በጄ… አምቼ… የቢሾፍቱ አስካሪ!



ክፍል አንድ፤
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው የሚያድጉ መረብ-ምላሴዎች፤ “አምቼ” እንደሚባሉ በተስፋዬ ገብረአብ የተደረሰውን፤ ‘የስደተኛው ማስታወሻ’ ካነበብኩ በሁዋላ ነው ያወኩት። ኢታሊያ አገር ግን ሁሉም ‘አስካሪ’ ናቸው።
1.   እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር(እ.ኢ.አ) እንጂ እንደ ግእዝ አቆጣጠር(ግአ) ብዬ በመጻፍ የኢትዮጵያን ስም በአማርኛም ሆነ በሌሎች ቁዋንቁዎች ስነጽሁፍ ውስጥ እንዲሳሳ አልተባበርም። የቢሽፍቱ አስካሪ አንዱ ሴራ ኢትዮጵያ የሚለውን ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ እንዲደለዝ ማድረግ መሆኑን በአዲሱ መጻህፉ እ.ኢ.አ የሚለውን በግ.አ በመተካት አሳይቶናል። የፈረንጆቹ መጽሃፍ ቅዱስም እንዲሁ የኢትዮጵያን ስም በመፋቅ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ግን እንደ ተዳፈነ ረመጥ ናት። አትጠፋም። 
2.   ታዲያ እ.ኢ.አ በ1978 ነበር። የቦሎኛ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ። ከእኔ ጋር የሚማሩ ራሳቸውን አንዴ ኤርትራዊ፤ አንዴ ኢትዮጵያዊ፤ ደግሞ ዝቅ ሲል፤ ከአገው ምድር የፈለስን ነን የሚሉ ቢለኖች(ከወሎ ነው የተሰደዱት-- ሴቶቹ ከወሎየዎች አይለዩም፤ ውቦች ናቸው)፤ ሃማሴኖች፣ በጀብሃና በሻእቢያ በተደረገው ውጊያም የተረፉት የጀብሃ ተጋዳሊያን ከሶሪያና ከአማን ወደ ኢጣሊያ የመጡም ነበሩ። ከእኔ ጋር በአማርኛም ሆነ በኢታሊያንኛ እንግባበለን። መጻሕፉት እንዋ’ሳለን። ሊሬም እንበዳደራለን። አብረን እንበላለን። እንጠጣለን። አመትባል ሲሆን ቤተስቦቻቸው ጋር ሄጄ  እውላለሁ። ወደ ቦሎኛ አመታዊ ፊስቲቫላቸውም ከከረኑ ልጅ ሃይሌ ጋር እንሄድ ነበር። ከመሃል አገር ተማሪዎች የነበርነው ሁለት ብቻ ስንሆን አንዱ እ.ኢ.አ በ1979 ሞተ። ሙዋቹ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ቁዋንቁዋ አጥንቶ የመጣ ስለነበር ብዙ የኢታሊያውያን ጉዋደኞች ነበሩት። ኑሮ ተስማምቶትና አለጥልጦ ነበር የማየው። ትምህርቱን ግን ችላ ብሎት ነበር። አሙዋሙዋቱን ሥሰማ ግን በጣም አዘንኩ። ተሰቅሎ ነው የተገኘው። ይሁን እንጂ ራሱን መስቀሉ አጠያያቂ ነው። ከጀርባው በጩቤ ተወግቶ እንደነበር አስከሬኑን በእርግጠኝነት ሙዋቹ መሆኑን ለፖሊስ ያረጋገጠው ሰው ነግሮኛል። ወዲያው አስከሬኑን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ፤ መዋጮ ተደረገ። መረብ ምላሴዎች 15 ሚሊዮን ሊሬ አዋጡ።  የገንዘብ አባሰቡ ለሙዋቹ ጸሎት ከተደረገ በሁዋላ በSanta Saragozza በሚባል የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ነበር የተካሄደው። ቄሱ በነገሩ ተገርሞ፤ “ጦርነቱ ቢቆም፤ ይህ ሕዝብ እንዲህ የሚተሳሰብ ከሆነ ለምን ይከፈላል? ባሕሉ አንድ ስለሆነ አንድ ላይ ነው መኖር ያለበት አሉኝ።” “እርግጥ ነው አባቴ አልኩአቸው።
3.   ብዙዎች መረብ-ምላሴዎች በዚያን ጊዜ የሚደግፉት  የራስ ገዝ አስተዳደርን ነበር። ጥቂቶች መገንጠልንም የሚደግፉ ነበሩ። ዛሬም ‘ከናፃነት’(ከኢሳያስ ባርነት) በሁዋላ ፕሮፌሰር ተክሰተ ነጋሽ እንዳሉት፤ መረብ ምላሴዎች አንድነት እንደሚሻላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። እንደውም ድሃው ኑሮው እጅግ ስላንገፈገፈው፤ የደርግ ስርአት ይሻለኝ ነበር ማለቱን በቅርቡ አስመራ ሄደው የተመለሱ ሰዎች በፓልቶክና በዩቲዩብ ካሰራጩት መረጃዎች መረዳት ይቻላል። አገረኛው የደርግ ዘመንን የተመኘው፤ደርግ ጊዜ ቢያንስ የቤት ኪራይና ሸመት ዋጋቸው እንደዚህ እንደዛሬው ውድ ስላልነበሩ ነው። የቢሸፍቱ አስካሪ ግን ዛሬ “የኤርትራን አንድነት በሚመለከት ማንም ኤርትራዊ ልዩነት የለውም” ሲል ሊያብለን ይከጅላል።
ይሁንና ራሱ ስለ ጄኔራል ታሪኩ ባቀረበው ጥሩ ትንታኔ፤ጄኔራሉ ያቀረቡት የሰላም መንገድ ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ለሁለቱም አገሮች በሚበጅ መንገድ የኤርትራ ችግር ሊፈታ ይችል ነበር ደግሞ ይለናል።
ይኸ ማለት መረብ-ምላሴ ላትገነጠል ትችል ነበር ማለት ነው። ከፍ ሲል ማንም ኤርትራዊ ከኢትዮጵያ ጋር ለመዋሃድ አይፈልግም ያለውን ረስቶ፤ ኤርትራ በመገንጠልዋ ጉዳት እንደደረስ በተዘዋዋሪ መቆጨቱን ራሱ በጄኔራል ታሪኩ ታሪክ ስር አድፍጦ ሲነግረን እኛን ያሞኘ ይመስለዋል መሰለኝ።
እርቦህ እንደሆነ ገብቶናል!! ወዲያና ወዲህ ከመግደርደር፤ ራበኝ አገሬ! ኢትዮጵያዬ ማሪኝ!! ብሎ ድንጋይ ተሸክሞ መለመን እኮ ደፋረነት ነበር ጃል! አልፈህ ተርፈርህ ሆላንድ መሽገህ ለሻእቢያ ከመሰለል።
4.   ለመጀመሪያ ጊዜ አስካሪ(Askari) የሚለውን ስም የሰማሁት እ.ኢ.አ በ1981 ከአንድ የኢታሊያዊ ሃብታም ጉዋደኛ ነው። አማርኛም ይሁን ኢታሊያንኛ መናገር እንጂ መጻፍ የማይችል ገብረእግዚ የሚባል ኤርትራዊ ነበር። ከስራ ተባረረና (የጉልበት ስራ) የስራ መፈለጊያ የሚሆነው ጥሩ ካሳ አገኘ።
5.   አጅሬ ገንዘቡን እጁ ካደረገ በሁዋላ የጭነት መኪናዎች ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ፈለገ። ትዳር ይዞ አንድ ወንድ ልጅ ቢወልድም፤ተፋትቶአል። ታዲያ ገብረእግዚ እቅዱን ለማሳካት፤ አማርኛና ኢታሊያንኛ የሚጽፍና ሁነኛ ሚስጥረኛ ሰው ይፈልጋል። ወደ አዲስ አበባ መመለስ ማሰቡን ማንም እንዲያውቅ አይፈልግም። የማጠናበት መጻሕፍት ቤት መጣና፤ ቡና ጋበዘኝ። አማርኛው ጥሩ ነው። ግን የኢትዮጵያን ኤምባሴ ፓስፖርት ለመጠየቅ ማመልከቻ መጻፍ አይችልም። ሌላ ሰውም ምስጥሩን እንዲያውቅ አይፈልግም። “ እኔ አሁኑኑ ልጽፍልህ እችላለሁ ይኼ ደግሞ ምን ችግር አለው አልኩት።” … “አደራ ለሰው እንዳትናገርብኝ” አለኝ። እነሆ ዛሬ ገና መተንፈሴ ነው ከ27 አመታት በሁዋላ። በመጀመሪያ ግን ኢትዮጵያ ኤምባሴ ደውዬ የኤርትራ ተጋዳላይ እንደነበርና አዲስ አበባ በሰላም ቢመለስ ችግር የማይገጠመው መሆኑን በስልክ እንዳጣራለት ለመነኝ። በማግስቱ ተቃጠርንና ኤምባሴ ደውዬ ጉዳዩን አስረዳሁ። ምንም ችግር እንደማይገጥመው፤ ማመልከቻውን እንደጽፍለት ምክር ተሰጠኝና ሁለት ፎቶና ለፓስፓርት የሚከፈለውንም ገንዘብ ይዞ እንዲመጣ የተነገረኝን ነገርኩት።
6.   በሌላ ቀጠሮ ደግሞ ከኢትዮጵያ መጥተው መኪና ለመግዛት የሚፈልጉ ሰዎችን በአስተርጉሚነትና በጽሁፍ በሚደረገው ውል እረዳቸው እንደነበር ያውቃልና(አንድ ቀይ ፈራንክ ተቀብዬ አላውቅም) አጋዛኝ አለኝና ሄድን። እንዳጋጣሚ ከአንድ የመኪናው ሺያጩ ጉዋደኛ ጋር ተዋወቅን። ተማሪ እንደሆንኩ ነገርኩት። ስለ ሙሶሎኔ ጦርነት አንስቶ ኤርትራ ዘመቶ እንደነበር ነገረኝ። “አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር ልንገርህ ... እየሳቀ… የአስካሪ እግር…ካ!ካ!ካ! ” ይስቃል ከልቡ! “እግራቸው ያልተማረ ነው። እንደ ማጭድ ነው። ስለዚህ ለጫማ አይሆንም!” የእኛ ግን የሰለጠነ ስለሆነ ጫማ ስለምናደርግ ከብዙ ተላላፊ በሽታና አደጋ ራሳችንን መጠበቅ እንችል ነበር” አለኝ። ምንድነው አስካሪ አልኩት? ጥቁር የሙሶሊኒ ወታደሮች እንደሆኑ ነገረኝ። እንዴት ማሸፌያ ሆን ብዬ ፈገግ በማለት ወሬ ለወጥኩ። ባላቤቱ ሁኔታዬን ተረድቶ ነው መሰለኝ፤ “ይኼ የኔ ጉዋደኛ ነው። አፉ ግን ባለጌ ነው። አንተ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ስለሆንክ በእንደዚህ ያለ አፍ እላፊ ቅር ይልሃል ብዬ አላስብም” አለኝ። ይኼ ንግግሩ ግን የባሰ ስላስቆጨኝ ከእንግዲህ ወዲህ ከእርሱ መኪና ለሚገዙ ሰዎች አላስተረጉምም ብዬ ወሰንኩ። በጣም ሆዴ ተቀየመ። ኢታሊያዊ እንደ አምቼ፤ አማራ፣ትግሬ፣ ኦሮሞና ወዘተርፈ አይለይም። ሁሉም አስካሪ ናቸው ለርሱ! ኮሎኔያሊዝምን ተጠየፍኩት። ገበረእግዚ መኪናውን ከገዛ በሁዋላ አይቼው አላውቅም። ስሄድም ደህና ሁን አላለኝም። ቦሎኛ ውስጥ ጠፋ ተባለ። ምናልባት አረብ አገር ሄዶ ይሆናል ይባልም ነበር። አጅሬ ግን መሄዱን ለልጁ እናት ነግሮአት ነበርና፤ አንዴ በወሬ ወሬ ተነስቶ አዲስ አበባ ገብቶ ‘አማራ’ አግብቶ፤ አንድ ሴት ልጅ ወልዶ ተመችቶች ይኖር እንደነበር ከርስዋ ከራሰዋ ሰማሁ። እኔ ግን የተጫወትኩትን ሚና ታውቅ እንደሆን እስከዛሬ አላውቅም። እንግዲህ ገብረእግዚ የተመለሰው የራሱ የወደፊት እጣ ከቦሎኛ ይልቅ አገሩ እንደሚሻለው አውቆ ነው።
ገብረእግዚ ለምን እኔን አማራውን አመነኝ? እንደሚመስለኝ ለሻእቢያ አሳልፊ እንደማልሰጠው ቢተማመን ነው። ዛሬ ቢያንስ ወደ 75 አመት ይሆነዋል።  ይኼ ታሪክ በአጼ ምንይልክ ጊዜ የሆነ አይደለም። እንደ ትናንትና የሚቆጠር ነው። መረብ-ምላሴዎች አማራ ነው?ኦሮሞ ነው? የሞተው ብለው እንባቸውን ማቆም አልቻሉም። አለቀሱ አስከሬኑንም ገንዘብ አዋጥተው፤ የሙዋቹን ዘመድ ወ/ሮ ሙሉን ከአዲስ አበባ ተቀብለው ሽኝዋት። የሕዝቡ ታሪክ በስደት እንኩዋን እንዲህ ነበር።ዛሬስ?በእነ አምቼ እየታመሰ? በቡርቃ ዝምታ ሽልማት እየተመንሸነሸነ።

ክፍል ሁለት፤ እንዴት ነበር የኖርነው? ጋላ፤ጋሌጃሬ….
7.   …«የቡርቃን ትዝታ ከመጻፌ በፌት በአስመሮም ለገስ ስለ ገዳ ስርዓት የተጻፈውን ማንበብ ነበረብኝ» ብሎ በጋዜጠኛው ማስታወሻ ላይ ተስፋዬ በመጻፉ፤ ወደፊትም በሚጽፋቸው መጻሕፍት ላይ በተለይ ታሪክን በተመለከት ቢያንስ ከግራኝ በሁዋላ እንኩዋን ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ በሚገባ ጊዜ ወስዶ እንዲያጠና በኢ-ሜል መክሬው ነበር። እርሱ ግን ግቡ ሌላ ነውና ዛሬ ደግሞ ጫልቱን ይዞ ብቅ አለ። ያስነሳውን የፌስቦክ አቡዋራ በተቻለ መጠን አለፍ አለፍ እያልኩ እፍ እፍ ብዬዋለሁ። እቅጩን እንጋገርና ተስፋዬን በዚህ ጉዳይ ላይ የደገፉ በሙሉ ከጎሳ ስሜት ያልጸዱ ናቸው። ስለጫልቱ ሲጽፍ አንድ አግጦ የወጣ ውሸት አለ። ገበያ ሄዳ ስትገበይ የጠራ አማራኛ አለመናገርዋን ያጤነው ነጋዴ. “ጋላ ነሽ እንዴ?” ሲላት፤ ከገላን ነው እንዴ የመጣሸው? ማለቱ ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ተይዛ አክስቱዋ እንዳብራራችላት የከተበው፤ነው። ይሔ ቅጥፈት ነው። ለፈጠራም የማያመች ጅልነት ነው። ምክንያቱም ኦሮሞ ሆኖ የጋላን ቃል የማያውቅ ሊኖር በጭራሽ አይችልምና። ኦሮሞ ልጁን እንደ ጉዋደኛው ስለሚያየው እንኩዋን ይህቺንና ሌላም የሚደብቀው ነገር በጨራሽ የለም። በአብዮቱ ጊዜ መኮም ስለ ጋላ ዘፍና አብረን ጨፍረን ነበር፤
“ገደልን ተንደርድረው አይወርዱትም፤
“ገደልን ተንደርድረው አይወርዱትም፤
ቅማላም ጋላ ማለት ሁለተኛ አይመለስም።
8.   የአገሬ ኦሮሞዎች ለልጅ የሚሰጠው የነጻነት ገደብ አስደናቂ መሆኑን ከአንድ የልጅና የእናትን ውይይት እንመልከት፤
ራቢያ፤ “ሐሰን እስኪ ባክህ አማርኛ አስተምረኝ፤”
ሐሰን፤ ”እሺ እ.ስ በይ? መጀመሪያ ትርጉሙን በኦሮምኛ ንገረኝ”
ሐሰን፤ ”..ዋን ከን.ላቲ’’!። እናት ምንም አልተቆጣችም። “አንተ ባለጌ ብላ ሳቀች”! ሊሎቻችንም ተከትለናት ሳቅን! አዋቂ ሲያወራ ልጅ ወደ ውጭ ብሎ ነገር የለም በኦሮሞ።
9.   አንዴ ቦሎኛ ከፓሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት Cafe Galla የሚል አየሁና ጎራ ብዬ ቡና አዘዝኩ።  ባለቤቱን Galla ማለት ምን ማለት ነው አልኩት? ምናልባት ከሙሱሊኒ ጋላ ግዛት ጋር ዝምድና ይኖረው እንደሆነ ብዬ ነበር። “ጋላ ማለት፤ በሰው ትከሻ ላይ የሚኖር” እንደማለት ነው አለኝ። ወዲያው ገባኝ፤ Galleggiare ማለት መንሳፈፍ(በውሃ ላይ) ማለት እደሆነ አውቅ ነበርና። በእኛ አገር፤ “የአንድ የነገድ ስም ነው” ስለው ከት ብሎ ሳቀና “የደላው ነው በለኛ!” አለኝ። “ተወኝ ባክህ እዚያ አገር የደላው ለገዢዎች ብቻ ነው” ብዬ ወጣሁ።
10. መሬት ይቅለለውና፤ እ.አ.አ በ1995 በጋው ላይ ሎሬት ፀጋዬ አምስተርዳም መጥቶ ነበር። በእግራችን ከተማውን አስጎብኘኝ ብሎ ቀኑን ሙሉ ሳዞረው ዋልኩ። አንዳንዴ አረፍ ብለን ሻይ ቡና እንላለን። ለበሽታው ማስታገሻ፤ ስኩዋር አልፎ አልፎ ይቅማል።  ፓለቲካውን መቼም ኮመኮምነው። የኮሎኔል ጎሹ ወልዴ መድሕን ድርጅት ነበር በወቅቱ በስደት ገኖ የነበረው።
ታዲያ ጎሹና የኦነጉ ኢብሳ ጉተማ በአንድ አምስተርዳም መድረክ ላይ ተገኝተው ስላደረጉልን ገለጻ ነገርኩት። በተለይ ኮሎኔል ጎሹ አቶ ኢብሳ ስለ ብሄረሰብ ጥያቄ አንስተው በተናገሩት ላይ “አቶ ኢብሳን ደርግ አስሮአቸዋል። ስብአዊ መብታቸው መገፈፉ ያሳዝናል። ይሁን እንጂ የብሄረሰብ ጥያቄ የሚባለው ውሸት ነው። እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። በደምና በባሕል ተዋህደናል። ቁንቁዋውም የሁላችንም ነው። ችግራችን ድህነትና ሁዋላ ቀርነት” ነው ያለውን ነገርኩት። ጋሼ ጸጋዬ….” እውነቱን ነው ጎሹ፤ ኦነግ የጥላቻና የመገንጠል ፖለቲካ ነው የሚያራምደው። ለምሳሌ ጋላ አትበሉኝ ፈሊጥ ከፍተኛ ድንቁርና  ነው። እኔ ጋላ ነኝ። ክፋት እኮ የለውም። ጋላ ማለት እኮ እምቢ/አሻፈረኝ የሚል ማለት እኮ ነው! አንድ ባለጌ ከቃሉ ፊት ይሁን ሁዋላ ብልግና ይሁን ንቀት ቢዶልትበት የናቂውንና የባለጌውን ማንነት ድንቁርና ያሳያል እንጂ የማንነትህን መለያ፤ ጋላነትህን ሊያስተውህ ይገባል? አሁንማ በታሪክ ሁሉ ጋላ ተብሎ የተጻፈው ኦሮሞ እየተባለ እየተለወጠ ነው። ይህ ራስን መካድ ነው። በአገራችን ሚስቴ/ባሌ ጋላ ናት፤ጋላ ነው ይባላል። ጋላ አገር ለንግድ ሄድዋል ይላሉ እስከዛሬ ጎንደሮች።” … “ጃንሆይስ ቢሆኑ? አብዛኛው ደማቸው ጋላ ነው። ጴጥሮሥ ግማሽ ጎኑ ጋላ ነው።’’። ፍየል ከመድረስዋ ቅጠል መበጠስዋ እንዲሉ፤  ሕግ ከተማረ በሁውላ ወደ እውነተኛው ዝንባሌው ሄዶ የጠለቀ እውቅት በማካበትና በማስተማር የሚያወቀውን የሎሬትን ፀጋዬን ስራ ምንም ሌላ ማስረጃ ሳያቀርብ..”የቃላት ጫወታ” ብሎ ማጣጣሉ ስራው ሁሉ ከተንኮል ውጭ የሚመንጭ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ከመሆኑም በላይ፤ በሁሉን አውቃለሁ  በሚል ድፍረትና እብሬት መወጠሩን አሳይቶናል።
11. አምቼ፤ “ኦሮሞን በኦሮሞ መምታት የተለመደ ነው” ሲል በቀባጠረው ውሽት፤ አንድ እራሴ የማውቀውን ሃቅ አዛብቶአል። “ዋቁ ጉትን በጃጋማ ኬሎ ማስመታት የሚል።” ጃጋማ ባሌ እንደራሴ ሆነው የተሾሙት የነዋቆ ጉት እንቅስቃሴ ከተፈታና ጃንሆይ ባሌን ጎብኝተው ከተመለሱ በሁዋላ ነው። በእርግጥ ጃጋማ ኬሎ በባሌ በተለይ በደሎ፤መሽገው የነበሩትን የዋቆ ጉቱ የቀኝ እጅ አማጽያን፤ ሐሰን ቱሬ፣ከዲር ዋቆ፣በከር ሃጂንና የመሳሰሉትን በሰላም እንዲገቡ፤ ጉቦ አልፈልግም! አሻፈረኝ ብሎ የሰው ተወዳጅነት ያተረፈውን የካሣዬ ምሕረቴ ደፋርነትና ረዳትነት በማግኘታቸው፤ አማጽያኑ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ትልቅ ስራ ሰርተዋል። ጃጋማ ደሎን በተለይ በአረና (አረና ትግራይ ፓርቲ አይደለም፤ አፈንዲ ሙቲም ስለ ጠባቡ ኦነግ ጥብቅናውን ተወት አድርጎ አረና በአፋን ኦሮሞ ምን እንደሆነ ቢያስረዳን መልካም ነው) ጫካ ውስጥ የሸፈቱትን አማጽያን በሃይል የመደምሰስ ስልጣን ቢኖራቸውም፤ ከላይ እንደጠቀስኩት የሰላሙ ጉዳይ ስለተሳካ ተጨማሪ ደም ከመፋሰስ ሊዳን ችሎአል። ይህን ታሪክ፤አቶ ስዩም ሰርፀ መድህንም ጽፈውታል። ልጃቸው ለንባብ እንደምታበቃው ተስፋ አለኝ።
12. አንዱ ቀንደኛ ሽፍታ ከዲር ዋቆ ነበር። ከዲር ዋቆ እጁን ከሰጠ በሁዋላ ከደሎ ወደ ጎባ ሲመጣ የሚያደርው እኛ ቤት ነበር። የምንተኛውም ከእኔ ጋር አንድ አልጋ ላይ ነበር። እስላምም ቢሆን ጠጅ ይወዳል ። ሞቅ ሲለው፤….” ካሣዬ እንቅልፌ መጣ?” ይለዋል። “እንቅልፍህ መጣ በል ጋሽ ከዲር”! እንለውና ከት! ከት! ብለን እንስቃለን!!። እኛ ልጆች ነን።  ግን..” የእኔ አባት ኦሮምኛ ሲያወራ… ከዲርም ያርመውና ፍርፍር ብሎ…እንባው ጠብ እስኪል ነበር የሚስቀው”።
13. ጃጋማ ኪሎ የባሌ እንደራሴም ሆነው ብዙ አልሰሩም። ከፍታውራሪ አበበ አሻጋሪ የገዙትን ኩታ ገጠም የቡና መሬት ለመረከብ በሄሊኮፕተር ወደ ደሎ ሄደው ነበር። ሄሌኮፕተርዋ ተከሰከሰችና አሻጋሪ ሕይወታቸው አለፈ። ጃጋማም በደረሰባቸው ከፍተኛ ቃጠሎ ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና መሄድ ነበረባቸው። ከዚያም በሁዋላ አልተመለሱም።
14. ጃጋማ ፤ የባሌን ዋና ከተማ ጎባን ወደ ጎሮ ለማድረግ አስበው፤ ተቃውሞ ስለበዛባቸው አልገፉበትም። ኸረ ለመሆኑ የባሌው አመጽ መነሾው ምንድን ነበር? አፈላማ!!

15. ተስማ ኢላላ ይባላሉ የመዘጋጃ ቤቱ ሹም። እርሳቸው መሬት ላይ አንድ ከብት ዝር ካለ፤ የአፈላማ ከፍሎ ነው ከብቶቹን ማስለቀቅ ያለበት። አንዴ ከአባቴ ጋር ሄድን የኛን ላሞች ለማስለቀቅ። አባቴ ለመክፈል ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ተሰማ አላስከፈሉትም። ምናልባት የታጠቀውን ኮልት ከግንዛቤ አስገብተው ነገር ለማብረድ ያደረጉት ይመለኛል አሁን ሳስበው። አይወዳቸውም ነበር። ገፋፊ፤ አፈር ይብላና! ይላቸው ነበር ቀንና ማታ።
16. የባሌው ፓፓስም ከደሙ ንጹህ አልነበሩም። አቡነ መርቆርዮስ የሚባሉ የኤርትራ ትግሬ ነበሩ። ጥሬ ስጋ በመብላት ተወዳዳሪ አልነበራቸውም እየተባለ ይታማ ነበር። ታዲያ የወቾን ገበሬ እያፈናቀሉ መሬቱን ለዘመዶቻቸው ማደል በመጀመርአቸው የአዝማች ዳግለሃን ተማሪዎች ተቃውሞ ስልፍ አድርገው ነበር። በስለፉ ላይ የተዘመረው እስካሁን ከጭንቅላቴ አልጠፋም፤
“አቡነ መርቆርዮስ፤ አቡነ መርቆርዮስ፤
እርኩስ አይሉህ ቅዱስ!እርኩስ አይሉህ ቅዱስ!
ከሁሉም የምትበላ! ከሁሉም የምትበላ!
ስላም አትል አማራ። ስላም አትል አማራ»

ክፍል ሶስት….
እንዴት ነበር የኖርነው?
ስለ አፈላማ እጽፍለሁ። ብዙ ነው። አሁን ግን አባባ ኡስማን አሳባ ናፍቀውኝ ነው። አገራቸው ባሌ-ጎለልቻ ነው። ታዲያ በመሬት ድንበር ውዝግብ ሙግት ውስጥ ገብተው ነበር። ዶሴአቸው ወደ ጎባ አውራጃው ፍርድ ቤት ተመርቶአል። ስንት ግዜ ጉዳያቸው በሆነ ባልሆነው ሰበብ ለሌላ ቀጠሮ እንደተላለፈ እርሳቸውም የሚያውቁት አይመስልኝም። አባባ ሙኑሸዋ ስጦታውም እንዲሁ ከአዳባ እየተመላለሱ በቀጠሮ ይጉላሉ ነበር። ሁለቱም ሰዎች ጎባ ሲመጡ የሚያርፉት እኛ ቤት ነው። እኛን ልጆቹን ግን በጣም የሚናፍቁን አባባ ኡስማን ናቸው። ካለ ነገር አይደለም። አባባ ኡስማን ጭኮ ይዘውልን ይመጣሉ! እቤት የሚሰራው አይጣፍጠንም እንደ እርሳቸው ጭኮ! ጥዋት ቁርስ ይሁን፤ ከሰአት በሁዋላ ራት እስኪደርስ ለመቅሰስ የርሳቸው ጭኮ እስኪያልቅ ሌላ ነገር እሺ ብለን አንበላም። ሽማግሌ ናቸው። የጎባን ብርድ አይችሉትም። ታዲያ ቶሎ ብለን ከስል እናያይዝና ድንክ አልጋቸው አጠገብ እናስጠጋለን። ወገቤን አመመኝ ስለሚሉ፤ ብዙ ግዜ እኔና እህቴ እየተፈራረቅን በቅባት አንገታቸውን፣ትከሻቸውን፣ ወገባቸውንና እግራቸውን እናሻቸዋለን። በጣም ነበር የሚወዱንና የሚመርቁን። አንዳንዴ እያሸናቸው እንቅልፍ ይዞአቸው ጭልጥ ይላል!
አንዴ ከሰላቸውን እየሞቁ ራት አብረን እየበላን…እናቴ... “ባለቤቶ ለመሆኑ ደህና ናቸው?” ብላ ጠየቀቻቸው።

አባባ ኢስማን የከሰሉን እፍም በጣታቸው እያሳየዋት…” እንደዚህ እንዳንቺ ከሰል የምትሞቅ ሌላ አግብቼአለሁ!” ብለዋት እርፍ!! እናቴ…”አፈር ብሉ እቴ”! አለቻቸው።..” ወላሂ ወላሂ!እውነቴን አሉ”!። እኛም በሳቅ ፈረስን!! በጣም እንወዳቸው ነበር። ወደ ጎለልቻ ሲመለሱ ቅር ይለን ነበር። እንደአያታችን ነበር የምናያቸው።

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!