደነበርና፤ አሁን ግን በኦነግ የመገንጠል አቁዋም ላይ ስለማይስማማ እንደማይደግፈው ነግሮናል። ሃቀኝነት ያለው ምላሽ አይደለም።
1.1 በዚሁ ምላሹ፤ በቂ ዋቢ ሳይጠቅስ ‘ኦነግ አደረጋቸው’ ተብሎ ሲጻፍና ሲነገር የነበረውን ወንጅሎች፤ በአንድ ቦታ  ከተፈጸመው ወንጀል በስተቀር ውድቅ አድርጎለታል። እውነት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከእርሱ ገና ድሮ ቀድሞ ኦነግ ከሽግግሩ መንግስት ከመውጣቱ በፊት እርሱ በሚያስተዳድርበት አካባቢ ስለተፈጸመው ወንጀል ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ራሱ ስለነገረን፤ የአፈንዲ ማብራሪያ መረጃ ላልነበራቸው ሰዎች ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር፤ ለብዙዎቻችን ተደጋጋሚ ነገር በመሆኑ ምንም ተጨማሪ ፋይዳ አላየንበትም። በነገራችን ላይ እኛ እራሳችንን “እኛ” የምንለው፤ እኔ የሚለው ተውላጠስም ስለ ራስ የገነነ እድምታ እንዳይፈጥር በመስጋት ነው። እኛ የምንጽፋውም ሃሳብ ቀደም ሲል ሌሎች ያጤኑት ወደፊትም ሊሎች ሊያጤኑት እንደማይቀሩ ከግንዛቤ በማስገባትም ነው። ቀዳማዊ ኃይሥላሴ ግን “እኛ”ይሉ የነበረው፤ የዘውዱ፣የሃይማኖትና የሕዝቡ ተቀቢ፣ተወካይና ገዢ መሆናቸውን ለማንጸባርቅ እንጂ፤ አፈንዲ እንዳለው የሐረር ሰው ስለነበሩ አይደለም።
1.2 የሆኖ ሆኖ አፈንዲን ኦነግ ነው! ያልንበት ምክንያት ከኦነግ ወንጀል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ደግሞ በኦነግነት መከሰስ አይገባም። የኦነግ አባል ወይም ደጋፊ መሆን ማለት እኮ የፖለቲካ ምርጫ ነው። አጎቱና አባቱ በኦነግ ሰበብ በደርግ በደረሰባቸውም ግፍ ቂም ይዞ ነው በሚልም በኦነግነት አፈንዲን አልጠረጠርነውም። ኦነግ ነህ ያልነው ራሱ፤ ለተስፋዬ ገብረአብና ለኢሳያስ አፈወርቂ ባለው ወገንተኝነት፣መራራ በጦቢያ መጽሄት በሰጠው ቃለ ምልልስ ኦሮሞን ከፋፍሎአል ብሎ በመክሰሱና፤ የኦሮሞ ጥያቄ ወይ በኢትዮጵያ መብቱ ተከብሮለት መኖር አሊያም ተገንጥሎ(በሽታ ይገንጥለውና!) ራሱን ማስተዳደር እንደሆነና እርሱም ይኸን እንደሚደግፍ በመጻፉ ነው። አትፍራ ኦነግ ነህ። ወይም የኦነግን የፖለቲካ መስመር ትደግፋለህ።

2. ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያ በጎ አሳቢ ነው በማለቱ የተነሳ፤ ለተሰነዘረበት ወቀሳ ደግሞ፤ ሌላ ሰው ማነካካት አስፈልጎታል። ወይም ሌላ የፖለቲካ ዳንኪራ ሲረግጥ ይታያል። ዳንኪራውም እ.አ.አ በለንደን 1991 የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና የኢሳያስ አፈወርቂ ግንኙነትን የተመለከት ነው። ለነገሩ ኢሳያስና ፕሮፌሰሩ ከለንደንም በሁዋላ አዲስአባም ተገናኝተዋል። ቁምነገሩ ተገናኝተው ምን አወሩ ነው? ስለ አዲስአባው አላውቅም። የለንደኑ ግንኙነት ፍሬ ነገር ግን ምንም ሚስጥር የለውም። እንደውም ደርግ ሊወድቅ አካባቢ፤ ኢሳያስ አዲሳባ ገብቶ ስልጣን ይይዛል የሚል ከፍተኛ ግምት ነበረ። ትዝ ይለኛል መንግስቱ ከዙፋኑ ላይ ተነስቶ፤ ኢሳያስ ደግሞ ዙፋንዋን ሲመለከት በታይምስ መጽሄት ላይ የተቀነባበረ ፎቶና ጽሁፍ። በለንደን ፕሮፌሰርን ጨምሮ ኢሳያስን  ያነጋገሩት ሽማግሌዎች ያሉት «በወድማማችና በእህትማማቾች መካከል የተደረገው ጦርነት አለቀ። አሁን በሰላም አንድ አገር መስርተን እንኑር ነው።» ኢሳያስ ግን “እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም” ብሎ ስላለ፤ ሽማግሌዎቹም አፊን በዳቦ ብለው፤ «ኢትዮጵያዊ አይደለሁም በማለትህ ትልቅ የታሪክ ስተት ሰርተሃል» በማለት እርማቸውን አውጥተዋል።
2.1 በወቅቱ ስለ ወያኔ የወታደራዊና የፖለቲካ አቅም ብዙ ግንዛቤ ባለመኖሩም የሻእቢያን ሃይል የማግዘፉ ሁኔታም ነበር። ወያኔ ኢሳያስን እንደ ፕሬዜዳንት ሊቀበል ይችል ነበር? ይኼ ጥናት የሚስፈልገው ጉዳይ ነው። እንለፈው።
2.2 ፕሮፌሰሩና መለስ ዜናዊ አልተገናኙም ማለት አስገራሚ ነው። ድፍን ጦቢያ የሚያውቀው በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ውይይት ማካሄዳቸውን ነው። ፕሮፌሰሩ እንደውም በአጋጣሚው ‘አማራ’ የለም ብለው በመናገራቸው ብዙ ተገቢ ወቀሳ ደርሶባቸዋል።
ፋይሉ አሁንም ዪ-ቲዮብ ላይ ይገኛል። አማራ የለም ያሉበት ምክንያት ምናልባት ብዙዎች እንደሚሉት፤ «አለ ተብሎ የተፈጠረን ጠላት የለም ሲባል ኢላማ ያስታል» ከሚል እሳቤ ቢሆንም፤ መሬት ይቅለላችውና ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እዳሉት፤ «የአማራ ጠላቶች ግን አማራ የሚሉትን ለይተው ለማጥቃት ሲቸገሩ አላየንም።» በዚህ እልቂት ‘አማሮች’ ያልሆኑ መጨፍጨፋቸው የተረጋገጠ ነገር ነው። ስለዚህ በአፍቅሮተ ኢሳያስነት የተለከፍከው ለኦነግ ልብህን በመስጠትህ በመሆኑ የተሰነዘረብህን ትችት፤ በዳንኪራህ ውስጥ ፕሮፌሰር መስፍንን በመደንጎር ማንንም ግራ ልታጋባ አትችልም! ኦነግ ነህ።
3. አፈንዲ ጎሰኝነቱንና የመገንጠል ረቂቅ አላማውን ሲያስፋፋ ...«ፕሮፌሰር መስፍንን በአካል ያየሁት[ያየኋቸው] ሁለት ጊዜ ያህል ብቻ ነው፡፡ በነዚህም ጊዜያት ከመጨባበጥ በቀር ሌላ ነገር ማውጋት አልቻልንም፡፡ ብንጨዋወት እንኳ በፖለቲካ አመለካከታችን የምንግባባ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ እሳቸውኢትዮጵያ ውስጥ ነገዶችና ጎሳዎች እንጂ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የሉም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንድ ብሄር ብቻ ነውነው የሚሉት፡፡ እኔ ግንበኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ፤ ነገድና ጎሳ የብሄር ቅርንጫፎች እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ህዝቦች አይደሉምነው የምለው፡፡ በሌላ በኩል ፕሮፌሰር መስፍንየብሄረሰቦችን መብት ለማስከበር በብሄር መደራጀቱ ለሀገር አንድነት አደጋ አለውየሚል እምነት አላቸው፡፡ እኔ ግንለመጥፎ ዓላማ እስካልሆነ ድረስ በብሄር መደራጀቱ መጥፎ አይደለምየሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላም ብዙ ልዩነት ማስቆጠር ይቻላል፡፡»
3.1 በመጀመሪያ ፕሮፈሰር መስፍን አሉ የተባሉት ነገሮች የጽሁፍ ይሁን የቃል ዋቢዎች አልቀረቡልንም። ግድየለም፤ አፈንዲን እንመነውና እርሱ እንደነገረን ፕሮፌሰሩ ብለዋል ብለን እንቀበል። ምክንያቱም ቁምነገሩ በአመለካከት መለያየታቸው አይደለም። ዋናው ሊጤን የሚገባው ነገር ግን፤ «ብንጨዋወት እንኳ በፖለቲካ አመለካከታችን የምንግባባ አይመስለኝም፡፡» የሚለው ነው።  ይኼ አባባል በአንድ በኩል የአፈንዲን ጀቢሌነት(/ጥጃነት/ለጋነት) የሚይሳይ ሊሆን ይችላል። በተቃራኔው ደግሞ እንደ ጭራሮ የደረቀ የፖለቲካ አቁዋሙን የሚያመላክት ነው። የጀብሌነቱ ነገር ብዙ አያሳስብም። ሁሉም የሚያልፍበት መንገድ ነውና። ማንም ቅን ሰው እንደሚገነዘበው፤በአንድ አገር ውስጥ የሚነሱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን ለመፍታት፤ መንጫጫት ሳይሆን፤ የሰከነና የጠለቀ ውይይቶች ማካሄድ ያስፈልጋል። ከልብ ከሆነ፤ በውይይቶችም ተሸናፊ፣አሸናፊ ወይም እኩል ሊወጣ ይቻላል። ብዙ ትምህርት ይገበያል። ፕሮፊሰር መስፍንም ደግመው ደጋግመው፤ “ሃሳቦች መፋጨት አለባቸው” ይላሉ። አፈንዲ ከፕሮፌሰሩ ጋር በብሄረሰብ ጥያቄ ላይ  ለመወያየት አይደፍርም። ስለዚህም ነው ገና ሳይወያይ የምንግባባ አይመስለኝም ብሎ እንዳልተገራ ፈረስ የሚፈረጥጠው። ለነገሩ ፈርጣጩ  ወይም ውይይትን የሚቦካው አፈንዲ ብቻ ሳይሆን ድፍን የጎሳ ጭፍራ መሪ ነው። ለምን? እንዴ! ጎሰኛ በውይይት ከተረታና የጎሳው ቀመር ብትንትኑ ከወጣበት፤ የየራሱን ትንንሽ መንግስት ለማቁዋቁዋምና ሚኒስቴር ሆኖ፣ቪላ ቤት እየኖረ መርሴዲስ ለመንዳት የሚያልመው ህልሙ እንዳይተንበት ስለሚሰጋ ነዋ! ከዚህ በመነሳት የምንረዳው የአፈንዲ ሚና እንደ ኢትኖግራፈር ልዩነትን በማንቦርቀቅ፤ እንደ ጎሳ ፖለቲከኞች ደግሞ ውይይትን በመሸሽ፤ ኢትዮጵያ ፈርሳ በአፍሪካ ቀንድ እንዲፈጠሩ ለታሰቡት አገሮች ጥርጊያ መንገዱን አዘጋጅ መሆኑን ነው። የአፈንዲ ፍቅረኛ፤ የሻእቢያው ተላላኪ ተስፍዬ ገብረእባብም በስደተኛ ጋዜጠኛ መጽሃፉ ላይ ያደረገው ይኸንኑ ነው። ግጥምጥሙ አሰደናቂ ነው።
3.2 ከፍ ሲል በጥቅስ እንደተመለከተው፤ አፈንዲ የብሄረሰቦች መደራጀት ለጥሩ ነገር እስከሆነ አስከፊነት የለውም የሚል አስቂኝ ነገር ጽፎአል። ይኼ አመለካከቱ የጀብሌነቱ ነጸብራቅ ነው ብለን እንራራለት። ከዚያም እርሱ እዛው አጠገቡ ሆኖ ያላጤነውን፤ የብዙ ‘የብሄርና ሕብረብሄር’ ድርጅቶች ስብስብ ወይም መድረክ በሚባለው ዙሪያ ያለውን ችግር እንደ ምሳሌ እናንሳ።
3.3 በቅርቡ በኢሳት ቴሌቪዝን ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ እንደተናገሩት፤ በመድረክ ስብሰብ ውስጥ ለሚቀጥለው አመት በሚደረገው ‘አገራዊ’ ምርጫ፤ እጩዎችን በመደልደል ላይ በብሄርና በሕብረብሄር በተደራጁ ድርጅቶች መካከል አለመስማማት አለ። ብሄረሰቦች በአካቢያቢያቸው የመወደደር መብት የእነርሱ ብቻ መሆን እንዳለበት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ይኼን የሚሉት ከሜዳ ተነስተው አይደለም። ሲመረጡ ከፍ ሲል የተጠቀስናቸውን ጥቅሞች በማሰላሰል ነው። አለበለዚያ ‘አማራ’ ተመልሶ ይመጣብናል ብለው ይሰጉ ይሆን? በመሆኑም አሁን መድረክ ውስጥ ሕብረብሄራዊ ድርጅቶች አብረው አንድ ላይ ካልሰሩ በስተቀር፤ ተቃዋሚ ነን የሚሉ የብሄረሰብ ድርጅቶች ከአለው አገዛዝ የተለየ የፖሊሲ አማራጭ እንዳላቀረቡ እንረዳለን። እዚህ ላይ የክልሎችም ሕገመንግስት፤ ክልሉ የተወሰኑ የብሄረሰቦች፤ለምሳሌ ጋምቤላ የኑዌር፣የአንዋክና ደግም አንድ የሌላ  ጎሳ ብቻ እንደሆነ ነው የሚደነግገው።

እንግዲህ አፈንዲ፤ ብሄረሰብ የኢትዮጵያዊነትን የዜግነት መብት እየገፈተረው እንደሆነ  እያጤነው፤ ምኑን ነው በብሄረሰብ መደራጀት ጥሩ እስከሆነ ድረስ የሚለን? ለዚህም ነው የአፈንዲ ሙተኪ ተልእኮ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የበኩሉን ኢትኖግራፊያዊ አስተዋጽኦ ከኦነግ አለቃ ሻእቢያ ጋር ሆኖ መግፍት ነው የምንለው። ወጣቱ በዚህ የወርቅ-ቅብ፣መርዘኛ ብእር ጊንጥ ሸር እንዳይሳሳት  ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል።
 ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንዲሉ፤በዚህ የኢትዮጵያ ታሪክ አስቸጋሪ ወቅት፤ በዩሉኝንታ፤ ሰውን አስቀይማለሁ ብሎ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ምንም ተሳትፎ የማያደርግ ሰው ከታሪክ ተጠያቂነት አይድንም። ወጣቱ እንደነ እስክንድር ነጋ፣ርእዮት አለሙና የመሳሰሉት ጀግኖች፤ከጎሳ ስሜት፣ከመጥፎ ሱሶችና ርካሽ ዘመናዊ ባሕሎች ራሱን ነጻ አውጥቶ፤ ኢትዮጵያ የልጆችዋ ሁሉ እንድትሆን የማድረግ ግዴታ፣አቅምና መብት እንዳለው በመገንዘብ ከአሁኑ 10 ጊዜ የበለጠ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት። ይኼን ሳያደርግ ቢቀር፤ በአገሩም ሆነ በቅርቡ በአረብ አገር እንደየው እጣ ፈንታው፤ ውርደትና ባርነት ሆነው መቅረታቸውን መገንዘብ አለበት።

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!