በበርበሬ! ከቦጋለ ካሣዬ(አምስተርዳም)
ከቦጋለ ካሣዬ ( አምስተርዳም ) የመጀመሪያው የባሌ ጎባ አዝማች ደግለሃን ትምህርት ቤት ግድግዳውና ወለሉ በእንጨት ነው የተሰራው። ታዲያ የጎባ የእድገት በሕብረት አዝማች ሆኖ የተላከውን መኮንን፤ መሬት ይቅለላቸውና እነ ታምራት ያለው እጁን የፍጥኝ፤ እግሩንም አስረው በርበሬ አጠገቡ በመነስነስ፤ « ለወታደር መንግስት፤ ሕዝብ ላልወከለ ! አልገዛም አለ፤ ሕዝቡ እየታገለ ! አንገዛም ! አንገዛም ! አንገዛም !!» እያሉ በመዘመር የጣውላውን ወለል ሲረግጡት በርበሬው እየቦነነ ሰውየው አይኑ ውስጥ ይገባል። የሰውየው አይን ተጎልግሎ ሊወጣ ያለ እንደነበር እስከዛሬ ይታየኛል። እኔና አብሮ አደጌ አብርሃም ያኔ ዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ስለነበርን አልዘመትንም። ታዲያ ዘማቾች ቅጥር ግብያችን ውስጥ ለስብሰባ መጥተው ነው፤ ወታደር አዝማቻቸውን በበርበሬ ሲለበልቡት የምንታዘበው። መዝሙሩን ግን ወደነዋል። አሁን ዝም ብዬ ሳስበው አድራጎታቸው ሰላማዊ ባይሆንም፤ የወታደራዊውን አገዛዝ እንዴት ይጠየፉ እንደነበርና ለራሳቸው ደሕንነት ምንም የማይፈሩ ወኔ ያላቸው ትኩስ ወተት የጠገቡ አንበሶች ሆነው ይታዩኛል። ታምራት ያለው ሲዘምት የ 11 ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ጋሼ ወልደሰማያት የሚባል የሂሳብ አስተማሪ ነበረን። ሰነፍ ስለነበር ብዙውን ግዜ ቀላል ቀላሉን ነገር ነው የሚስተምረን። አንዳንዴ ታምራት መጥቶ እንዲያስተምረንም ያደርግ ነበር። ታምራት ከጋሽ ወልደሰማያት አስር እጥፍ ይበልጣል ! ታዲያ ያልገባንና ጋሼ ወልደሰማያት የሚያልፈው...