መሬት ላራሹ!
አንድ ለመንገድ.... ወ/ሮ ታደለች ኃይለሚካኤል፤ በ“ዳኛው ማነው ?” [1] መድብላቸው የመሬት ላራሹ መፈክር ለኩዋሸ፤ የትግራይና የወሎን ገበሬዎች ችጋር በለጋ እድሜው ያስተዋለውና የኪነ-ጥበብም ፍቅር የነበረው ባለቤታቸው ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደሆነ ነግረውናል። የመሬት ስሪት እንዲሻሻል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው የህግ መወሰኛ ምክርቤት፤ ለአንድ ሰው በይዞታ እስከ 90 ጋሻ መሬት(90*40 =3600 ሄክታር) መብለጥ የለበትም የሚለውን ጣራ መቃወሙንም ይጠቅሳሉ። ማነሱ እኮ ነው ጃል! አስገራሚ ተቃውሞ ነው። ደራሲዋ የመሬት ላራሹ፣የብሄረሰብና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የተሳሰሩ ናቸው ይሉናል። የሆኖ ሆኖ እስከ ዛሬ በደርግ የታወጀው አዋጅ አራሹን በዘላቂነት የመሬት ባለቤት እንዳላደረገው፤ የወያኔ/ኢሕዴግ ይሁን የቀጠለው የብልጽግና/ኦሆዴድ ስርአቶች መሬት የብሄረተኛ ኢሊቶች መበልጸጊያ እንዲሆን በማድረጋቸው የባለቤታቸው መሬት ላራሹ መፈክር በተግባር እንዳልዋለ ያስረዳሉ። የግል መሬት እንደማንኛውም ቁዋሚ ንብረት የግል ካልሆነ፤ አራሹ ላቡንም ይሁን ጥሪቱን በመሬቱ ላይ አፍሶስ ምርታማነቱን ለማሳደግ ልቡ መንታ ነው የሚሆንበት። ነገ እፈናቀላለሁ ብሎ ይሰጋል፡፡ የመሬት ምርታማነት መጨመር በቀጥታ ከግል ይዞታ ጋር የተያይዘ ነው የሚሉ ጥናቶች አሉ። የብዙ የአፍሪካ አገሮች የመሬት ስሪት በመንግስት ቁጥጥር ሥር ነው። መሬት በግል ይዞታ እንዲያዝ የፈቀዱት ምስርና ሞሮኮ የመሬታቸው ምርታማነት በመንግስት ይዞታ ስር ከተያዙት አገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው። በመሬት ይዞታ ላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ደሳለኝ ራኽመቶ፤ የኢትዮጵያ ገዢዎች መሬት የግል ከሆነ ገበሬው ሽጦት ከተማ በመግባት ስራፈት ...