አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሰብአዊ መብቶችና ድርጅቶቻቸው
አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሰብአዊ መብቶችና ድርጅቶቻቸው የደላቸው... የሰው ልጅ ይቅር፤ ማንኛውም ህመም ሊሰማው የሚችል ፍጡር አይጠቃ! አይገደል! ብለው እሪ! እሪ! ይላሉ። ያነባሉ። እንቅልፍ አይወስዳቸውም። የሌሎች ስቃዮች እነርሱንም ያስቃያቸዋል። አንዴ ተማሪ እያለን የደብረ-ብርሃንን የብርድ ልብስ ፋብሪካ ልንጎበኝ ሄድን። አስተማሪያችን ፕሮፌሰር ፓንዲታ የሚባል ህንድ ነበር። ለምሳችን ስጋ ያለበት ሳንዱውች ተዘጋጅቶአል። የደብረብርሃን ብርድ ለጠኔ ዳርጎን ነበርና ሰፍ ብለን ሳንዱቻችንን መግመጥ ጀመርን። አስተማሪያችን ግን ከንፈሩ ደርቆ አይን አይናችንን ያየናል። ለመብላት ፈልጎአል። "ለምን አትበላም?" ብለን ብንጠይቀው፤ "ስጋ አልበላም። እምነቴ ማንኛውንም ፍጡር አትግደል ይላል።" ብሎን እርፍ! በሆላንድ የእንሳስት መብት ተሙዋጋች የፖለቲካ ፓርቲ አለ። አሁን ዳች ፓርላማ ውስጥ ሁለት መቀመጫዎች አሉት። ፓርቲው መሬት ማንኛውንም የሰው ልጆች ፍላጎቶች ለማሙዋላት ትችላለች። ይሁን እንጂ የሰዎች ስግብግብነትን ለማሙዋላት አትችልም ብሎ ያምናል። እንደ ፓርቲው ከሆነ ለምሳሌ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ እንዱስትሪ፤ 30% በተፈጥሮ ይገኙ የነበሩ የእንሥሣትና የእጽዋት ዘሮችን በማጥፋት ተጠያቂ ነው። ከብቶችንም ለማደለብም ሆነ የወተት ጎርፍ ለማምረት መኖ በገፍ ስለሚያስፈልገው፤ በዚህም ሳቢያ መሬት ከድሃ ገበሬዎች ስለሚቀማ፤ የአለም ርሃብ እየተባባሰ የመጣበት አንዱ ዋናው ምክንያት ከእንስሳትና እንስሳ ተዋጾእኦ እንዱስትሪ ተግባር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም የእርድ እንሳሳት ሲታረዱ ...