WHAT A LIFE!
What a life![1]
ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ
የጻፉት ዳጎስ ያለ የህይወት ታሪካቸው ነው፡፡በብዙ ዋቢዎች የታጨቀ ስራ ነው፡፡ በአማርኛ ይተረጎማል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ እንግሊዘኛ የምትችሉ ገዝታችሁ ብታነቡት ትጠቀማላችሁ
እንጂ አትከስሩም፡፡
አንዳንድ ጉዳዮችን በወፍ በረር እነሆ፤
1/አባታቸው
ወልደ ጊዮርጊስ ዮሃንስ የቤተክህነት ትምህርትን በትጋትና በጥልቀት ስለተማሩ ለትርጉም ስራ ያግዛሉ ተብሎ ተመረጡና ከቤተመንግስት ጋር ትሥራቸው ቀና ሆነ። የመጀመሪያው የአዲስ ዘመን
ጋዜጣ አዘጋጅ ለመሆንም በቁ። መጻህፍትም ጽፈዋል። አንዱ ልጃቸውም የኢትዮጵያ ሄራልድ አዘጋጅ ለመሆን በቅቱዋል። የዳዊት እናት ዋካ የቤት እመቤት ናቸው። እውቁ ዲፕሎማት ብርሃኑ ድንቄ አጎታቸው ናቸው። ዳዊት ለጣሊያን ያደሩት የባንዳ ወልደ ጊዮርጊስ
ዮሃንስ ልጅ ነው የሚለው ሃሰት መሆኑንና፤ ጉዳዩ በሰመ ሞክሼ የመጣ እንደሆነ አብራርተዋል። በበአሉ ግርማ፤ ኦሮማይ ድርሰትም እርሳቸውን የሚገልጠው ገፀባህሪ የተለየ እንደሆነና ፍያሜታም ከእርሳቸው
ሁለት ፀሃፊዎች አንዱዋ እንደነበረች፤ በአሉም የራሱን የአዲስ አበባዋን
ፀሃፊ ከሚያመጣ ይልቅ ፍያሜታን ራሳቸው እንደመደቡለት ያስረዳሉ።
በዘፈቀደ ወደ እርሳቸው የተላከከው የፍቅር ተረክ ካለማወቅ እንደሆነ አብራርተዋል። ዳዊት አብርሃም ያየህና ገ/መድህን አርአያ ለደርግ
እጃቸውን በሰጡበት ወቅት፤ በስፋት የተሰራጨው “ታላቁ ሴራ” የእርሳቸው ጽሁፍ መሆኑን ኢፋ አድርገዋል፡፡
2/ለምለም
ምህንድስና ነበር ለማጥናት ያሰቡት። ካለፍላጎታቸው ወደ ሐረር ጦር አካዳሚ ለስልጠና ከገቡ በሁዋላ ነው ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን
ስም፤ ራሳቸው ወደ ዳዊት የለወጡት። ምክንያታቸውም፤ እንግዲህ ወታደር ከሆኑኩ
አይቀር ፤ ዳዊት ለወንድ መጠሪያ ብዙም ከማይውለው ለምለም ተስማሚ ነው በሚል ነው። የኤርትራ አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት አንድ
ወደ ሻእቢያ ገብቶ የተማረከ ጉዋደኛቸው ተይዞ ፊታቸው ሲቀርብ “ለምለም”! ብሎ ሲጠራቸው የአንድ አገር ልጆች የነበራቸውን ንፁህ ወንድማማችነት አስታውሶአቸው ስሜታቸው በጣም ተነክቶ እንደነበር
አልደበቁም።
3/ናዝሬት
ት/ቤት መማር ከቻለቺው የመጨረሻ እህታቸው በስተቀር ሁሉም የወልደ ጊዮርጊስ ዮሃንስ ልጆች የተማሩት ተፈሪ መኮንን ነው። ዳዊት
ስካውት ነበሩ፡፡ ስድስተኛን ክፍል እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ወደ ዘጠነኛ ክፍል እንዲያልፉ ከተደረጉት ጥቂት ተማሪዎች አንዱም ነበሩ። እድለኛ
ነኝ እንጂ ጎበዝ ነበርኩ አይሉም።
የሐረር አካዳሚ
ትምህርታቸውን ከአጠናቁቁ በሁዋላ የተመደቡት ኤርትራ ነበር። ከዚያም በተለያየ ጊዜ አሜሪካ በመሄድ ከፍተኛ ትምህርት ቀስመዋል።
የአሜሪካ ቆይታቸው
ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም። በተለይ ዘረኝነቱ እጅግ ስሜታቸውን ነክቶት ስለነበር እረፍት እንዲወስዱ ሁሉ ተደርጎ ነበር።ፊት ለፊት የገጠማቸውንም ዘረኝነት በቡጢያቸው ለመመለስ ተገደውም ነበር። በዚህም ከኢትዮጵያውያን አለቆቻቸው ጎሽታን እንጂ ተግፃፅ አልገጠማቸውም።
ኤርትራ በግዳጅ
ላይ እያሉ አደጋ ደረሰባቸው።ረዢም የማገገሚያ ጊዜ ስላስፈለጋቸው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው ህግ አጠኑ። ከጎሹ ወልዴና
ከአሰፋ ጫቦ ጋር ነው የተማሩት። ሁለቱም በትምህርታቸው ልህቀትን እንዳሳዩ ይመስክሩላቸዋል። ከዚያም አሜሪካ በህግ ማስትሬታቸውን
ስርተዋል። አብዮቱ ፈነዳና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።
በደርግ ስርአት
ውስጥ ከሰራዊቱ በተጨማሪ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኤርትራ አስተዳዳሪነትና በእርዳታ ማስተባባሪያ ኮሚሺን ሃላፊነቶች ስርተዋል፡፡
4/በውጭ ጉዳይና
በእርዳታ ማስተባባሪያ ኮሚሺን ሃላፊነታቸው ወቅት ከብዙ የአፍሪካም ሆነ የዓለም መሪዎች ለመተዋወቅና ለመስራት እድል አግኝተዋል።
ዳዊት በታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሬ ጨዋነትና ቅንጦት አልባ ህይወት ተገርመዋል። ኔሬሬ ስልጣን ከያዙ በሁዋላ ወደ ቤተመንግስት አልገባም
ብሎው አሻፈረኝ በማለት በገዛ ቤታቸው ነበር መኖር የመረጡት። ታንዛኒያ ነፃነቱዋን
የተቀዳጀቺው በድርድር ነው። እናንተ ኢትዮጵያውን ግን ተዋግታችሁ ጠላቶቻችሁን በማሸነፍ ነው፡፡ይኼን እጅግ ነው የማደንቀው ሲሉ እንደነገሩዋቸው ጽፈዋል።ዳዊት በደቡቡ አፍሪካ አፓርታይድ እንዲወገድ፣የናሚቢያንና
እንዲሁም የደቡቡ ሱዳን ነፃ አውጪዎችን በመደገፍ ኢትዮጵያ የተጫወተቺውን ወሳኝ ሚና በቀዳሚነት የመሩ ዲፕሎማት ናቸው።ይኼ ልምዳቸውና
የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚሺነር ስራቸው በስደት በኖሩበት ወቅት በተለይ በተባበሩት መንግስታት ስራ ለማግኘት እጅግ ጠቅሞአቸዋል፡፡
5/በኤርትራ ክፍለ አገር አስተዳዳሪነታቸው፤ የሻእቢያ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱና
ሌሎች ተዋጊዎችም ወደ በርሃ እንዳይሄዱ በማድረግ ስኬታማ ነበርኩ ነው የሚሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ሻእቢያ ሊገላቸው በተደጋጋሚ
ሞክሮ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ይሁን እንጂ ደርግ የሃይል መንገድ በመጠቀሙና በተለይ የቀይ ኮኮብ ጥሪ ከከሸፈ በሁዋላ የኤርትራ ጉዳይ
እንዳልሆነ ሆኖአል፡፡ የኤርትራ ፊዴሬሺን መፍረስ ህገ ወጥ ነበር የሚለውን የተሳሳተ አረዳድ ዳዊት አጥርተዋል፡፡ እንደርሳቸው ከሆነ
የፌዴሬሽኑ መፍረስ ይሁን መቀጠል የሚወሰነው በፌዴሬሼኑ በተሳሰሩት አገሮች ይሁንታ ነው፡፡የተባበሩት መንግስታትን የሚመለክት ጉዳይ
አልነበረም፡፡ሊቢያም የሆነው ይኼው ነው፡፡ዛሬ የኤርትራ ጉዳይ የተበላ እቁብ ቢሆንም የፊዴሬሽኑ አፈራርስ ግን ህገወጥ አልነበረም፡፡
6/ ወደ እርዳታ ማስተባበሪያ
ኮሚሺን ከተመደቡ በሁዋላ እ.አ.አ በ1984/5 በኢትዮጵያ ለተከሰተው ርሃብ በተለይ ከውጭ አገር እርዳታ በማስተባበር ዜጎችን ታድገዋል።
ከአቶ ሽመልስ አዱኛ የእርዳታ
ማስተባባሪያ ኮሚሽነር ጋር በጣም ፍሪያማ ስራ እንደሰሩና ብዙ እንዳስተማሩዋቸው ይናገራሉ።ማሪያ ተሬዛን ኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር
አግኝተው ለማነጋገር እድል አግኝተዋል፡፡በውጭ ጉዳይም ሆነ በማስተባበሪያ ኪሚሽነር ስራቸው ብዙ ጊዜ ወደ ውጭ በተለይም ወደ ምእራቡ
ስለሚጉዋዙ የመንግስቱ አገዛዝ በአይነቁራኛ ያያቸው እንደበር ጽፈዋል። በዚህም መሰረት ለደህንነታቸው ስለሰጉ አሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ።
ለጥቆም የመንግስቱ ሃ/ማሪያምን አገዛዝ ለመጣል ከጉዋዶቻቸው ጋር ሁለት ጊዜ የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ አካሂደው ሳይሳካላቸው ቀርቶአል።
የመጀመሪያው መፈንቀለ መንግስት ለምን እንደከሸፈ እርሳቸውም በእርግጠኝነት የሚነግሩን ነገር የለም። መፈንቅለ መንግስቱን ለማካሄድ
ናቅፋ ድረስ ሄደው ከሻእቢያ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነትም ደርሰው ነበር።በሻእቢያ ማሳሰቢያ ወያኔ እቅዱን እዲያውቅ አልተደረገም።
የሁለተኛው መፈንቅለ መንግስት
ግን ወያኔም ሻእቢያም የሚያውቁት ቢሆንም የከሸፈው መሬት ላይ ያለው የወያኔ ሃይል ብቻውን ስልጣኑን እንደሚይዝ እርግጠኛ በመሆኑ
ለሙከራው ክብደት ባለመስጠቱ ነው፡፡
6/ዳዊት በአሜሪካ ስራ
ለማግኘት አልተቸገሩም፡፡ መስራት የፈለጉት ስራ ግን ረብጣ ገንዘብ የሚያስገኝ ሳይሆን በአሜሪካ በታዘቡት ኢፍትሃዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ
ጉዳይ ላይ ማተኮር በሚያስችላቸው መስክ ነበር፡፡ አሜሪካን አገር የቤት አልባ ሰዎች መብዛት አንዱ ትኩረታቸው ነበር፡፡ በአሜሪካ
ስለ ልጆች ማደጎ/ጉዲፈቻ እንዲህ ይላሉ፤ ነጮች ጥቁሮቹን በማደጎ ለመወስድ አይችሉም፡፡ ጥቁሮቹ ደግሞ በማደጎ መውሰድ የሚፈልጉት
ልጅ ቆዳው ነጣ ያለውን ነው፡፡በዚህም ምክንያት አሳዳጊ የሚሹ ጥቁር ልጆች አስታዋሽ የላቸውም፡፡
7/ዳዊት በተባበሩት መንግስታት
ድርጅት ተቀጥረው፤ አማካሪ በመሆን በአፍሪካ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ረሃብ፣መፈናቀል፣ጦርነት፣የዘር ማጥፋትና መድልዎ፣ የመሳሰሉትን
በተለይ በደቡብ ሱዳን፣በላይቤሪያ፣በሩዋንዳ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ተጋፍጠዋል፡፡የአገሮቹን የአቅም ግንባታ በማጠናከርና በማቁዋቁዋም
አግልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ስለሚካሄደው የጦር መሳሪዎች ዝውውርም ጥናት አካሂደዋል፡፡
በእነዚህ አገሮችም ሆነ በኢትዮጵያ በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ በማየት፤ እንደው ለመሆኑ አምላክ አለ ወይ? ይኼ ሁሉ
ሰቆቃ ሲደርስ ለምን አያስቆምም? ብለው ህሊናቸውን እንዳስጨነቁት
አልደበቁም፡፡
8/ዳዊት ኮሌኔል መንግስቱ
ሃይለማሪያም ስልጣኔን እቀማለሁ ብሎ የሚፈራ ወፈፍተኛ/ psychopathic/ የሰነልቦና ችግር ያለበት ሰው ነው የሚለውን ሲያጠናክሩ፤
ለምሳሌ ጄኔራል ፋንታ በላይን (ገና ዳዊት ኢትዩጵያ እንዳሉ ጄኔራሉ መንግስቱን ለማስወገድ እንደሚፈልጉ እንደነገሩዋቸው ይጠቅሳሉ)፤ በገመድ አሳንቆ ካስገደላቸው
በሁዋላ፤ሬሳቸው ላይ ተፍቶና ተሳድቦ ሲወጣለት ሁለት ሲጋራ አጭሶ ወደ ስራው እንደተመለሰ፤ ዝምቡዋቤዬ አግኝተው ያናገሩት አንዱ
አጋዳይ/ገዳይ አጫወተኝ የሚሉትን አጋርተዋል፡፡
ምንም እንኩዋን ካሣ ከበደ
ከመንግስቱ ጋር ምንም ዝምድና እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ራሳቸው የገለጡ ቢሆንም፤ ዳዊት ግን ጉዳዩ የተዋጠላቸው አይመስልም፡፡ እንደርሳቸው
ከሆነ ካሳ ከመንግስቱ ቀጥሎ ፈላጭ ቆራጭ ወሮበላ(thug) ነበሩ፡፡ ዳዊት ከተሰደዱ በሁውላ ሚስጥር እንዳያወጡ ካሳ ነበሩ አስጠነቀቁኝ
የሚሉት፡፡እርሳቸውንም ለማስገደል በተደጋጋሚ ይዝቱም ስለነበረ ይኼንኑ በሰደት አሜሪካ እያሉ ለአሜሪካው የስለላ ቢሮ ሰዎች ማሳወቃቸውን
ገልጠዋል፡፡ ካሳ ከበደ ሆሎታ ጦር አካዳሚ ገብተው አጥጋቢ ውጤት ባለማምጣታቸው አባታቸው ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ወደ እስራኤል ይልኩዋቸዋል፡፡
እዛም ከትምህርታቸው ይልቅ አሸሼ ገዳሜ ላይ ማተኮራቸው ሲታወቅ ወደ አሜሪካ ደግሞ ይላካሉ፡፡ ከዚያ ተመልሰው ነው ኢትዮጵያ መስራት
የጀመሩት፡፡ በደርግ ውድቅት ዋዜማም ፈላሻዎችን ወደ እስራኤል በማጉዋጉዋዙ
ሂደት ትልቁን ገንዝብ መቆጣጠር ባይችሉም ወደ 3 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኙበት ዳዊት በማስረጃ ይገልጣሉ፡፡ በስደትም ካሳ ትምህርት
ቤት ገብተው ከጨረሱ በሁዋላ አገኙት የሚሉትን ዶክትሬት እንደ ዳዊት ከሆነ መደበኛ አካሄዱን ያልተከተለ ስለሆነ የውሸት ነው…የአብይ
አህመድ አይነት መሆኑ ነው፡፡ ዳዊት በእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሺን በሚሰሩበት ጊዜ ደርግ ገንዘብ ሰርቀዋል ብሎ ሰማቸውን ቢያጠፋም፤ከድህረ
ደርግ በሁዋላ ሂሳቡ በኦዲተር ተመርምሮ ምንም የሚያስጠይቃቸው ነገር እንዳልተገኘ አብራርተዋል፡፡
9/ዳዊት የትኛውም በጭቆና
ስር ይሁን በጦርነት ስር ያለፈ አገር እውነተኛ ሰላም ለማምጣት ሃቀኛ የሽግግር ፍትህ( transitional justice) ማካሄድ
አለበት ይላሉ፡፡ ለምሳሌ አፓርታይድ በደቡቡ አፍሪካ ተወገደ ቢባልም አሁንም ቢሆን የነጮቹ የኢኮኖሚ የበላይነት እንደቀጠለ ነው፡፡ጥቁሮችም
በድህነት አረንቁዋ ውስጥ ተዘፍቀው ቀርተዋል፡፡ በላይቤሪያም ስላም መጣ የሚባለው እስከ ሰው መብላት ድረሰ የደረሰ ወንጀል የሰሩ
ዜጎች ለፍትህ ሳይቀርቡ ነው፡፡ስለዚህም እነዚህ አገሮች ትክክለኛ የሸግግር ፍትህ ስላላካሄዱ በማንኛውም ጊዜ ለሌላ ዙር ግጭት ተጋላጮች
የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡
ዳዊት የ Rwandan
Patriotic Army(RPF) ስልጣን ይዞ የዘር ፍጅቱን እንዳስቆመ ሩዋንዳ ሄደው የመንግስት አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡በሩዋንዳ
የተካሄደውን ዘር ማጥፋት ያደረሰውን የስብአዊ ቀውስ በአይናቸው አይተዋል፡፡ ስለባዎችንና ገዳዮችንም አናግረዋል፡፡እንደ ዳዊት ከሆነ
ይኽም ሆኖ ሩዋንዳ የአገረኛውንም የቅራኔ አፈታት(Gacaca/ጋቻቻ) ተመክሮ በመጠቀም፣ የአህጉራዊና የአለም አቀፍ ድጋፍና ትብብር በማግኘቱዋ የተሻለ የሽግግር ፍትህ የተካሄደባት
አገር ናት፡፡ በዚህም መሰረት ዜጉዎቹዋ ያለፈውን ሳይረሱ፤ በሰላም
እየኖሩና ኢኮኖሚያቸውም የተፋጠነ እደገት እያሳየ ይገኛል፡፡
ዳዊት በኢትዮጵያም እንዲሁ
እውነተኛ የሽግግር ፍትህ አማራጭ የለሽ ነው የሚሉት፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት የህልውና አደጋ ለማውጣት ዛሬ መሪ፣ብርታትና ብልሃት
አስፈላጊ እንደሆኑና እነዚህ ሲሙዋሉ ፤ ህገ መንግስቱን መቀየር፣የጎሳ ክልልሎችን አስወግዶ የአካባቢ/መልካምድራዊ ፌዴሬሺን ማዋቀር፣በእርስ
በርስም ሆነ ከመንግስት ጋር የሚደረጉ ግጭቶችን ለማቆም የቆረጠ አቁዋም ወስዶ ሰለምና ደህነትን ማሰጠበቅ፣ ትክክለኛ ዳኝነትና የህግ
የበላይነትን ማስፈር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
10/ዳዊት አፍሪካም ሆነ
በተለይ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ዋና የሽብርተኝነትን አሰራጭ/ የክፋት ፍሬ(kernel of evil) በሆነው ሳውዲአረቢያ እየተስፋፋ
ያለውን ዋሃብዚምን በአንድነት መታገል አለባቸው ይላሉ፡፡ በተለይ ለኤርትራ ይህ ሁዋላቀር ሃይማኖት ከፍተኛ አደጋ እንደሆነ ከየመን
ተመክሮ ልትማር ይገባል ይላሉ፡፡ ኤርትራ ዛሬ ለብቻዋ አገር ብትሆንም ይኼን አደጋ ለመቁዋቁዋም ከኢትዮጵያ ጋር የፖለቲካ መቀራረብ ማድረጉዋ ለህልውናዋ መጠበቅ ወሳኝ ነው የሚሉት፡፡ ዳዊት
የአሜሪካን ቅጥ ያጣ ሞራለቢስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አምርረው ይቃወማሉ፡፡ ከሳውዲ ጋር ያለውን ግንኙነት ይኮንናሉ፡፡ አሁን በአሜሪካ
የሚታየው ህዝበኝነትና ዘርኝነት ከቀጠለ አሜሪካ የአለም መሪ ሳትሆን መሳቂያ መሆኑዋ አይቀሬ ስለሚሆን ዜጎቹዋ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ
መነሳት አለባቸው ብለውም ይመክራሉ፡፡
11/ ዳዊት አንድ ልጅ
አላቸው፡፡ ስፖርተኛ ናቸው፡፡ ተራራ መውጣት፣በበርሃ አሸዋ ላይ መኪና መንዳት፣ የሞተር ሳይክልና ውሻ ይወዳሉ፡፡ አላማጅም ናቸው፡፡ የደቡቡ
አፍሪካ ደንቆሮ የነጭ ዘረኞችን አስተምረው ጥሩ ጉዋደኛና የቤተ ሰራተኛ አድርገዋል፡፡ ሆን ብለው ዘረኝነት የሚያቀነቅኑትን ግን
አምርረው የሚቃወሙ ናቸው፡፡
ቦጋለ ካሣዬ
ዲሴምበር 2023/አትዋ
Comments
Post a Comment