ተፈሪው ፋኖ እስክንድር ነጋ!

    

                             ተፈሪው ፋኖ እስክንድር ነጋ!



ዳማዊ ማንነታችን አማራ ነው፡፡ የአካባቢ ማንነቶች(ጎጥ) ከቅርብ ታሪካችን የተከሰቱ ናቸው፡፡ ጥንታዊ የአማራነቱን ማንነት ሳያውቅ በአካባቢ ማንነት መኩራራት አጉል መኮፈስና ታሪክን አለማወቅ ነው ሲል እስክንድር ድል ለዲሞክራሲ በሚለው መድብሉ ገና ዱሮ የትጥቅ ትግል ከመጀመሩ በፊት በዝርዝር ጽፎኣል። እስክንድር-ጠሎች ግን እርሱ ድል ለዲሞክራሲ ነው እንጂ ድል ለአማራ አይልም ሲሉ ይከሱታል። በእርግጠኝነት ለመናገር ወይ መጽሃፉን ተንተርሰውታል፣ አላገኙትም ወይም ሃቁን ቢያውቁትም ወደ ስም ማጥፋት ላለመሄድ ህሊናቸው አልቆረቆራቸውም።

ስክንድር አማራው መንግስት፟፟-መር የዘር ፍጅት እየተካሄደበት ለከፍተኛ የህልውና አደጋ በመጋለጡና አደጋውም በሰላማዊ ትግል ማስቆም ስላልተቻለ  የፋኖን የትጥቅ ትግል ከጎዋዶቹ ጋር ማስተባበር ጀመረ። ወጣት የነብር ጣቶቹ በተለይ እኔ የማውቃቸው ጌጥዮና ወንድይራድ በአሳፋሪ ሁኔታ ዘመኔ ካሴ(የአማራው አብይ አህመድ) አግቶታል። እንዲሁም ሌሎቹ ስማቸውም የማላቀው ብዙዎች አይኔ ላይ ይመጣሉ። በወጣጥነት እድሜያቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትውልድ የሚኮራበት ነው። እስክንድር ገና ወደ ትጥቅ ትግሉ ከመግባቱ በፊት የባልደራስ መሪ እያለ ከታዋቂ የፋኖ መሪዎች ጋር ተገናኝቱዋል። መክሮአል። አንዴ እንደውም በአዲስ አበባ ዘላለም ከሚባል የአገዛዙ ደጋፊ ጋዜጠኛ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ የወለጋን ጭፍጨፋ የአካባቢው ልዪ ሃይል ማስቆም ስላልቻለ ወይም ስላልፈለገ፤ ፋኖ ከመከላከይ ጋር ቢዘምት ጉዳዩ እልባት ያገኛል የሚል ሃሳብ ከማቅረቡ ባሻገር፤ ፋኖ ለቆመለት አላማ የሚሰዋ እንጂ የሚማረክ ባህል ስለሌለው ቆርጦ ነው የሚዋጋው ሲል የፋኖን የውጊያ ባህል በአድናቆት መስክሮአል። ዘላለም እስክንድር በተናገረው ደንግጦ ብርክ ብርክ ነበር ያለው።

መነሻችን መድረሻችን

አንዱ በእስክንድር ላይ የሚሰነዘረው የሃሳብ ትችት፤ መነሻችንም መዳረሻችንም አማራ ብሎ ከመታገል ይልቅ፤ መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያ ማለቱ ነው ። በቅርቡ ከእስር ተፈትቶ አሁን በስደት የሚኖረው አሳዬ ደርቤም አማራ በአማራነቱ ብቻ ታግሎ ስልጣንም መያዝ ይችላል፤ ኢትዮጵያ እያለ ለሌሎች አጉል አሳቢ መሆን አይገባውም የሚል ግራ የተጋባው ትችት አቅርቦአል።

እንደ እውነቱ ከሆነ አማራ በታሪክ፣በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች አማራም ኢትዮጵያዊም ነኝ የሚለው ለራሱ ነው።ለማንም አይደለም።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ብሄርተኝነት በባህሪው ፈጥኖ ተደራጅቶ የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ ስለሚያግዝ ሁሉም የፋኖ ድርጅቶች  በአማራነት ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡

የህልውና አደጋው ከተወገደ በሁዋላ፤ ማለትም የአብይ አህመድ አገዛዝ በትጥቅ ትግል ይሁን በድርድር ከተወገደ በሁዋላ፤ ማንንም የማያገል፣ለሰላምና ለእድገት ምቹ የሆነ ሰርአት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መዘርጋት አማራን ይጠቅመዋል እንጂ በጭራሽ ሊጎዳው አይችልም፡፡ እስክንድርም እያደረገ ያለው ይኼንኑ ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ከጀመረ ጀምሮ አንዱንም ድርጅት በኢትዮጵያ ስም ስይሞ አያውቅም፡፡

እዚህ ላይ የፕሮፌሰር ሃብታሙ፤ እስክንድር ርእይ የለውም የሚል ትችትን አብሮ ማንሳት ተገቢ ነው። ፕሮፌሰሩ አማራ በሰላም እንዲኖር ኦሮሞ የቀማውን አፅመ-እርስቱን  ማስመለስ አለበት የሚል ጠንካራ አስተያየት አለው። ይኼም የመነጨው በታሪክ  የኦሮሞ ጽንፈኞች ከሚያደርጉት ተደጋጋሚ ወደር የለሽ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች የመነጨ ነው።ፖለቲካ በተጨባጭ መካሄድ ስላለበትና እስክንድርም ፖለቲከኛ ስለሆነ የፕሮፌሰሩን ሃሳብ አልገዛም።ፕሮፌሰሩም ተመራማሪ ስለሆነ እርሱ ለአማራው ይሻለዋል ብሎ ያስበውን ሃሳብ ከማራመድ ሊቆጠብ አይገባም። በመነሻችን አማራ በመዳረሻችን አማራ ጥቁር አንበሳ የሚል የፖለቲካ ድርጅትም ተመስርቶ ብዙ እንዳልተራመደ ፕሮፌሰር ሃብታሙ  በደንብ ያውቃል። የበራራ ደራሲ ሃብታሙ ተገኝ ግን የጎጠኝነት ስሜት አይነካውም።ጉዳዩ  በልዩነት  ሊያዝ የሚችል ነው።

ለነገሩ በዚህም በዚያም ያለው የፋኖ ጦርም በአረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ አሸብርቆ ነው የምናየው።  የአማራ ጠላቶች ፤ አማራ አማራነትንም ብቻ ሆነ አማራነትንና ኢትዮጵያዊነትን ቢያቀነቅንም ከጠላትነታቸው አይታደቡም። ትግላችን በአሁን ሰዓት የህልውና ነው እንጂ ጠባብ የስልጣን ፋላጎት አይደለም ሲል እስክንድር ደጋግሞ የሚናገረው በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል።

ስልጣን

ሌላው እስክንድር ባልዋለበት የሚጥላላው ደግሞ በባልደራስም ሆነ በፋኖ እንቅስቃሴ እርሱ ሚሾማቸውንም ሰዎች ከሌሎች ጋር ሳይማከር እራሱ ነው የሚል ነው። ለምሳሌ በባልደራስ የሚሰነዘርበት ትችት፤ ኤርሚያስ ለገሰን በውጭ አገር ተወካይ ማድረጉ ስህተት ነበር የሚል ነው። አሳዬ ደርቤ ኤርሚያስ የባልደራስ አባላትን ስም ዝርዝር ለአብይ አሳልፎ ሰጥቶታል ብሎ ይከሳል። የአሳዬን ክስ እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኩዋን፤ የዛሬው የኤርሚያስ ክህደት እንዴት ሆኖ  የእስክንድር ጥፋት ሊሆን እንደቻለ በአመክንዮ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያዳግታል። እስክንድር ጠንቁዋይ ይቀልባል እንዴ? በወቅቱ ኤርሚያስ በውጭ አገር ለአዲስ አበቤ መብት ከሚታገሉት ሰዎች ነበር።

ባልደራስም ከማህበራዊ ድርጅት ወደ ፖለቲካ ድርጅት ሲቀየር ኤርሚያስ እኔ የፖለቲካ ድርጅት ተወካይ መሆን አልፈልግም ብሎ መውጣቱን ነው የምናውቀው። አሁን ኤርሚያስ የሚያደርገው ትግል ሌላ ጉዳይ ነው። እንደው ለነገሩስ ባልደራስ በግልጽ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለሆነ ለምንድነው የአባላቱ ስም የሚደበቀው?  የስም ዝርዝሩ አሜሪካ የሚላክበትስ ምክንያት ምንድነው? ሃቀኛ ትችት ነው?

ሁለተኛው ክስ ደግሞ የአማራ ሕዝባዊ ግንባርን ሲመስርት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን በውጭ አገር ተወካይ ማድረጉ ነው። ሻለቃ  በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እንደ ዘመን አመጣሽ፤ አማራን እንደ ጨቁዋኝና በዳይ አድርገው ከሚስሉት ሰዎች ስለነበሩ፤ (መረጃውን የደም እንባ/Red Tears መጽሃፋቸው ላይ ማየት ይቻላል)፤ ቢያንስ ይቅርታ ሳይጠይቁ በአማራው ትግል የጎላ የመሪነት ስፋራ መያዝ የለባቸውም የሚል ነው። ትችቱ ተገቢ ነው። ቢዋጥ ኖሮ ችግሩ ወዲያው ሊቀጭ ይችል ነበር። ሻለቃው ግን እልህ ስለተያያዙ ይቅርታ መጠየቅ አልፈለጉም።

ልደቱ አያሌውም የሻለቃውን፤ አማራ እኛ የሰራናት አገራችን ናት የሚለውን የፖለቲካ አተያያቸውን ቀልብ አድርጎ ከአስተባባሪነታቸው እንዲነሱ ወይም ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠንካራ ዘመቻ ከፍቶ ነበር።

ዳዊት What a life! ከሚለው መድብላቸው የምንረዳው በአለም ላይ ካሉት ባለስልጣናት በቀላሉ መገናኘት የሚችሉና ብዙ የአለም አቀፍ ተመከሮ ያካበቱ ዲፕሎማት ናቸው። የቀረበባቸው ወቀሳ  ከመነሳቱ በፊት ለግንባሩ ያሰባሰቡት ገንዘብና ያከናወኑት የዲፕሎማሲ ስራዎች አማራውን የጎዱ ሳይሆኑ የጠቀሙ ናቸው። የፋኖም አደረጃጃት ቢያንስ በብርጌድ እንዲደራጅ የተደረገውም በዚህ ወቅት ነው። ስለዚህ ዳዊት የተነሳባቸውን ትችት ቶሎ ቢቀበሉ ኖሮ የእስክንድር ምርጫ ልምድንና ችሎታን ያካተቱ መስፍርቶች ስለነበሩ የዳዊትም ስራ ስኬታማ ይሆን ነበር። ይኼም የእስክንድር ችግር አይደለም።የዳዊት የፖለቲካ ባህል እንጂ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እስክንድር በመክሊቱ(ጋዜጠኛነቱ) እንጂ መሪ ሊሆን አይችልም የሚል የአቻምየለህ ታምሩ አሲቂኝ ትችት ነው። የሚገርመው ደግሞ አቻሜለህ የእርሱ የመሪ መስፍርት ምን እንደሆነ  የጠቀሰው ነገር አለመኖሩ ነው። እስክንድርም ጋዜጠኛ ሆኖ ቢሰራም የተማረው ፖለቲካ ሳይንሳና ኢኮኖሚክስ ነው። ምንም ፍርሃት የለሽ ፖለቲከኛም ነው።

አሁን ደግሞ የአማራ ፍኖ ድርጅት ተመስርቶ እስክንድር  5 ለ 4 ዘመነን አሸንፎ ከተመረጠ በሁዋላ አቻምየለህ፤ እስክንድር የነካው ነገር ሁሉ ይፈርሳል የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶአል።

አንደኛ ነገር እስክንድር መስራች የሆነባቸው ድርጅቶች አንዳቸውም አልፈረሱም። መአሕድ ወደ መኢአድ ሲቀየር እንኩዋን እስክንድር የተቻኮለ ነው ብሎ ይደግፍ የነበረው መአህድን ነው። ባልደራስንም ከአዲስ አበባ አትኩሮቱ ወደ አገራዊ ቁመና ያለው ፓርቲ ነው የለወጠው። አላፈረሰውም። የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ከተመሰረተ በሁውላም ትግሉ ከገንዘብ ማሰባሰብ ወደ ሌላ ከፍታ ይሄድ ተብሎ ነው የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሰራዊት የተመሰረተው። በዚህ ምስረታ እንደልማዳቸው ያፈሩ ስለነበሩ ይኼኛው ድርጅት በሜዳ ስራውን ቢሰራም በውጭ ግን በግልጽ የሚደርገው እንቅስቃሴ ውስን ነበር።

አሁን የተቁዋቁዋም የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ገና አዲስ ድርጅት ስለሆነ እንዴት ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገና የምናየው ነው። የጦር ካቢኔ ግን አቁዋቁሙዋል። አብዛኛውን የፋኖ ኃይል ያካተተ ስለመሆኑ አሌ የሚባል አይደለም።አቻሜለህ እርሱ የፈለገው የጎጡ ሰው ዘመነ ካሴ እንዲመረጥለት የፈለገበትን ምክንያት ለመደበቅ እንኩዋን ያለመቻሉን የምናጤነው እስክንድር እንደ መሪ “የአካባቢውን ህዝብ ስሜት”፤ በሌል አነጋገር ጎጥ! አይጋራም ሲል በመጻፉ ነው። እርግጥ ነው! ከላይ እንደጠቀስነው እስክንድር ጎጠኝነትን አያራምድም። ቀዳማዊ አማራነቱን ከፍ ሲልም ኢትዮጵያዊነቱን ነው።

ኮማንደር አሰግድ

አሰግድ በወርቁ አይተነው(የጎጃም ተወላጅ ነው) ገንዘብ ጦሩን እንዳጎለበትና እንደውም አንዱን ክፍለጦር በእርሱ ስም እስይማለሁ ሲል ተደምጦአል። ወርቁ የስድተኛ ክፍል ተማሪና ህጋዊ ሌባ ቱጃር ነው።

አሰግድ እርሱ በሚቆጣጠራቸው ቀበሌዎች ነዋሪዎቹን ሰብሰቦ፤ “እስክንድር ከአዲስ አበባ በአማራነታቸው ለተፈናቀሉት 500000 ስዎች ሳይሆን የቆመው ለኢትዮጵያ ነው”   ብሎ ህዝብ ሲቀሰቀስ አድምጪያለሁ። ያልኩት አንድ ነገር ነበር። “አንተ ጭቦኛ እግዜአብሄር የእጅህን ይስጠህ”። የባልደራስ ቁንጮዎች እንደ ማንም በተቃዋሚ ስም ድርጅት መስርቶ ቢሮ ብቻ በመጎለት መግለጫ ብቻ የሚያወጡ የድርጅት መሪዎች አልነበሩም። እስክንድርና ስንታየሁ ቸኮል ሰው በተፈናቀለ ቁጥር ፈጥነው በቦታው ደርሰው ለተጎጂዎች እርዳታ እንዲያገኙ፤የሚያስተዛዝኑና እንዲታገሉም የሚመክሩ እንደነበሩ የትናትና ትዝታ ነው። አሰግድ በአንድ ወቅት እጅግ የሚያደንቀውን እስክንድር ለምን ተገልብጦ እንደ ጠላት ማየት ጀመረ? ነገርማ አለ።አሁን ግን እርሱ ታሪክ ነው።

ዘመነ ካሴ

የጎጃሙ ዘመነ ካሴም እንዲሁ “እስኬው ዘመን የማይቀደረው የሁላችንም መሪ ነው " ባለበት አንደበቱ እስክንድርን በማጥፋት ስራና  በጎጠኝነት ሰንስለት ተተብትቦ ነው  የሚገኘው። በእኔ አስተያየት የጎጃም እዝ አመራር ፤ ጎጠኛና ሕዝበኛ 'ከመሆኑም ባሻገር ገና ከአሁኑ ጋዜጠኛና ልዩነት ያላቸውን  ወንድሞቹን የሚያስር ሆኖአል።  የእዚህ ቡድን አካሄድ የነፃነት ታጋይ መንፈስ የለውም። እውቀቱም ውስን ነዉ። መሪው ራሱ ለደህንነቴ እሰጋለሁ ብሎ በአደባባይ ለሰራዊቱ የሚናገር ቡኬ ከመሆኑም በላይ ካልጠፋ ቲሽርት  በደማቅ ቀይ USA የተፃፈበት ለብሶ ስራዊቱ ፊት የሚታይ ነዉ። ልክ እንደ አብይ አህመድ ለአሜሪካ ለመታገል የሚወድ ወይም እይታገለ የሚመስል… ሃላፊነቱን ያልተገነዘበ ጎጃሞች እደሚሉት ገና ሞሳ(ልጅ)  ነው። እስክንድር ግን አስቦ የሚናገር፣ቆራጥ፣ ተአማኒ፣ መንፈሳዊ፣ ንዋይ የማይደልለው፣ በሚገባ የተማረ፣ያነበበና የፃፈ በመሆኑ የአብዛኛውጓ ፋኖ ድጋፍ ስላገኝ አሁን የግዙፉ ፋኖ ኃይል መሪ ሆኖአል። በዚህ ምክንያት ተቀናቃኞቹና የስልጣን አምሮት ያላቸው እርሱ እደሚለው የደም ነጋዴዎች፤ አራት ኪሎ ስልጣን ይይዛል ብለው ፈርተዋል። ፍራቻቸውን አምላክ ቢያሳካው፤ የአገሪቱ ጠር የሆኑት፤ ሌብነት፣ንቅዘት፣ጎጠኝነት፣ጎሰኝነትና የመሳሰሉት ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው የሚገቡት። ገደል ይግቡ አቦ!

8/8/2024

ቦጋለ ካሣዬ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!