አስራት !

                                                                             

                                                      አስራት ወልደየስ!  ነብስ ይማር!                                                                                                


                                                                                                                                     ቦጋለ ካሣዬ 

 ...ወያኔ በፕሮፈሰር አስራት ሞት  ግንባር ቀደም ተጠያቂ ቢሆንም… አስራት በራሳቸው አንደበት.."እኔን የቀበረኝ አማራው ነው" በማለት አስረግጠው ነበር።

አማራ ጠልነት

 ሻእቢያ፣ ወያኔና ኦነግ ገና ስልጣን ሳይጨብጡ በአማራው ላይ  ስለሚያካሂዱት ግፎች  መረጃዎች ይወጡ ነበረ።  በኦነግና በሻእቢያ ሶስት መቶ አማሮች በቤተክርስቲያን ውስጥ በእሳት የጋዩበት የአሶሳው አረመናዊ እልቂት አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም መሰረት… የወያኔንና የሻእቢያን ስልጣን ላይ መውጣት አማራውን ለባሰ የህልውና አደጋ እንደሚዳርገው በሆላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ስለተገነዘቡ፤ ገና በፕሮፈሰር አስራት የሚመራው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት(መአሕድ) ከመመስረቱ ቀደም ብለው ለአማራውና አማራን ጠል ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን  ሊሰባሰቡበት የሚችል.." ግዮን" የሚባል የመረዳጃ ማህበር መሰረቱ፡፡ ወያኔም ስልጣን ያዘ። የተፈራውም  አልቀረም…የአርባጕጉ፣ የበደኖ፣ አሰቦት፣ የጎንደር እየሱስ ወዘተርፈ እሊቂቶች ጎረፉ!
 ለጥቆም መአሕድ እንደተቁዋቁዋመ የመአሕድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ኢንጂነር አስናቀ፤ ከአዲስ አበባ  ወደ አምስተርዳም ልጃቸውን ለማየት መጡ፡፡ .መአሕድን ሊደግፉ የሚችሉ ሰዎች ሲያፈላልጉ የእኛን(የግዮንን) ስብሰብ አገኙ፡፡ ሁሉም አልጋ በአልጋ ሆነና፤ ከኢትዮጵያ ውጭ የመጀመሪያው የመአሕድ የድጋፍ ኮሚቴም በአምስተርዳም ሆላንድ ሊመሰረት በቃ፡፡ የዛሬ ሃያ አምስት አመት መሆኑ  ነው፡፡ ኮሚቴው ከመአሕድ ጋር ግንኙነት ፈጠረ፡፡ አስራትም  ኮሚቴው የላከው  ገንዘብ መድረሱን አረጋግጠውና አመስግነው..."ድጋፋችንን አጠናክረን እንድንቀጥልና በድጋፉ ሰጭ ድርጅት  ውስጥም በኢትዮጵያ  አንድነትና በልጆቹዋ እኩልነት  የሚያምኑትን ሁሉ እንዲሰበሰቡበት" አደራ አሉን፡፡ እኛም እንደተባልነው አደረግን፡፡ ለጥቆም በለንደን ከዚያም በሲዊዲን ተመሳሳይ የድጋፍ ኮሚቴዎች ተመሰረቱ፡፡ እኛን በአምስተርዳም ያደራጁን የመአሕድ የማእከላዊ ኮሚቴው አባል… አዲስ አበባ ከተመለሱ በሁዋላ ከመአሕድ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳላደረጉ አስራት በደብዳቤያቸው ገልጠው ነበር፡፡ ኢንጂነሩን… ነፍሳቸውን ይማረውና...ገና ከአምስተርዳም ሳይነሱ ያስፈራራቸው ሰው እንደነበር ማስብ ይቻላል፡፡  ገንዘቡንና ደብዳቤያችንን  ግን በሌላ ሰው በኩል እንዲደርስ  አድርገዋል።

 የመአሕድን ፕሮግራም በደንብ አጠናነው። ከቅርጹ በስተቀር ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ ነው። በቅንነት ስራችንን ቀጠልን፡፡ ብዙዎቻችን  የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን(ኢሕአፓ) ደጋፊዎች ነበርን። ይሁንና ከኢሕአፓና ከሌሎች ግለሰቦች ወዲያው ግን  ችግር ገጠመን፡፡ … "ጠባብ... የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች" በሚል ታፔላዎች ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፈተብን። እንተዋወቃለንና የእኛም የመልስ ምት ደግሞ  የወዛ አልነበረም።  ታዲያ ተቀናቃኞቻችን  ሌላ ዘዴ ፈለጉ፡፡ አንዳንድ በውስጣችን ያሉ  ጀሌዎችና አቅመ ደካሞችን በመቅረብ በተለይ በድርጅቱ ሊቀመንበርና የፕሮፓጋንዳ ዘርፍ ሃላፊዎች ላይ በማነጣጠር 'አማራውን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ሊያላትሙት' ነው የሚሉ  አሉባላልታዎች በሰፊው አሰራጩ፡፡ ለሁለት አመታት የአንድነት ጋዜጣን ጭምር  ከአዲስ አበባ በቀጥታ እያስመጣና ለፈለገው ሁሉ በማሰራጨት ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ኮሚቴ  ... ምርጫ ደረሰና  በሌላ ኮሚቴ  ተተካ። አዲሱ ኮሚቴ ትንሽ ወልገድ ወልገድ ብሎ ቀጥ አለ።
ይሁንና ውሎ አድሮ  አስራት የዘራው ዘር እንደገና አጎነቆለና… ሞረሽ ወገኔ የአማራ አንድነት ድርጅት ደግሞ  ተመሰረቶ  አማራውን በማንቃት ከፍተኛ ስራ መስራቱን ቀጠለ።  ቀጥሎም  አማራውን  በማህበራዊ ሚዲያ… ቤተ አማራና በአማራ ተጋድሎ ተደራጅተው የመጡት   ትኩስ ሃይሎች ቀሰቀሱት። ቀጥሎም የአማራንም ሆነ የኢትዮጵያን  ብሄረተኝነት በኢትዮጵያ  ከህግ ውጭ እጄን አልሰጥም ብሎ 9 የወያኔ ልዮ ሃይል ታጣቂዎችን ከጥቅም ውጭ ያደረገው ጀግናው ኮሎኔል ደመቀ አየለ  ብሩ ተኮሰው።  አሳልፊ አልሰጥም ብሎ የተመመው የጎንደር አንበሳም ሌላው ታሪካዊና አኩሪ ተዋንያን ነው።  አሁን ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)  መመስረት የአማራውን አደረጃጀት ቅርጽ እያሲያዘው መጥቶአል። አብን የሚመራው በተማሩና በሳል በሆኑ  ወጣቶች ነው።   በቅርቡ ደግሞ አስራት ሚዲያ  ተቁዋቁሞ ማለፊያ ስራ እየሰራ  ይገኛል።
በተጨማሪም የአማራው ልሂቃን በብሄር በተለከፈች ኢትዮጵያ ውስጥ አማራው ራሱን ለመከላከልና ለኢትዮጵያም ህላዌ ቀጣይነት መደራጀቱ ተገቢ ነው ስንል የነበረውን አማክንዮ እያመኑበት መጥተው …"አማራ የሚል ስሜት የለም" ከሚል የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም  ተጨባጫ-አልቦ አስተምሮት በመላቀቅ..  እንደ ይልቃል ጌትነት ያሉት ትግሉን ሲደግፉ  ማየት ፖለቲካው መሬት መርገጡን ያሳያል። አስራት ይኼንን አማራ የለም የሚል ሃሳዊ ትርከተ…" አንዳንድ ምሁራን አማራ የለም ይላሉ። የአማራ ጠላቶች ግን አማራን ፈልገው ሲያጡት አይታይም። "ብለው የሞገቱት የዛሬ 27 አመት ነበር።

እኔን የቀበረኝ…ተጠንቀቅ አማራ…

በተቃራኒው ለምሳሌ  የሰማያዊ ፓርቲን አግባብ ባልሆነ መንገድ አመራሩን ተቆጣጥሮ ራሳቸውን ሹመኛ ያደረጉ እንደ አቶ የሺዋስ አሰፋ ያሉ ሰዎች ላይ  አማራው እምነት ሊጥል አይገባም። እነ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ገጠመው የተባለውን ችግር ለመፍታት የተመሰረተውን ሽምግልና ሆን ብለው አልተቀበሉም ። እነ የሺዋስ የመርህ ሰዎች አይደሉም። በህብረ ብሄራዊ ድርጅት ካባ  አስራት እንዳሉት ... አማራውን ቀባሪዎች እንደዚህ ያሉ ሰዎች ናቸውና…ተጠንቀቅ አማራ!
ከየሺዋስ አሰፋ በተለየ አማራው  በአንደበተ ርቱእ  አንዱአለም አራጊ እንዳይጠቃ ከፍተኛ  ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። አንዱአለም በቀደም ከስዩም ተሾመ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ላይ፤ በቀጥታ ባይናገርም እንደነ አብን አይነት ድርጅቶችም የተመሰረቱበትን ምክንያት ከሌሎች የብሄር ድርጅቶች ምስረታ ጋር ያመሳስለዋል። በቃለ ምልልሱ ላይ እንደ አብይ አህመድ ሁሉ አማራው ከሌሎቹ ማህበረሰቦች ተለይቶ ጥቃት አልደረሰበትም ወደ ሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሶአል። እንዴት ይኼ ሊሆን ይችላል? አይኔን ግንባር ያደረገው ነው እንዴ? ሲጀመር ኦነግ፣ ሻእቢያ ይሁን ወያኔ የመጨቆን ትርክታቸው እነ ብርሃኑ ነጋ የሚጋሩት ልብ ወለዱ የአማራ ጭቆና አይደለም እንዴ? ከዚያስ… ወያኔ ይሁን ኦነግ(ለጥቂት ጊዜ)  ስልጣን ከያዙ በሁዋላ አማራውን አይደለም እንዴ ያፈናቀሉት? የጨፈጨፉት? ወያኔ ስልጣኑን ካደላደለስ በሁዋላ ከፖለቲካ፣ከኢኮኖሚ ተሳትፎ የተገለለው አማራ አይደለም እንዴ? ከዚህስ በባሰ በክትባት ሰበብ የሕዝብ ቅነሳ የተደረገበት አማራ አይደለም እንዴ? ስንቱን ዘርዝሬ እዘልቀዋለሁ። ስለዚህ ምንም እንኩዋን ሌሎች ማህበረሰቦችም አልተጨቆኑም ባይባልም እንደ አማራ ዛሬም እየተሰቃየ ያለ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ አለ ለማለት ከቶውንም አይቻልም። ለዚህም ነው ይኼን ጉዳይ በለቅሶ ሳይሆን በድርጅታዊ ኃይል ለመለወጥ ግድ ስለሚል እንደነ አብን ያሉ ድርጅቶች የተመሰረቱት። ይኽም ሆኖ አብን  ደጋግሞ እንደገለጸው በመስኮት አሻግሮ ማየት የሚችል ጭፍን ብሄረተኛ ያልሆነ ድርጅት ነው።

አድፋጭ…

አንዱ የአማራ ጠላቶች ሥልት በኢትዮጵያ ተሰሚነት ሊኖራቸው በሚችሉ ሰዎች ጀርባ አድፍጠው አማራውን ማጥቃት ነው። በተለይ ትግሬዎች ይኼን ተክነውበታል። ለምሳሌ የወልቃይትን ጥያቄ በሚመለከት የወያኔ መስራች አረጋዊ በርሄ (መጀመሪያ ወልቃይትን የወጋ ነው)  ጉዳይ በህዝበ-ውሳኔ ሊፈታ ይችላል  ብሎ የስዬ አብርሃምን ሃሳዊ መፍትሄ አስተጋብቶ ነበር። በሁዋላ አረጋዊ ተቃውሞ ሲበዛበት ጊዜ  የፕሮፌሰር መስፍንን መፍትሄ ቀዳና የወልቃይት ጥያቄ ቀሽም ነው፤ የሚፈታውም በዜግነት ፖለቲካ እንደሆነ ነገረን.. ምንም እንኩዋን ራሱ አረጋዊ ዛሬም ከጎሳ ፖለቲካ  ያልተላቀቀ ታማሚ ቢሆንም። አሁንም እንደ ብርሃኑ ነጋ ያሉ ጮሌዎች ከአንዱ አለም አራጊ በስተጀርባ ያደፈጡ አማራ ጠል መሆናቸውን አማራው ሊዘነጋው በጭራሽ አይገባውም።   አንዱአለም ..እንስከን ብሎአል። በጣም እስማማለሁ። ታዲያ ስከን ብለን ግንቦት-7 ምን አይነት ድርጅት እንደነበረ… አረበኞች ግንቦት-7 ውስጥስ ምን እንደተደረገ ካወቅን ከጀርባችን ያደፈጡትን ለማየት እድል እናገኛለንና ስክነቱ ለራሱም እንደሆነ ሊያጣው አይገባም።  ሳይሰክኑ ታዋቂነትን ተጠቅሞ አስተያየት መስጠት  ላለአስፈላጊ ጠብ ይዳርጋልና። አንዱአለም ዶክተር ኪንግን በመጥቀስ ፤ የትንሾች ጩኸት ጎልቶ የሚታየው ብዙሃኑ ዝም ስለሚል ነው ስለዚህ እያንዳንንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት በመውሰድ እነዚህን አቃጫዮች አደብ እንዲገዙ ማድረግ ይችላል ሲል ተደምጦዓል።  ይኼ መቼም ፖለቲካን ሞራላዊ ሽፋን መስጠት ካልሆነ በስተቀር በአጭር ጊዜ ተግባራዊ አይሆንም። በየትኛውም ማህብረሰብ ፖለቲካ የሊሂቃን ወይም የጥቂቶች ስልጣንን ለመቆጣጠር የሚደረግ ፍክክር ነው። በማንኛውም ትርከት ይሁን በየትኛው የጫወታ መድረክ ብዙሃኑ ሊሂቃኑን ሰምቶ መከተሉን ወይም የሚሻለውን ከመምረጥ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም... ምርጫው ትክክል ይሁንም አይሁንም። ይኼ በረዢም ጊዜ በትምርት ሊቃለል የሚችል ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ይኼን ነገር አንዴ ኖሃም ቾምስኪ በማጤን የኢታሊያንና የአማሪካን ማህበረሰቦችን ያወዳድራል። በኢታሊይ አንድ ዜጋን የኢታሊያ መንግስት ጠላት ነህ ብሎ አንድ ኢታሊያዊ ሌላውን ለማስፈራራት ቢሞክር አስፈራሪው ይሳቅበታል እንጂ ጩኸቱን ከቁም ነገር የሚቆጥረው የለም። እንደውም አስፈራሪው እንደ እብድ ነው የሚቆጠረው። አንድ አሜሪካዊ ግን ሌላውን የአሜሪካ ዜጋ የመንግስት ጠላት ነህ ቢለው  ተስፈራሪው ሰውዬ ራሱን ተጠራጥሮ ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ ይገባል። አስፈራሪውም አድማጭ ያገኛል ይላል። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ውስጥ ሆላንዶች አይሁዶችን ለናዚ አሳልፈው ያልሰጡ ጥቂት ቢኖሩም… አብዛኛዎቹ ግን የናዚን አይዶሎጂ በመቀበላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አይሆዶች አሳልፈው ሰጥተዋል። ይኼ ጉዳይ የተቀለበሰውም በሞራል ስብከት ሳይሆን በድርጅታዊ ሃይል ነው። አሁንም አልቆም ያለው የአማሮች ማፈናቀል ምክንያቱ ከዚሁ  አማራ ጠላትህ ነው ቀጣይ ትርከት ተሰሚነት ጋር በሚገባ የተሳሰረ ነው። የእነ ጃዋር፣የእነ በቀለ ገርባና የአጠቃላይ የኦነግ ተደማጭነት በሞራል ተኖ የሚሄድ ጉም አይደለም።  በድርጅት ነው የሚታረቀው። አንዱ አለም በደግ ስብእናው አማራውን ሊቀብሩ ከሚፈልጉ ጋር ተሰልፊያለሁ ወይ? ብሎ በጥሞና እንደሚያስብ ተስፍ አለኝ። አለበለዚያ የተቆጣን ሕዝብ የባሰ ማስቆጣት አያስደምርም።በእርግጠኝነት ግን ያስቀንሳል።

ድርጅታዊ ጥንካሬነት…

አማራው ዛሬም በገጠር ይሁን በከተማ ይፈናቀላል። የገበሬው መሬት ሆነ ጣና  በእንቦጭ እየጠፉ ነው። ሆን ተብለው የሚለኮሱ እሳቶች ትልቅ ጉዳት እያሥከተሉ  ነው። አማራ ወዳድ የፖለቲካ ይሁን የሲቪክ ማህበራት እነዚህንና ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቆጣጠር መደራጀት አለባቸው። አማራው ሁለት ቢበዛ ከሶስት በላይ የፖለቲካ ድርጅት አያስፈልገውም። እነዚህም ቢሆኑ በብዙ ጉዳዮች ላይ አብረው ሊስሩ ይገባል። የድርጅት ጋጋት ሃይልን ስለሚበታትን ለጠላት አጋላጭ ነው።   ስለዚህ አሁን የምናቃቸው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) ፣የአማራ ህልውና ለኢትዮጵይ አንድነት ድርጅት(አህኢአድ) ፣የአማራ ዴሞክራ ኃይል ንቅናቄ(አዴኃን) ፣የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ሌሎች ተቃዋሚዎች፤ በስልጣን ላይ ያለውን የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ(አዴፓ)  በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ለመረከብ ይሁን  በቅንጅት ለመስራት የሚያሽችላቸውን አቅም ለመፍጠር መቀናጀት ሳይሆን  መዋሃድ አለባቸው። በአገር ውስጥ በተለይ የአማራ ወጣቶችን የማደራጀቱን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ወሳኝ ነው። የወልቃይት፣የጠገዴ፣የራይ፣የደራ እንዲሁም የመተከል የመብት ጥያቄዎች መቀናጀትና መደጋገፍ አለባቸው።

በውጭ አገር ለአማራ ከቆሙት ግንባር ቀደሙ የሲቪክ ማህበር አንዱ  ሞረሽ ወገኔ… በቅርቡ ተጠናክሮ ይወጣል  የሚል ሙሉ እምነት አለን። ሌሎች በውጭ አገር የሚገኙት የዓማራ ማህበራትና የአማራ ባለሙያዎች ድርጅትም…አንድ ሊሆኑ ባይችሉም በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል።  ለምሳሌ ከአማራው ባህል አንጻር ሁሉም ድርጅቶች ሞረሽ በሚል ጥላ ስር ቢሰባሰቡ፤ ውጭ አገር ያለውን የአማራ የገንዝብ አቅምና እውቀት ለማስተባበር ይቀላል። ዛሬ ግለሰቦች ናቸው ጉዳት ሲደርስ ወይም አንድ ሃሳብ ብልጭ ሲልላቸው  በጎፈንድሚ ገንዘብ የሚሰበስቡት። አንዳንዶች ሃፍረትም ስለሌላቸው የተዋጣውን ገንዘብ  ኪሳቸው የከተቱ አሉ። እንደዚህ ያለውን የተዝረከረከ  አሰራር ለማስቀረት ተጠያቂነት የሚኖረው ተቁዋማዊ አደረጃጀት በጣም አስፈላጊ ነው። ዛሬ ሃያኛው አመት የአስራት መታሰቢያ ለማክበር በምንዘጋጅበት ወቅት ፤ አማራ … ኢትዮጵያን ሳይረሳ በተከላካይ ብሄረተኝነት እየተደራጀ መሆኑን እየተመለከትን ነው።  ይሁን እንጂ በአገር ቤትም ሆነ ከአገር ውጪ የአማራ ተቁዋምያዊ የድርጅት ጥናካሬዎች በጮርቃነት የሚታዩ ናቸውና ገና ብዙ ስራ መሰራት አለበት። ይሁን እንጂ ከዛሬ 28 አመቱ ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ነንና፤  … " ኢትዮጵያ የልጆቹዋ ሁሉ ትሆን ዘንድ ቀበቶአችንን አሁንም ጠበቅ ማደረግ አለብን። ብሄረተኝነት መጣብን እንጂ አላመጣነውም። ፖለቲካው ከብሄረሰብ ቅድ እስካልወጣ ድረስ በተምኔታዊ የዘግነት ፖለቲካ አንሸወደም። የብሄር ፖለቲካ በህግ ከታገደም አማራ ከቶ አይናፍቀውም። ደረቱን ይዞ ዋይ! ዋይ! እያለ አያለቅስለትም። የሚያውቀውና የሚወደው ሰርቶ፣ ገበያውን አጥግቦ፣ አብሮ መብላትን ነውና።

Comments

Popular posts from this blog

የፋኖ አንድነት እንዴት?

እስከ ስባት ትውልድ!

አሞላቃቂ ጥቅመኛ!