ሕጻናት አምባ

ሕጻናት አምባ....

ኤርሚያስ ተኩማ...ስለ ሕጻናት አምባ የጻፈውን ካነበብኩ በሁዋላ አንዳንድ የማውቃቸውን ነገሮች ለማንሳት ፈለኩ። በርግጥም አምባው የተመሰረተው በሶማሌም ሆነ በኤርትራ ጦርነቶች ሳቢያ አባቶቻቸውን ያጡ ሕጻናትን ለማሳደግ ተብሎ ነበር።
ከዚህ ቀደም ብሎም ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም በጦርነት ለአካለ-ጎዶሎነት የተዳረጉትን ወታደሮች በደብረ-ዘይት... ወደ ሆራ መሄጃ ላይ የጀግኖች አምባ መስርቶ በሚገባ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ያደርግ ነበር። ሁለት እግሮቹና አንድ እጁ የተቆረጠ ጀግና በአይኔ አይቻለሁ። ከዚህ በመለስ የተለያዩ ጉዳተኞች ነበሩ። እንደዚህ አይነት ጉዳተኞቹን ለመንከባከብ ሙሉ ግልጋሎት የሚሰጥ ተቁዋም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ቤተሰባቸው በመንግስት ገንዘብ ቢደጎም እንኩዋን ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ እውቀቱና አቅሙ አይፈቅዱለትምና። የጀግኖች አምባ ዛሬ ባይኖር አይገርመኝም። በወያኔ አይን የጠላት ማገገሚያ ነበርና።
የሕጻናት አምባን ጉዳይ ግን ዘለግ አድርጎ ማየት ሳይጠቅም አይቀርም። በአቡነ ጎርጎርዮስ ምክር ቤተክርስቲያንና መስጊድ ተሰርተው መንፈሳዊ ግልጋሎት መስጠት መጀመራቸውን ከኤርሚያስ ጽሁፍ ነው ላውቅ የቻልኩት። እኔ አምባው ውስጥ ሰራተኛ በነበርኩበት ወቅት ይኽ ግልጋሎት አልነበረም።
በመጀመሪያ ደረጃ ልጆቹ ሁሉ አባት የላቸውም ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም .... አብዛኞቹ እናት ነበሩዋቸው። አባታቸው የሞቱባቸው ልጆች የተሰበሰቡትም በኮታ ነው። ለምሳሌ አንድ አባት 5 ልጆች ጥሎ ከሞተ አምባ ይገባ የነበረው አንድ ነው። ስለዚህ ሁሉም አባቶቻቸው በጦርነት የሞቱባቸው ልጆች ሕጻናት አምባ ውስጥ አልገቡም።
የአባታችንን ምክር ያነሳሁት ካለነገር አይደለም። በአምባው ውስጥ የነበሩ የስነልቦና ጠበብቶች የነበራቸውን ስጋት አውቅ ስለነበር ነው። ስጋታቸውም በአጭሩ የልጆቹ ከህብረተሰብ ተለይቶ ማደግ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ያስከትላል የሚል ነበር። በዝርዝርም .... ኢትዮጵያውያን ያደገነው ሁሉም ነገር ሳይጉዋደልበን አይደለም። ያልታሰበ እንግዳ መጥቶ ቤት ያለውን ምግብ ቡን! ካደረገው፣ ሌላ እስኪዘጋጅ ድረስ በጥሬ ወይም በቂጣ ረሃባችንን አስታግሰን ነው... ከባሰብንም ሂድ! አክስትህ ጋ፣ አያትህ ጋ ብላ ተብለን ነው። ያደገነው ከእናቶቻችን፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በፍቅርም በጠብም ነው። ከሰፈሩ ልጆች ጋር ጉዋደኞች መስርተን ተጫውተን ነው። ገበያ ይሁን ሱቅ ተልከን ነው። ውሃ ቀድተን፣ አጥር አጥረንና እንጨት ፈልጠን ነው። አርሰን፣ ጎልጉለን፣ ዘርተን፣ አርመን፣ አጭደን፣ ከምረን፣ ወቅተን ነው። እህል ወፍጮ ቤት ወስደን አስፈጭተን ነው።
ኽረ ስንቱ፦ ሱሬያችንም ሲቀደድ የመለበስ ተስፋ ካለው ተጥፎ ነው። በባዶ እግራችን ሮጥን ነው። ብዙዎቻችን ምናልባት ከአንድ የበለጠ የሚቀየር ልብስ አልነበረንም። ልጆቹ ግን ፒጃማ፣ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም፣ የስራ፣ የስፖርት፣ በባእል ቀን የሚለበስ ልብሶች ፣ ጫማዎች ወዘተርፈ ነበሩዋቸው። የሚተኙት በተደራራቢ አልጋ ቢሆንም ዘመናዊ የመታጠቢያም ሆነ የመጽዳጃ ግልጋሎት አሉዋቸው። ልብሳቸው ይታጠብላቸዋል። ምግባቸው በፕሮግራም ነው። የሚበሉት እንደኛ የተገኘውን ሳይሆን ቀደም ብሎ በፕሮግራም የተያዘ ነው። ህክምና ጣቢያው ይሁን ትምህርት ቤቱ አፊንጫቸው ስር ነው። እንደኛ ኪሎሜትሮች መጉዋዝ አይጠበቅባቸውም። የሕጻናት አምባ ልጆች ያድጉ የነበሩት በአለባበስ ይሁን በአመጋገብ ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ልጆች አስተዳደግ በልጦ ነው። ምንም እንኳን... " የእንጀራ ጠርዝ እኮ አልወድም... ይኮርተኛል... እንደሚሉ ሞልቃቄዎች ባይሆኑም።"
ታዲያ እንዲህ ሁሉ ነገር ተደላድሎለት ያደገ ልጅ፣ ወደ ትልቁ ህብረተሰብ ተቀላቅሎ ኑሮውን መግፋት ሲጀምር የህብረተሰቡን ችግር ይገነዘባል ወይ? ሕብረተሰቡን ከማገልገል ይልቅ ህብረተሰቡን አይንቅም ወይ? የቁሳዊ ፍላጎቱስ መረን ያጣ አይሆንም ወይ? ይህንንስ የለመደውን ፍላጎቱን ለማርካት ወንጀል ከመስራት ይመለሳል ወይ? በማለት የሰነልቦና ጠበብቶች ትልቅ ስጋት ይደመጥ ነበር። አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የስነልቦና ጠበብቶችን ስጋት በመንፈሳዊ ትምህርት አስቀድሞ ለመግራት ያደረጉት ውሳኔ በጣም የሚደነቅ ነው ።
የስነልቦና ጠበብቶች ግን እንደመፍሄ ያቀርቡ የነበረው፤ ልጆቹ እናትና ሌሎች ዘመዶችም ስላሉዋቸው መንግስት ለነርሱ በነፍስ ወከፍ የሚያወጣውን በጀት በቀጥታ ለእናቶቻቸው ቢሰጥ እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ልጆች ህብረተሰቡን አውቀው ለማደግ ይችላሉ። ይኽ በማይቻልበት ሁኔታም መንግስት ልጆች ለማሳደግ አቅምና ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ልጆቹ በህብረተሰቡ መካከል እንዲያድጉ ማድረግ ይገባዋል ይሉ ነበር።
ልጆች በቤተሰብ መካካል እንዳያድጉ የሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የቤተሰብ አባል በጦርነት መሞቱ ብቻ አይደለም። ድህነት፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ መፈናቀልን መጠቀስ ይቻላል። እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በአውሮፓም ተቁዋሞች አሉ። ለምሳሌ በኢታሊያ አገር ሳንታ-ካተሪና የሚባል መንፈሳዊ የካቶሊኮች ድርጅት አውቃለሁ። ድርጅቱ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ ከወላጆቻቸው ጋር ማደግ ያልቻሉ ሕጻናትን ያስተዳድርራል። የሚተዳደረውም ከምእምናን በሚገኝ ገቢ ነው። አንዳንድ አቅም እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ማሳደግ ያልቻሉ ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው የሚወጣውን ወጪ ይሸፍናሉ። ልጆቹ የሚተኙትና የሚመገቡት እዚያው ድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ቢሆንም፣ የሚማሩት ግን የተለየ ትምህርት ቤት የለም። ማንኛውም የኢታሊያ ተማሪ የሚሄድበት ትምህርት ቤት ነው የሚሄዱት። ከህብረተሰቡ እንደ አምባ ልጆች አልተገለሉም። ብዙም ባላቅም በአበበች ጎበና የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚያድጉ ልጆችም ከህብረተሰቡ ተገለው አይደለም የሚያድጉት።
ከፍ ሲል ልጆችን ከህብረተሰቡ ነጥሎ በማሳደግ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ችግሮችና የነበሩትን ስጋቶች አይተናል። አንዳንድ መፍትሄዎችም መጠቆማቸውን አይተናል። ይኽ ሁሉ እንዳለ ሆኖ... ኽረ ለመሆኑ የሕጻናት አምባ ቆሜለታለሁ ያለውን አላማ ለማሳካት በሚገባ የታሰበበትና የተጠና ፕሮጀክት ነበር ወይ?
ቦታው፥
አምባው ዝዋይን አለፍ ብሎ ወደ ሻሸመኔ ሲኬድ በስተቀኝ ሰላሳ ሁለት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው የተመሰረተው። አላጌ ይባላል መንደሩ። አመሰራረቱ በጥናት ሳይሆን...በድንቁርናና በትእዛዝ ነው። ስለምስረታው ከሚተርክ መጽሄት እንዳነበብኩት ጭብጡ እንዲህ ነው... 'ኮሎኔል መንግስቱ ከደቡቡ የመንግስት እርሻ ልማት ጉብኝት ሲመለሱ፣ ሄሊኮፕተር ላይ እያሉ ቦታው በወንዝ(ጅዶ) የተከበበና ኩታ ገጠም መሆኑን በማጤናቸው የሕጻናት አምባ በቦታው እንዲመሰረት ትእዛዝ ሰጡ።' ይኽን ድንቁርና አርቆ አሳቢነት ነው እያለ እንደ ሃምሳ አለቃ ሲሳይ ያለ ካድሬ ሲያደነቁረን ነበር።
እንግዲህ ልጆቹን ለማሳደግ የታሰበው ወጪ መገኘት ያለበት፤ ከእርሻ ና ከብት ርቢ ከሚገኝ ገቢዎች ነው።
የልጆቹ ማደሪያዎች፣ ምግብ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ተሰሩ። ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆችም ተሰበሰቡ። ደርግ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣ ባላውቅም፣ ሲዊድን ለሕጻናት አምባ ምስረታ ከፍተኛ ርዳት አድርጋለች።
1.ግራሩ ተመንጥሮ ተቃጠለ። መሬቱ በትራክተር ታረሰ። ሙዝ ተካዩ አረፋይኔ ነው። መሃይም ነው። ጥራዝነጠክ ኢታሊያኒኛ ይችላል። ሚኒስትር ካሳ ከበደ ወደ አምባው አዘውትረው ይመጣሉ። ታዲያ አረፋይኔ! ብለው ሲጠሩት ሌላ ስራ አሰፈቺ ሰው እንደጠራው በማስመስልና በስራ መጠመዱን ለማሳየት ባፍንኩሎ!! ብሎ የቅጥፈት ንዴት ይናደዳል። ወዲያው ዞር ብሎ ካሳን ሲያይ ዝቅ ብሎ እጅ ይነሳል። አረፋይኔ ሙዝ ይተክላል። የሙዙ ተክል ግን ከአረንጉዋዴ ወደ ቢጫነት ይለወጣል። የሚበላ ሙዝ ለልጆቹ አያፈራም። አረፋይኔ ቢበሳጭ ማን ይገረማል? አማካሪው ደግሞ እንደ ሻለቃ ሃይሉ ያሉ የእርሻ መሃይም... "ስብል እንኩዋንስ በትራክተር የታረሰ መሬት ላይ ይቅርና ድንጋይ ላይ ይበቅል የለ? የሚሉ ደንቆሮ ናቸው።
2. ደግሞ ከአዲስ አበባ ብሄረ ጽጌ፣ ገብረተንሳይ የሚባል ረዘም ያለ ሉጫ ራስ ሰውዬ አምባውን በአበባ ተክል ለማስጌጥ ሃላፊነት ወስዶዋል። ቀን ላይ የአምባው ሙቀት ወደ 40 ዲግሪ ይደርሳል። በጣም ይሞቃል። ትንሽ እውቀት ላለው ሰው አበባ ውሃ መጠጣት ያለበት ሙቀቱ በረድ ሲል ነው... ትነትን ለመቀነስ። ውሃው ከጥዋት እስከማታ ሲፈስ ነው የሚውለው... አበባው የሚጠጣው የፈላ ውሃ ነው ማለት ይቻላል። እንደዛ አይነት ገልቱነትና ብኩንነት አይቼ አላውቅም። አይፈረድበትም። እርሱም ሌላ መሃይም ነው እንደ አረፋይኔ።
3. ከነዚህ ካለሙያቸው ከተቀጠሩ ሚስኪኖች ሌላ... እውቀት ያላቸው ሰራተኞች አሉ። አንዱ በአዝእርት ሳይንስ ከአለማያ ኮሌጅ የተመረቀ አምሃዬ ነው። ምን ስብል ይዘራ? ስንዴ፣ በቆሎ? መሬቱ በትራክተር ታርሱዋል። ዝናቡስ አስተማማኝ ነውን? የለም አርቆ አሳቢው መንግስቱ ሃይለማሪያም ያየውስ ወንዝ ውሃ የለውም እንዴ? ባይዘንብም በመስኖ ነው እንጂ.... ወዲሁስ ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናደርጋለን የሚለው መፈከር መሪ ቃል አይደል? ተዘራ። ትንሽ ቡቃያ ታየ። በቃ። በቆሎ በመጠኑ ያፈራል። ስንዴው ድካም ሆነ። ያን ሁሉ መሬት በመስኖ ማጠጣት የማይቻል ነው። ለምን? የግድቡ ውሃ ሊያልቅ ይችላል። አርቆ አሳቢ መሪያችን ሂሊኮፕተር ላይ ሆነው ያዩት የጅዶ ወንዝ የሚፈሰው ከየቦታው ከሚጠርቀመ ጎርፍ ነው። ዝናብ ሲያቆም ጅዶም ድርቅ ነው። ሲዘንብ ብቻ ነው ጅዶ ነፍስ ያለው። ጅዶ ከማያቁዋርጥ ምንጭ አይደለም የሚፈሰው።
3.1 ከዚህም የባሰ ችግር አለ ይለናል እውቁ የአፈር ጥናት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ታምሬ። አፈሩ በጣም ጨዋማ ስለሆነ ለስብል እርሻ አይሆንም። የውሃው ጨዋማነት ደግሞ ከአፈሩ ይበልጣል። ጨው በጨው። ግድቡ የተሰራው ከስድስት እስከ አስራምንት አመት እድሜ ያላቸው ልጆች ከሚያድሩበት ቤት፣ከሚበሉበት የምግብ ቤትና ከሚመማሩበት ትምህርት ቤት በላይ ነው። ውሃው በአፈሩ ውስጥ ያለውን ጨው እያማሙዋው ስለሚዘልቅ ግድቡ ሳይታሰብ ሊናድ ስለሚችል የልጆቹ ህወይት አደጋ ላይ ነው። ይኽ ውሃ ውሎ ሳይድር ወደ ጅዶ ይመለስ! አደገኛ ነው። ታምሪ የደቡብ ሰው ናቸው። አይፈሩም።
3.2 ጨው የሚቁዋቁዋም ስብል አርቆ አሳቢ መሪያችን ሳያውቁ አይቀርም። ግን ደፍሮ የሚጠይቃቸው ማን አለና? ደፍሮ መጠየቅ እኮ ዋጋ ያስከፍላል። ይኼ እኮ የሰጡት ትእዛዝ ትክክል አልነበረም ያልተጠና ነበር ሊሆን ነው። አርቆ አሳቢ መሪያችንን አጭር ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነው! ደፋር መቼም አየጠፋምና ጉዳዩን ሳይሰሙት አልቀሩም። ለዚህም ይመስላል ከእስራኤል አገር አንድ ሽማግሌ የአፈር ጥናት ሳይንቲስት የመጣው። ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስንማ ማን ያምነዋል? እስራኤሉ የጨውን መጠን ለመቀነስ የተፈጨ በሃ ድንጋይ [ጂፕሰም] ተጠቀሙ አለ። የሚያስፍልገው ጂፕሰም ግን የራስ ዳሽን ተራራን የሚያህል ክምርም ያህል አይበቃውም። ካልጠፋ ቦታ? ስንት ለሰብል ተስማሚ ቦታዎች እያሉ? ሽማግሌው ጥሩ ሰው ነው። ይኼን ሁሉ የሚነገረኝ አምሃዬ የወተት ከብቶች እርሻን ጣቢያ ሊያስጎበኘው መጥቶ ለመጀመሪያ በሕይወቱ ትኩስ ወተት ሰተነው እየጠጣ ነው ።
4.የከብት ርቢው ሌላ ጉድ ነው። የላሞቹ ቤት ተሰርቱዋል። የቤቱን ሙቅት ለመቆጣጠር ብዙም ችግር የለውም። ትልቁ ፈተና ላሞቹ ከቤት ውስጥ ወጥተው ሳር እንዲግጡ ለማድረግ አለመቻሉ ነው። አላጌ መዥገር ሞልቶአል። በመዥገር ሳቢያ የሚተላለፍ ሃርት-ዋተር የሚል በሽታ ደግሞ አለ። መዥገሩ ከነከሳቸው በሁዋላ ልባቸው ውሃ ይቁዋጥራል። ብዙዎቹ ይሞታሉ። የተረፉትም በደምብ አያገግሙም። በጣም ውድ ላሞች ናቸው። ይኼ ብቻ አይደለም። ለነርሱ የሚሆን መኖ አምባው ስለማያመርት የሚበሉትና የሚያታሉቡት ሲሰላ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። የፖለቲካ ፕሮጀክት እንጂ ትርፍ ያለው አልነበረም።
4.1 የዶሮ ርቢውም በመኖ ወጪ ሂሳብ ሲሰላ የሚሰራው በኪሳራ ነበር። ሌላው ቀርቶ ለእርድ የደረሱት ዶሮዎች በጊዜ አይታረዱም ነበር። ወይም አይሸጡም። ጎብኚ እንግዳ ሲመጣ ሃያ ሰላሳ ዶሮ ለአሮስቶ ይታረዳል። ለልጆቹም ይታረዳል። ሲዊድኖች በየጊዜው እየመጡ ፕሮጀክቱን ይከታተላሉ። አንዴ ሻለቃ ለማ ቁጮ ከሚባል የአምባው ባለስልጣን ጋር የሲዊዲን ኢምባሲ ባለስልጣን ሊጎበኘን ይመጣል። መልሱን የማውቀውን ጥያቄ ጠየቀኝ። እዛው አምባ ውስጥ ካለአግባብ ሃያ ሁለት ቀን ከተቀሩት የስራ ባልደረቦቼ ጋር ጣራውም ግድግዳውም በቆርቆሮ የተሰራ እስር ቤት ታስሬ ስለነበር... አስብ የነበረው እንዴት ከዚያ ግቢ ለመልቀቅ እንጂ ሌላ አምባውን 'ስም ሊያጠፋ' የሚችል እውነት ለፈረንጅ ተናግሬ ጣጣ ውስጥ ለመግባት አልፈልኩምና... አንድ ዶሮ ለእርድ እስኪደርስ ድረስ የሚባለውን የመኖ መጠን እንድነግረው ለጠየቀኝ ጥያቄ፣ ዶሮቹ የሚቆዩበትን ጊዜ በርግጥ ለመናገር ስለማይቻል የመኖንና የስጋ ክብደታቸውን ግንኙነት በግምት ለመናገር አስቸጋሪ ነው ብዬ አልኩ። ለመናገር እንዳልፈልኩ ስለገባው አዲስ አበባ ስመጣ እንድጎበኘው ካርዱን ሰጠኝ። እኔ ስራ አጥቼ... አልሄድኩም።
5. የእንሳስትና እንሳሳት ተዋጽ አለቃዬ ብልጥ ነው። የአምባው የእርሻ አጠቃላይ ስራ አስኪያጅ ግን የዋህ ሰው ነው። አጠቃላይ ስራስኪያጁ የአዋሽ የእርሻ ልማት ስራስኪያጅ የነበረ ነው። ወደ ሕጻናት አምባ ሲዘዋወርም አምባው በእርሻ ከሚገኝ ገቢ መተዳደር ስላለበት እርሱ የአምባውም ዋና ስራስኪያጅ እንደሚሆን ገምቶ ይሁን ቃል ተገብቶለት ነው። በሁለቱ ሰዎች መካከል ታዲያ ጥልም ባይኖር ግንኙነታቸው ከአንገት በላይ ነው። አምባው እንደ አግባቡ በሕጻናት ኮሚሽን ስር መተዳደር ሲገባው፣ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ነበር የሚተዳደረው። አዛዥ ናዣዡም ካሳ ከበደ ናቸው። በአምባው ሌላ ቀደማዊ አገልግሎት በሚል የተዋቀረ አስራር አለ። የዚህም ሃላፊው እኔ በነበርኩበት ጊዜ ጸሃይ ፈለቀ የሚባል ቀይ ሰውዬ ነበር። እውነቱን ለመናገር የአምባው ስራስኪያጅም እርሱ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ በዋናው ማናጀር ዘመድኩንና ጸሃይ መካከል ጤናማ ግንኙነት የለም። የኔ የቅርብ አለቃ ... ሽመልስ ደግሞ ገለልተኛ ለመሆን ቢሞክርም የነ ጸሃይን ጥንካሬ ስለሚገነዘብ የሚሰራው ስራ እንዳይታጎል ከነርሱ ጋር ተግባብቶ ይሰራል።
5.1 ሽመልስ አንዴ " ቦጋለ ለአገራችን የተፈጠርነው ልንሰራላት ሳይሆን ልንሰራባት" ነው ያለኝ እስካሁን አይረሳኝም። ነገሩ እንዲህ ነው። ከሽመልስም ሆነ ከዘመድኩን እውቀት ውጭ ለአምባው የወተት እርሻ የሚሆን ዘመናዊ የማለቢያ ፕላንት/መሳሪያ ከአልፋ ላቫል የሚባል የሲዊድን ካምፓኒ ተገዝቶ ይሁን በርዳታ ስም ይመጣል። ፕላንቱ በአንዴ 12 ላሞችን ለማለብ የሚያስችል ነው። ላሞቹ የታለቡትን የሊትር ቁጥር ይመዘግባል፣ ወተቱም በቀጥታ ወደ ማቀዝቀዣ ይከታል። ሁሉም ነገር ወቶተካ (automatic) ነው። ሰው የሚያስፈልገው ላሞቹን ወደ ማለቢያው አስገብቶ ጡታቸውን አጽድቶ የማለቢያውን አራት ክልስተርስ(miliking clusters) ውስጥ ጡታቸውን መክተት፣ ከዚያም አውልቆ ከማለቢያው ማስወጣት ነው። አንድ ሰው ሁሉንም ሊሰራው ይችላል። በወቅቱ ግን ይታለቡ የነበሩ ላሞች አርባም አይሞሉም። ላሞቹም በአማካይ የሚሰጡት ወተት ከ15 ሊትር በላይ ስላልሆነ ወተቱ ለልጆቹ ፍጆታ ነው የሚውለው። በተጨማሪም ቀደም ሲል ላሞቹ እዚያው ከበረታቸው ሳይወጡ እንዲታለቡ.... ቫኪዮም እንዲፈጠር የሚያስችል ቱቦ በበረቱ ልክ ተዘርግቶ miliking clusters ባለው ባልዲ ከሾላ በረት ተቀጥረው በመጡ ታታሪ አላቢዎች ይታለቡ ነበር። ይኽ በቂ ነበር።
5.2 ታዲያ ዘመናዊ ማለቢያው ተተከለ። ወዲያው ችግር መጣ። አንዱ የወተት ማቀዝቀዛ አልሰራ አለ። ኬንያዊው ኢክስፕርትም ፣ አንደኛው ማቅዝቀዝዛ እስካልሞላ ድረስ ሁለተኛው ሊሰራ አይችልም አለን። አላመነውም። ከኢትዮጵያ የመብራት ሃይል ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች አስመጥተን አሳየን። ወዲያው ሽቦዎቹን ፈታተው ሁሉቱም ማቀዝቀዝዎች እዲሰሩ አደረጉ።
ይሁን እንጂ ለእኛ ምርት ተመጣጣኝ ስላልሆነ... አንድ መቶኛ ካፓሲቲውን እንኳን አንጠቀምም... ከብቶቹን እዚያው በቆሙበት ማለባችንን ቀጠልን። ዘመናዊው ለጎብኝዎች ነው። እንደ ክት ልብስ አይነት። በሁለተኛ ደረጃም አንዱ የመሳሪያው ክፍል ቢበላሽ ምንም ሌላ ተተኪ አልነበረንም። መቼም ይሄን በመንግስቱ ትእዛዝ ተደረገ ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ጸሃይ ፈለቀ ግን ከሚኒስትሩ እውቀት ውጭ በርዳታ መልክ ይቀበላል ወይም ይገዛል ማለት አስቸጋሪ ነው። ይኽ ጉዳይ በግዢ የመጣ ከሆነ እንደ ታምራት ላይኔ የስኩዋር ችግር ባይበዛበትም ጨርሶ የለበትም ለማለት አስቸጋሪ ነው።
አሳማ ርቢውም ያው ነው። በኪሳራ ነው የሚሰራ የነበረው። ምናልባት ወጪ ስለሌለው የንብ ርቢው ነበር የሚሻለው ምንም እንኩዋን ግራሩ አላግባብ ቢጨፈጨፍም።
እንደ ማጠቃለያ....
እንግዲህ ከላይ እንዳየነው አምባው በቅንነት የተመሰረተ ነበር ብንል እንኩዋን፣ በጥናት የተመሰረተ ስላልሆነ ከውድቀት ሌላ አማራጭ አልነበረውም። አፈራረሱ ኢሰባዊ መሆኑን እጋራለሁ። ወያኔ ምን ርህራሄ አለውና? የጭን ቁስልን አንብቤ አልቅሻለሁ።
ካሳ ከበደ ሳይታጀቡ ራሳቸው መኪና እየነዱ በተከታታይ ወደ አምባው ይመጡ ነበር። ታዲያ እርሳቸው ሊመጡ ነው ሲባል ጭንቅ ነው። ምጥ ነው። ምንም ግን የሚለወጥ አስተዳደራዊ ነገር አልታየም። ካሳ ከበደ አንዴ በኢሳት ቴሌቪዝን ተጠይቀው ሕጻናት አምባ አድጎ፣ ኩባ ተልእኮ፣ አሁን የልብ ሃኪም ሆኖ ያከማቸው ልጅ.... "የኔ ካሳ ነህ?" ብሎ ስለጠየቃቸው የተሰማቸውን ደስታ መግለጣቸውን አስታውሳለሁ። ደስ ይላል። ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አምባው ሌሎች መሰረታዊ ድክመቶቹ እንዳሉ እንኩዋን ሆኖ ባለሙያዎችና ሃቀኞች እንዲያስተዳድሩት አልተደረገም። ከጮሌው ጸሃይ ዘመድኩን ለአምባው የተሻለ ሰው ነበር። በቀዳማዊ አገልግሎት፣በእርሻው ስራስኪያጅ የነበሩት መራራቆች ሆን ተብለው የተፈጠሩ ነው የሚመስለው።
ካሳ ከበደ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከተነሱ በሁዋላ በምትካቸው ብርሃኑ ባዬ ተሹመው ነበር። ይኼን ሹመት ተከትሎም የታሰሩ የአምባው ባለስልጣኖች ነበሩ ። አንዱም ጸሃይ ነበር። የእሰሩ ምክንያት ከንቅዘት ውጭ ይሆናል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ነው።
በጦርነት አባቶቻቸውን ያጡ ልጆች መንግስቱን እንደ አባታቸው ማየት ማቆም አለባቸው። ሌላው ይቅር መንግስቱ ሻእቢያ እኮ ናቅፋ መፈናፈኛ አጥቶ ሊደመሰስ ሲል እንዳይደመሰሰ ያደረጉ መሰሪ ናቸው። ራስ ወዳድ ሰው ናቸው። ያስቆሙበት ምክንያትም ሻእቢያን መደምሰስ ያለበት፣ በከበበው ጦር ሳይሆን ለታሪክ ሽሚያ ሲባል እርሳቸው አባል በነበሩበት ጦር ነው ተብሎ ያ ሁሉ ትእዛዝ እስኪፈጸም ድረስ ሻቢያ ለመቁዋቁዋም ጊዜ በማግኘቱ ነው። ይኼን ያጋለጡት እነ ደራሲ በአሉ ግርማ ታርደዋል። በሌላ አነጋገር አባቶቻችሁን በተለይ በኤርትራ ጦርነት ይማግዱ የነበሩት ራሳቸው መንግስቱ ነበሩ። ጦርነቱ እንዲቆም ፍላጎት አልነበራቸውምና። ይኼን ደግሞ በመጨረሻው ስልጣናቸው ዘመን እንኩዋን የአገሪቱን ቁንጮ ጄኔራሎች ሰላም በመፈለጋቸው ብቻ መቆርጠማቸው ምስክር ነው። ስለዚህ አባትን እያስጨረሱ ልጅ የማሳደግ ፖለቲካ ስብአዊኒት ያለው ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው። ልጅ ከአቅም በላይ ካልሆነ ማደግ ያለበት ከህብረተሰቡ ውስጥ ነው። የሕጻናት አምባ ፕሮጀክት የመንግስቱን የቅጥፈት አባታዊነት ገጽታ ለማሳየት ችሎ እንደሆን አላውቅም። ከዚያ ውጭ ከሂሊኮፕተር ላይ የተጸነሰ የመሃይም ፕሮጀክት ከመሆን አልዘለለም። ጨረስኩ።
Vind ik leukRe

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!