መሬት ላራሹ!
አንድ ለመንገድ....
ወ/ሮ ታደለች ኃይለሚካኤል፤ በ“ዳኛው ማነው ?”[1]
መድብላቸው የመሬት ላራሹ መፈክር ለኩዋሸ፤ የትግራይና የወሎን ገበሬዎች ችጋር በለጋ እድሜው ያስተዋለውና የኪነ-ጥበብም ፍቅር የነበረው
ባለቤታቸው ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደሆነ ነግረውናል።
የመሬት ስሪት እንዲሻሻል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ
የነበረው የህግ መወሰኛ ምክርቤት፤ ለአንድ ሰው በይዞታ እስከ 90 ጋሻ መሬት(90*40 =3600 ሄክታር) መብለጥ የለበትም የሚለውን
ጣራ መቃወሙንም ይጠቅሳሉ። ማነሱ እኮ ነው ጃል! አስገራሚ ተቃውሞ ነው።
ደራሲዋ የመሬት ላራሹ፣የብሄረሰብና የዴሞክራሲ
ጥያቄዎች የተሳሰሩ ናቸው ይሉናል። የሆኖ ሆኖ እስከ ዛሬ በደርግ የታወጀው አዋጅ አራሹን በዘላቂነት የመሬት ባለቤት እንዳላደረገው፤ የወያኔ/ኢሕዴግ
ይሁን የቀጠለው የብልጽግና/ኦሆዴድ ስርአቶች መሬት የብሄረተኛ ኢሊቶች መበልጸጊያ እንዲሆን በማድረጋቸው የባለቤታቸው መሬት ላራሹ መፈክር በተግባር
እንዳልዋለ ያስረዳሉ።
የግል
መሬት እንደማንኛውም ቁዋሚ ንብረት የግል ካልሆነ፤
አራሹ ላቡንም ይሁን ጥሪቱን በመሬቱ ላይ አፍሶስ ምርታማነቱን ለማሳደግ ልቡ መንታ ነው የሚሆንበት። ነገ እፈናቀላለሁ ብሎ ይሰጋል፡፡ የመሬት ምርታማነት መጨመር በቀጥታ
ከግል ይዞታ ጋር የተያይዘ ነው የሚሉ ጥናቶች አሉ። የብዙ የአፍሪካ አገሮች የመሬት ስሪት በመንግስት ቁጥጥር ሥር ነው። መሬት በግል ይዞታ እንዲያዝ የፈቀዱት ምስርና ሞሮኮ የመሬታቸው ምርታማነት በመንግስት ይዞታ ስር ከተያዙት አገራት ጋር
ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው።
በመሬት ይዞታ ላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ደሳለኝ ራኽመቶ፤ የኢትዮጵያ ገዢዎች መሬት የግል ከሆነ ገበሬው ሽጦት ከተማ
በመግባት ስራፈት ይሆናል ብለው በማሳበብ መሬት ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር አይፈልጉም። ገበሬውን ለመቆጣጠርና ለማራቆት እንዲመቻቸው
‘የመንግስት’ ሆኖ እንዲቀጥል ነው የሚሹት ይላል። ደሳለኝ ገበሬው እንኩዋን መሬቱን አንዱዋን ጠቦቱን ለመሸጥ ስንቴ እንደሚያስላስል
ማወቅ ያስፈልጋል ሲል በገዢዎቻችን ስግብግብነት ያዝናል።
የመላው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ድርጅት(መኢአድ)
የመሬት ይዞታን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱትን
የፖለቲካ ድርጅቶችን ሰነድ አላገኘሁም። ይሁን እንጂ አንዴ የመኢአድ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኢንጄነር ኃይሉ ሻውል፤ በዚሁ ጥያቄ ላይ
ምላሽ ሲሰጡ፤ “መኢአድ አሁን ገበሬው ያለበትን ይዞታ፤ ወደ ግል ይዞታ አዛውሮ፤ ሙሉ ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥ ስርትፌከት ነው የሚሰጠው” ሲሉ አድምጪያለሁ። ይኼ መልካም ሃሳብ ቅንጀት
በምርጫ እንዳሸነፈው ስልጣን ቢይዝ ኖሮ ምርት ስለሚያደግ ለእንደዛሬው ያለ የከፋ ድህነት አንዳርገም ነበር።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት/አፋሕድ
የአፋሕድ አቁዋም በመሬት ይዞታ ላይ ምንድነው የሚለውን
ለመዳሰሰ ረቂቅ ሰነዱ ስላለኝ በጣም ተመችቶኛል። አፋህድ የኢትዮጵያን መሬት፤ የግለሰብ፣የመንግስት፣ የእምነት ተቁውማትና የህብረተሰብ ብሎ ከፍሎታል።
የግለሰብን በሚመለከት፤ የገጠርም ሆነ የከተማን መሬት የመሸጥ፣እንደ ቁዋሚ ንብረት አስይዞ ከባንክ መበደርም ሆነ
በውርስ ማስተላለፉንም ይፈቅዳል። በተጨማሪም መሬት በወታደራዊና በብሄረሶች ቁጥጥር ስር ከወደቀ ጀምሮ በተለይ የአማራው ህዝብም
ሆነ ሌላው ታታሪ ገበሬ ካለተመጣጣኝ ካሳ ንብረቱን ያጣበት፣የተፈናቀለበትና የተገደለበት ስለሆነ፤ጉዳዩን ልዮ ኮሚሺን አቁዋቁውሞ
በመመርመር አስፈለጊውን ካሳ እንዲያገኝ እንደሚያደርግም አስፍሮአል፡፡ ይኼ የከተማንም መሬትና ቤቶች ያጠቃልላል።
የመንግስት የሚላቸው፤ የመንግስታዊ ተቁዋማት ያሉበት፣ጥብቅ ደኞችና ፓርኮች ናቸው። እዚህ ላይ መብራራት ያለበት
ጉዳይ አለ፡፡ ለምሳሌ ማእድናትና ነዳጅ ያሉበት መሬቶች፤ በግልና በመንግስት ይዞታ ስር እንዲውሉ መደረግ እንደሚገባው መጠቀስ
አለበት፡፡
የእምነት ተቁዋማትንም ይዞታ በሚመለከት
፤ለማንኛውም የሃይማኖት ክንውን የሚውል መሬት በኃማኖት ተከታዮቹ
ስር እንደሚሆኑ አስፍሮአል።
በመጨረሻም የህብረተስብ የሚላቸው፤
የአርብቶ አደር የግጦሽ፣ባህላዊ ተግባራትንና ለማህበራዊ ግልጋሎት የሚውሉ ቦታዎች የወል ስለሆኑ፤ ይዞታቸውም የኅብረተሰቡ እንደሚሆን
አስቀምጡዋል።
የአፋሕድ የመሬት ይዞታ ፖሊሲ፤ ስር ነቀል ለውጥ አካሄዳለሁ
ከሚለው ፖለቲካዊ አቁዋሙ ጋር በቀጥታ የሚስማማ ነው። ለኢትዮጵያ የሚበጅ ነው፡፡

Comments
Post a Comment